መነሻ ገጽአንደበትየብሔር አደረጃጀት በሕግና በስርዓት እውቅና ተሰጥቶት፣ የበለጠ እያደገ መጥቶ ነው ዛሬ ላለንበት...

የብሔር አደረጃጀት በሕግና በስርዓት እውቅና ተሰጥቶት፣ የበለጠ እያደገ መጥቶ ነው ዛሬ ላለንበት ቀውስ የዳረገን

ያየህ አስማረ
የእናት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

በ2012 ነበር፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅናን አግኝቶ እንደ አገር ዐቀፍ ፓርቲ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ መንቀሳቀስ የጀመረው፣ እናት ፓርቲ። በኋላም በተካሄደው የ2013 አገር ዐቀፍ ምርጫ ላይ በርካታ እጩዎችን ካቀረቡ ፓርቲዎች መካከል ተጠቃሽ ሆኗል። ከምርጫው በኋላም በየጊዜው ወቅታዊ የሆኑ መግለጫዎችን በማውጣት ድምጹን ከማሰማት ባሻገር የፓርቲውንም አቋም እያሳየ ቆይቷል።

ፓርቲው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግሮች በሦስት ጉዳዮች ላይ ተተብትበው የተያዙ ናቸው ብሎ ያምናል። በዚህም ፖለቲካው፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ይጠቅሳል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የማኅበራዊ ሕይወት ትስስርም በተለያየ ምክንያት አደጋ ላይ እንደወደቀ በጽኑ ያምናል። እነዚህ ችግሮች ፓርቲው እንዲመሠረት ምክንያት ሆነው ተገኝተዋል።

በዚህ መሠረት ፓርቲው በቅርቡ ‹መንግሥት ዜጎችን መጠበቅ ቢያቅተው ከማዘናጋት ይቆጠብ› በሚል ይፋ ባደረገው መግለጫ፣ ጎሳ ተኮር ግድያና ፍጅት በኢትዮጵያ መታየትና መሰማት ከጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ባለፉት አራት ዓመታት የሆነውን ያህል ግን በሰላማዊ ዜጎች ላይ የበዛ ግፍ አልደረሰም ሲል ድምጹን አሰምቷል። ይህንን አሁን ላይ የብዙዎችን ትኩረት ያገኘውን የንጹሐን ዜጎች ጭፍጨፋን ጨምሮ ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ በሚመለከት፣ የእናት ፓርቲን እንቅስቃሴና ምልከታንም በማንሳት፣ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ከእናት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ያየህ አስማረ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

የዛሬ ሦስት እና አራት ዓመት፣ በወቅቱ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ሁኔታ አንጻር ወደፊቱን ስትገምቱ አሁን ያለችበት ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ትገባለች የሚል ግምት ነበራችሁ?
የዚህን ያህል መጠን ይሆናል ብለን ባንገምትም፣ የብሔር ፖለቲካ እስከቀጠለ ድረስ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ እንደምትወድቅ ማንኛውም ሰው፣ በተለይ በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ ያለው ሰው የሚረዳው ሀቅ ነው።

ግን አሁን እያየነው ባለው እንደዚህ በከፋ መጠን ሰዎች እጅግ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሰዎች እንደ አውሬ የሚገደሉበት ሁኔታ ይመጣል የሚል ግምት ግን አልነበረንም። የከረረ ፖለቲካ ሊኖር እንደሚችል፣ ከዚህ ከኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይልቅ የብሔር ፖለቲካው አይሎ ሊወጣ የሚችልበት እድል ሊኖር እንደሚችል፣ ነገር ግን የለውጥ ኃይሉ በደንብ መቆጣጠር (ማኔጅ ማድረግ) ከቻለ፣ እየረገቡ ወደ አገራዊ አንድነት የመምጣት እድል ይኖረዋል የሚል ግምት ነበረን። አሁን ባለው፣ በዚህ ልክና በዚህ መጠን ይሆናል የሚል ግምት ግን በፍጹም አልነበረንም።

ኢትዮጵያን እዚህ ያደረሳት የመጣችበት መንገድ ምን ዓይነት ነው ትላላችሁ? ማንንስ ነው ተጠያቂ አድርገን መውቀስ ያለብን?
ይህን ካነሳን፣ ረጅም ጊዜ ወደኋላ ሄዶ ለሀምሳ ዓመት የተደረገውን የፖለቲካ ትግል ማየቱ አስፈላጊ ይመስለኛል። ከንጉሡ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ የነበረው ትግል እየቆየ ሄዶ በደርግ ጊዜ የብሔር ማንነት ወይም የብሔር ትግል የሚል ሥም ተሰጥቶት (በጊዜው የብሔር ጭቆና ባይኖርም) ትግሉ ቀጠለ።

መጨረሻ ላይ ደግሞ ሕወሓት ኢሕአዴግ ከመጣ በኋላ የብሔር አደረጃጀት በሕግና በስርዓት እውቅና ተሰጥቶት፣ የበለጠ እያደገ መጥቶ ነው ለዚህ ዛሬ ላለንበት ቀውስ የዳረገን። እና ታሪካዊ ዳራው እንዳልኩት ወደኋላ ነው።

ግን ትልቁ ችግር የተፈጠረው ሕወሓት ሥልጣን ከያዘ በኋላ በሕግ እና በስርዓት፣ የብሔር አደረጃጀቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ጨምሮ በክልልና በሕገመንግሥትን ከጸደቀ በኋላ ነው። ከዛ በኋላ ነው እንደዚህ ዓይነት ውስብስብ ችግር ውስጥ የገባነው።

በቅርቡ የነበረውን የወለጋን ክስተት እናውሳ። እንዲህ ያሉ አሰቃቂና ዘግናኝ የንጹሐን ግድያዎች ተገቢውን ትኩረት አግኝተዋል ብለው ያምናሉ?
በፍጹም። ብዙ ጊዜ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ከተፈጸሙ በኋላ ሁሉም ሙሾ ማውረድ ነው እንጂ ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታበት ነገር ላይ ቁርጠኛ የሆነ አካል አታይም፣ መንግሥትን ጨምሮ። እንደውም አሁን አብዛኛው ፓርቲዎችም ሆነ መገናኛ ብዙኀን፣ መንግሥትን ጨምሮ እውቅና የሰጡት ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን ትኩረት ስለሰጡት ነው።

እንጂ ከዚህ ቀደም በዚህ መጠን ባይሆንም በርካታ ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል። የአሁን ለየት የሚያደርገው ቁጠሩ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ነው። እንጂ ዘግናኝ ግድያዎች ከዚህ በፊትም ነበሩ፤ ወለጋ ላይ በተደጋጋሚ ዐይተናል፣ ቤኒሻንጉልም ነበረ። እና እንዳልኩት የአሁኑ ለየት የሚያደርገው ቁጥሩ መጨመሩ እና ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት ሰጥተው መዘገባቸው ነው።

ትልቁ ነገር ግን፣ ይህን እውነት ማጋለጥ እንዳለ ሆኖ፣ በተለያየ ቦታ የሚኖሩ ኢትዮጰያውያን በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት እንዳይደርስባቸውና በሕይወት የመኖር መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ዘላቂ መፍትሄ ላይ ማተኮር ነው ቁልፉ ነጥብ። በተፈጠረ ጊዜ መጮኹ ነገም ሊቀጥል የሚገባና ለተገፉ ሰዎች ድምጽ መሆን አስፈላጊ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ትልቁ ነገር በዘላቂነት የሚፈታበት ነገር ላይ ማተኮር ነው።

ይህን ዘለቂ መፍትሄ እንዴት ማምጣት ይቻላል? ከመንግሥትስ ምን ዓይነት እርምጃ ይጠበቃል?
እኛ ከዚህ በፊትም ደጋግመን ተናግረናል። ይህ የሚፈታው የስርዓትና መዋቅራዊ ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው። ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ ለአገሪቱ ነቀርሳ የሆኑ ነገሮች ሁሉ መቀየር አለባቸው። እውቅና ሰጥቶ እርስ በእርስ እንድንበላላ የሚያደርገን ሕግ አለ። ያ ሕግ ደግሞ ሕገመንግሥቱ ራሱ ነው። ከሚገባው በላይ እየተለጠጠ፣ ለብሔር ማንነት እውቅና ሰጥቶ ዜጎች በብሔር እንዲደራጁ አድርጎ፣ ለመሬት ሳይቀር ብሔር ሰጥቶ እንደዚህ እርስ በእርስ እንድንበላላ ያደረገን እሱ ነው።

ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ስርዓት ወለድ የሆኑ ነገሮች መቀየር መቻል አለባቸው። ከዛ ውጪ በጊዜያዊነት የዜጎች በሕይወት የመኖር ዋስትና ላይ ድርድር አያስፈልገውም። ይህ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ስለሆነ፣ ድርጊቶች በጣም እየወጡና ዓለም ዐቀፍ እውቅና እያገኙ ሲመጡ ብቻ ወጥቶ ‹እርምጃ እንወስዳለን› የሚል ፕሮፖጋንዳ ከመናገር ባለፈ፣ ተጨባጭ መሬት ላይ ሊወርድ የሚችል ሥራ ሠርቶ ለሕዝብ ማሳየትን ይፈልጋል።

እንዲህ ያለው ክስተት አገራዊ ምክክር ላይ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚሉ አሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
በእኔ ዕይታ፣ ይህ ከአገራዊ ምክክሩ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ምክንያቱም እየሞቱ ያሉ ሰዎች የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች አይደሉም። አሁን የሚጣሉት አካላት፣ አንድ አማጺ ነኝ የሚል ቡድን እና አንድ ደግሞ መንግሥት ነው። ኹለቱ የሚጣሉበት የራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል። ከተጣሉ ደግሞ ሁለቱ ናቸው መነጋገር ያለባቸው።

አሁን ሦስተኛው፣ ምንም ጉዳዩ ውስጥ የሌለበት ሰው ነው እየተጠቃ ወይ እየተገደለ ያለው። እንዲህ ያለው ነገር ከድርድሩ ጋር፣ ከብሔራዊ ምክክሩ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። እርግጥ ነው ብሔራዊ ምክክሩ ብዙ ችግሮችን ሊፈታ ይችላል፤ እኛ በአግባቡ ከተጠቀምንበት እና ልዩነታችንን በመነጋገር እንፈታለን ብለን የምናምን ከሆነ ማለት ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ግን ይህ ነገር ሁሉ እያለ፣ በአሸባሪነት የተፈረጀው ድርጅት፣ አሁንም ምንም የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው እናቶችን፣ ሕጻናትና አርሶ የሚበላውን አርሶ አደር ገበሬውን ነው እየጨፈጨፈ ያለው። እና ከምክክሩ ጋር ይህን ያህል የጎላ ነገር አለው ብዬ አላስብም።

ግን እነዚህ ሰዎች ልብ የሚገዙ ከሆነ፣ ነገ ከነገ ወዲያ ይህ ነገር እያንኳኳ እነሱም እንቆረቆርልሃለን ለሚሉት ማኅበረሰብ ራሱ ከባድ እዳ እየጣሉበት ነው። ቆም ብለው ማሰብ መቻል አለባቸው። በተለይ ደግሞ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ድርጅት አንዴ አሸባሪ ነው ተብሎ ተፈርጇል፣ ድርጊቱም እሱን ነው የሚያሳየው። ግን መንግሥት ራሱ ኃላፊነት እንደተጣለበት ትልቅ ባለድርሻ አካል፣ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

እንደ ተፎካካሪ ወይም ተቃዋሚ ፓርቲ እናንተስ ምን እየሠራችሁ ነው?
በእኛ በኩል እንዳልኩት፣ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ፣ የመጀመሪያው ሥራችን ድርጊቱ በሚገባው ልክ እንዲገለጽና የሚመለከተው አካል እንዲያውቀው፣ እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ድርጊት ለሚፈጸምባቸው ወገኖች ግልጽ ማድረግ አንዱ ሥራችን ነው።

ከዛ ባለፈ ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብም ጉዳዩን ለማሳወቅ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ያለነው። ከዛ ውጪ መንግሥትም ቢሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ብዙ ጊዜ መግለጫ ስንሰጥ፣ የዜጎች ደኅንነት ጉዳይ የመጀመሪያው ኃላፊነቱ እንደሆነም ጥሪ ስናቀርብ ቆይተናል።

አሁንም ቢሆን ጆሮ ካላቸውና የሚሰሙ ከሆነ፣ ሌላውን የልማት ሥራ ትተው፣ የመጀመሪያና ቀዳሚ ሥራ የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ ነው። ልማት የሚሠራው ለሰዎች ነው። ሰዎች ከሌሉ፣ የሚጨፈጨፉ ከሆነ፣ ማን ነው በልማቱ የሚጠቀመው? ይህ በጣም የሚጋጭ ነገር ነው። ለሰው የምትቆረቆሪ ከሆነ መጀመሪያ የሰዎችን ደኅንነት አስጠብቀሽ ነው ከዛ በኋላ በተረፈው ነገር የልማት ሥራ የምትሠሪው።

መንግሥት አሁን ተራ በሆኑ ጉዳዮች ተጠምዶ ነው የምታይው። ሰዎች ያልቃሉ፣ በዚህ በኩል ደግሞ አረንጓዴ አሻራ እያሉ ዛፍ ይተክላሉ። ከዛ የሚቀድመው የሰው ልጅ ነው። ዛፍን የምትተክይው፣ ለአረንጓዴ አሻራም ቢባል ወይም አየር ንብረትን መጠበቅ ወይም ሌላም ቢባል፣ ዞሮ ዞሮ አካባቢን ለሰው ልጆች ምቹ ማድረግ ነው የመጨረሻ ግቡ። ከዛ ባለፈ ግን የሰዎች ሕይወት ቅድሚያ የሚሰጠው የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ማሳሰብ ሁልጊዜ የምናደርገው ነው።

ከዛ ውጪ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ራሱን የመከላከል ተፈጥሮአዊ መብት ስላለው፣ ራሱን መከላከል መቻል አለበት እያልን ጥሪ ስናደርግ ነው የቆየነው፤ አሁንም እሱን ነው የምናስተላልፈው።

ሕግ ማስከበር በሚል መንግሥት እየወሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች ውስጥ እስር እና አፈና ይገኝበታል። በእናንተም ፓርቲ የታሰሩ አባላት እንዳሉ ይታወቃል። ይህ ድርጊት የፖለቲካ እንቅስቃሴው ላይ ምን ያህል ተጽእኖ ያሳድራል?
ከዚህ በፊት የተገባው ቃል አጣርተን ነው የምናስረው የሚል ነበር። አሁን ግን በተቃራኒው ከዚህ በፊት ሲታገሉለት የነበረው ጥያቄው ተመልሷል። ሰዎች ሊጠረጠሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ከተያዙ በኋላ ረጅም ጊዜ ቆይተው፣ አንዳንዶችም አድራሻቸው ሳይታወቅ፣ ቤተሰባቸውም ሲጨነቅ ቆይቶ በነጻ ይለቀቃሉ። ማን እንዳሰራቸው ሳይታወቅም የሚለቀቁ ሰዎች አሉ። አንዳንዱ ደግሞ ታስሮ ነው ማጣራት እየተካሄደ ያለው።
እንዲህ ያለ ነገር ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉ አደረጃጀቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሰዉን እንዲህ እየገፋሽው ስትሄጂ፣ ሌላ አማራጭ እንዲያይ ልታስገድጂው ትችያለሽ።

- ይከተሉን -Social Media

እና እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች (የእስር) ሊኖሩ አይገባም። ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው። ልክ ነው! በወንጀል የሚጠረጠር ሰው ካለ ሊጠረጠር ይችላል። ግን ሕግን በተከተለ መልኩ ሕጋዊ ምርመራ ሊደረግበት ይችላል። ሰላማዊ ሲሆን ደግሞ ሊለቀቅ ይችላል።

ግን በየትኛውም መንገድ አንድን ሰው አፍነሽ ወስደሽ፣ ረጅም ጊዜም ቤተሰቦቹ ያለበትን ሳያውቁ ማስቀመጥና ከዛም አልፎ ሐሳባቸውን በነጻነት በመግለጽ የሚታወቁ ሰዎችን ለማሸማቀቅ የሚደረግ ጥረት ግን፤ ትግሉን እያሰፋው፣ የተለየ አማራጭ እንድታይ ያደርጋል እንጂ፣ ሰዉ ዝም ብሎ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ነው ብዬ አላምንም። ትግል ያለ መስዋዕትነት አይገኝምና።

እና መንግሥት እንደዛ ማድረጉን ቢተወውና፣ ከዚህ ቀደም ቃል እንደገባው ትክክለኛውን መንገድ መከተል ለሁላችንም ይጠቅማል።

አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት አስጨናቂ ሁኔታ አንጻር ለወደፊት የምታደርጉት ተስፋ ምንድን ነው?
እንደሚታወቀው አገራችን ላይ አስቀድሞም እንዳልኩት ለረጅም ዓመታት የተተከለ መርዝ ስለሆነ በቀላል የሚነቀል አይደለም። ያንን መርዝ ለመንቀል ደግሞ እኛ ኢትዮጵያዊያን መተባበር መቻል አለብን። አሁን ላይ ተመርጠው የሚገደሉ ሰዎች አንድ ማኅበረሰብ በተለይ የአማራ ማኅበረሰብ ማንነት ያላቸው መሆኑ ግለጽ ነው፤ መዋቅራዊ ጥቃት ነው እየደረሰባቸው ያለው።

ይህ በብሔር የተደራጀ አደረጃጀት ነገ ሄዶ ሄዶ ጥያቄ ሲያጣ ወይም ጥያቄው ቢመለስ እንኳ፣ ነገ የግድ ሌላ አማራጭ ይፈልጋሉ። በዛም ከራሳቸው ማኅበረሰብ ጋር ጭምር ሊጋጩ ይችላሉ። ምክንያቱም በብሔር ላይ የተመሠረተ አደረጃጀት ስግብግብ ነው። መጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ብሎ የሚረካ ስላልሆነ፣ ተመልሶ ራሱ እቆረቆርላቸዋለሁ ለሚለው ማኅበረሰብ አደጋ ስለሚሆን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊታጋለው ይገባል።

ትግሉ መራራ ሊሆን ይችላል እንጂ ያንን የምንፈልገው ለውጥ የሚመጣበት ጊዜ የግድ ነው፤ ይኖራል። ግን ተጨማሪ ሰዎችም አላስፈላጊ ዋጋና መስዋዕትነት እንዳይከፍሉ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ነገር በጥንቃቄ እያየ ችግር እየደረሰባቸው ላለ ወገኖች ድምጽ ሊሆናቸው ይገባል።

ከዚህ ውጪ፤ እኛ ከሰሞኑ ባወጣነው መግለጫም እንዳየሽው፣ አሁንም ቢሆን መንግሥት ከማዘናጋት መቆጠብ አለበት። ቢቻል ቀዳሚ የሆነውን የዜጎችን ደኅንነት ይጠብቅ። እሱም ማድረግ ካልቻለ ግን፣ ‹አከርካሪውን ሰብረናል› እያለ ማኅበረሰቡን እያዘናጋ ለከፍተኛ ውድመት ሊዳርግ አይገባም የሚል መልዕክት አስተላልፈናል። ቢያንስ መከላከል ባይችሉ ማዘናጋታቸውን ሊተዉ ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች