መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየላዳ ታክሲዎቻቸው በአዲስ እንደሚቀየርላቸው ቃል የተገባላቸው ምላሽ እንዳላገኙ ተናገሩ

የላዳ ታክሲዎቻቸው በአዲስ እንደሚቀየርላቸው ቃል የተገባላቸው ምላሽ እንዳላገኙ ተናገሩ

ከአንድ ዓመት በፊት የላዳ ታክሲዎቻቸው በአዲስ እንደሚቀየርላቸው ቃል የተገባላቸው አሽከርካሪዎች እስከ አሁን ምላሽ እንዳላገኙ ተናገሩ።
መንግሥት ከኤል አውቶ መኪና አስመጭ ድርጅት ጋር በመነጋገር የላዳ ታክሲዎች በአዲስ እንደሚቀየርላቸው ተነግሯቸው የነበረ ቢሆንም፣ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ የላዳ ታክሲ አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የላዳ ታክሲ አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች እንደገለፁት፣ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በተለያየ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኤል አውቶ መኪና አስመጪ ድርጅት ጋር በመነጋገር ታክሲዎች በአዲስ መኪኖች ተቀይረው እንደሚሰጣቸው እና ወደ ሥራ እንደሚገቡ የተነገራቸው ቢሆንም፣ ቅሬታ ከማሰማት ባለፈ መፍትሄ አላገኘንም ብለዋል።

አክለውም፣ ቃል ተገብቶላቸው የነበረው የቀድሞ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት እንደነበር እና የላዳ ታክሲ ባለቤቶችንም ከባንክ ጋር የማስተሳሰር ሥራ የሚሠራ ሲሆን፣ በቀረበው ጥያቄ የተስማሙ ግለሰቦች ዕድሉን ለመጠቀም በማሰብ 30 ከመቶ ክፍያ በባንክ በኩል መክፈላቸውን ጠቁመዋል።

የላዳ አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች አስከትለውም፣ 30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ከባንክ ጋር በማገናኘት ክፍያውን ከፈጸሙ በኋላ አዲስ ታክሲ እንደሚሰጣቸው እንደተነገራቸው እና 70 በመቶውን በየወሩ እየሠሩ ከሚያገኙት ገቢ ላይ እንደሚከፍሉ ተነግሯቸው ነበር። ሆኖም በበኩላቸው የታዘዙትን ክፍያ ከመፈፀም ባለፈ ተግባራዊ የተደረገላቸው ነገር አለመኖሩን አመልክተዋል።

የኤል አውቶ መኪና አስመጪ ድርጅት ውስጥ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የተቋሙ ሠራተኛ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ ለመቀየር የተስማማቸውን መኪኖች ለማስመጣት ሥራ የጀመረ ቢሆንም፣ ሥራ ከጀመረ በኋላ አዲስ መመሪያ እና ለውጥ በመውጣቱ በመንግሥት በኩል ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተፈቀዱ መኪኖች ታግደው ከወደብ ማውጣት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር እፀገነት አበበ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ቢሮው የላዳ ታክሲ አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች እና ታክሲ የሚያቀርቡ ድርጅቶችን የሚስማሙበትን ሂደት የመፍጠር ኃላፊነት ተወጥቷል ብለዋል።

ይህም አሽከርካሪዎች 30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ እንዲፈፅሙ እና 70 በመቶ እየሠሩ የሚከፍሉበትን ሂደት ተነጋግረው እንዲስማሙ የሚያስችል እድል እንደፈጠረ እና መስማማት ላይ መድረሳቸውን ኃላፊዋ ገልፀዋል።

ዳይሬክተሯ በገቡበት ውል መሠረት አሽከርካሪዎች ክፍያውን የፈፀሙ ቢሆንም፣ በአሽከርካሪ አቅራቢዎች በኩል እንዲሁ በወቅቱ አለማቅረብ እና መጓተቶች መስተዋላቸውን ተናግረዋል።

ቢሮው በተጨማሪ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ማለትም አሽከርካሪዎች የማደራጀት እና ታክሲ የሚቀየርላቸውን አካላት የማሳወቅ ኃላፊነት መወጣቱን ያነሱት ዳይሬክተሯ፣ ለዚህም ኹለቱ አካላት የገቡበትን ውል ተንተርሶ የላዳ ታክሲ አሽከርካሪዎች ጥያቄያቸው እንዲመለስ እና የሚቀየርላቸው ታክሲ በቅድሚያ እንዲቀርብላቸው ጉዳዩ ለሚመለከተው ለፌዴራል ትራንስፖርት ሚኒስትር ደብዳቤ መጻፋቸውን አስረድተዋል።
በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መጓጓዣዎችን አዲስና ዘመናዊ እንዲሁም ለቱሪስቶችም ምቹ ለማድረግ ቢሮው በራሱ በኩል የሚያከናውናቸው ሥራዎች እንዳሉም ተነግሯል።

በተጨማሪ ለባለታክሲዎች ከቀረጥ ነጻ መኪናዎችን ለማስገባት ብድር የማመቻቸት ሥራ የሚሠራው እንዲሁ በከተማ አስተዳደሩ ነው ተብሏል።
አዲስ ማለዳ በተጨማሪ ስለ ጉዳዩ ለማጣራት ለፌዴራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ኃላፊ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ ሥማቸው ለጊዜው እንዲቆይ ያስረዱት ባለሥልጣን፣ ጉዳዩ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ሲነሳ ማስተዋላቸውን ጠቅሰዋል።

አክለውም፣ አሁን ላይ በኃላፊነት ያሉበትን ወንበር በቅርቡ መረከባቸውን ተከትሎ ሙሉ እና የተረጋገጠ መረጃ ለመስጠት ባለ ድርሻ አካላትን ለማናገር እንደሚገደዱ ተናግረዋል። አዲስ ማለዳ ላነሳችው ጥያቄም መረጃውን አጣርተው ወደፊት እንደሚያሳውቁ ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች