በምዕራብ ወለጋ በሸኔ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 1 ሺሕ 600 ደርሷል

0
4472

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር/ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ሸኔ የተገደሉ ሰዎች ከ1 ሺሕ 600 መሻገሩን የዐይን እማኞች ገለጹ።

በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን በመሰብሰብ ላይ የተሰማሩና ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ዐይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ1 ሺሕ 600 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ እና 900 የሚሆኑ ሰዎችን ሬሳ ቆጥረን ቀብረናል ብለዋል።

የዐይን እማኞቹ አክለውም፣ እስከ አሁን ሬሳቸው ተገኝቶ ከተቀበሩት ሰዎች በተጨማሪ፣ በመኖሪያ ቤታቸው እንዳሉ ተቃጥለው የተገደሉ እና በተለያዩ ምክንያቶች በጫካ ውስጥ ሬሳቸው ጠፍቶ ያልተገኘበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ከሰኔ 11/2014 ጀምሮ “በኦነግ ሸኔ ቡድን” የተፈጸመው ጥቃት ከፍተኛና አሰቃቂ መሆኑን ተናግረዋል።

በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመው ጅምላ ግድያ ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ተቀባብለው ለዓለም ማኅበረሰብ አድረሰዉታል። በጥቃቱ የሞቱ ዜጎች ቁጥር ጥቃቱ ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን እየጨመረ ሲሆን፣ አሁንም በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ እንዳልሆነ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

በጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የተፈጸመው ጥቃት ማንነትን ያነጣጠረ ጥቃት መሆኑን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በሸኔ ቡድን እና በአካባቢው በሚኖሩ የቡድኑ ተባባሪዎች አማካኝነት የሟቾች እና የተፈናቃይ ሰዎች ንብረትም ተዘርፏል ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች አክለውም፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ለሚኖሩ የማኅበረሰቡ ክፍል የክልሉ መንግሥት ምንም ዓይነት ትኩረት እየሰጠው አይደለም ያሉ ሲሆን፣ በቀጠናው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በዘላቂነት መፍታት እንዳልቻለም ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የመከላከያ ኃይል በቦታው ያለ ቢሆንም፣ በአካባቢው በሚገኙ በተለያዩ ጫካዎች የኦነግ ሸኔ ቡድን መኖሩን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሉ በማይደርስባቸው ቦታዎች በመንቀሳቀስ ጥቃት ከመፈጸም እንዳልተቆጠበም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በአካባቢው የክልሉ መንግሥት ልዩ ኃይል፣ የመከላከያ ኃይል መግባቱን ተከትሎ የጸጥታ ሁኔታው ቀድሞ ከነበረው አንፃር የመረጋጋት ለውጦች ቢኖሩም፣ አስተማማኝ ነው ለማለት እንደሚቸገሩ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ 3 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ እና በኦነግ ሸኔ ቡድን የሰዎች ንብረት እየተዘረፈ ነው።

አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ያደረገች ቢሆንም፣ ምላሽ አላገኘችም። በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አልፈለጉም።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ መንግሥት በአካባቢው መከላከያ እንዳሰማራና በታጣቂ ቡድኑ ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል። በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ማንነትን መሠረት ያደረገውን ጥቃት ዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ ያወገዘው ሲሆን፣ መንግሥት በየጊዜው በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ማስቆም ባለመቻሉ ቀላል የማይባል ትችት እያስተናገደ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here