መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናተቋርጦ የቆየውን የብሔራዊ ባህል ማእከል ፕሮጀክት ለማስጀመር ጥናት እየተካሄደ ነው

ተቋርጦ የቆየውን የብሔራዊ ባህል ማእከል ፕሮጀክት ለማስጀመር ጥናት እየተካሄደ ነው

ለዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማእከል ግንባታ ፕሮጀክት ለማስጀመር በአሁኑ ወቅት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማእከል ተቋም ከለውጡ በፊት ሲታጠፍ አስጀምሮት የነበረው የባህል ማእከል ግንባታ ፕሮጀክትም ተቋርጦ እንደቆየ ገልጾ፣ አሁን ላይ ለማስጀመር ጥናት እየተካሄደ ነው ብሏል።

በዚህም ለፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ እና ለጥናት ተብሎ ከመንግሥት ስምንት ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፣ መጀመሪያ ላይ የማማከር ሥራውን ይዞት ከነበረው የኢትዮጵያ ሕንፃዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ የቆየውን ውል ለማደስ አልያም ሌላ አማካሪ ድርጅት ለመቅጠር ሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ስለሆነም አሁን ያለበት አማካሪ የመቅጠርና ዲዛይንን የማሻሻል ሥራ ካለቀ በኋላ ወደ ተግባር ይገባል ነው የተባለው።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተፈሪ ተክሉ፣ አማካሪ የመቅጠርና ዲዛይን የማሻሻል ሥራው ካለቀ በኋላ አመራሩ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መርምሮ በአዲሱ በጀት ዓመት ስለፕሮጀክቱ አቅጣጫ ያስቀምጣል ነው ያሉት።

ቀድሞ የተጀመረው ስድስት ኪሎ አካባቢ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ቦታው ተቀንሶ ለሌላ ዓላማ በመዋሉና ባህል ማእከሉ በውስጡ የሚይዘው ነገር ሰፊ በመሆኑ የቦታ ለውጥ ሊኖር ይችላል ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም ለግንባታው ምን ያህል ካሬ ቦታ እንደሚያስፈልግም ያን ጊዜ ግልጽ እንደሚሆን ነው የጠቆሙት።

ማእከሉ በውስጡ የባህል እና የዕደ ጥበብ ማእከል እንዳለው አንስተውም፣ በተለይ ባህል ማእከሉ አጠቃላይ ከኪነ ጥበብ ጋር የሚያያዙ ዘርፎች የሚበለጽጉበትና የሚከወኑበት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የዕደ ጥበብ ማእከሉም የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ መገለጫዎቻቸውን እና እሴቶቻቸውን የያዘ ብሎም ለተለያዩ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ሥልጠና የሚሰጥበት ሊሆን እንደሚችል ነው ያመላከቱት።

ኢትዮጵያ የባህል ማእከልም ይሁን የዕደ ጥበብ ማእከል የግድ የሚያስፈልጋት በመሆኑ፣ ብሔራዊ የባህል ማእከል ግንባታ ፕሮጀክቱ የሚቀር አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ሆኖም ካለው ሁኔታ አንጻር በአጭር ጊዜ ይፈጸማል ተብሎ አይገመትም ሲሉ ተደምጠዋል።

ኹሉም የጥበብ ዘርፎች በአንድ ቦታ የሚገኙበት ማለት ነው ሲሉ የገለጹት ብሔራዊ ባህል ማእከሉ፣ ስዕልና ቅርፃ ቅርጽ፣ ሙዚቃና ፊልም፣ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች፣ ዕደ ጥበብ እና ሌሎች የሚዘጋጁበት እንዲሁም የሚቀርቡበት ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ብሔራዊ ባህል ማእከሉ ቴአትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቢሮዎች፣ አዳራሾች እንዲሁም ቤተ መዘክር (ሙዝየም) እና ሌሎችን ያካተተ ሰፊ ማእከል እንደሚሆንም ነው የተገለጸው።

ፕሮጀክቱ ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ሥራ ሲገባ የተያዘለት 250 ሚሊዮን ብር በጀት፣ አሁን ባለው የዋጋ ሁኔታ እንዲሁም የቦታ ለውጥ የሚደረግ ከሆነ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር እና ከዚያ በላይ ሊወስድ እንደሚችል ግምት ተወስዷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች