ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የመከላከያ ሰራዊትን ሚስጥር በማውጣትና ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ወንጀል ክስ ተመሰረተበት

0
1118

ጋዜጠኛው የቀረበበት ክስ ላይ የዋስትና ብይን ለመስጠትም ለፊታችን አርብ ተቀጥሯል

ዕረቡ ሰኔ 22 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሳምንታዊው “ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የመከላከያ ሰራዊትን ሚስጥር በማውጣትና ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት ሲሆን፤ የቀረበበት ክስ ላይ የዋስትና ብይን ለመስጠት ለፊታችን አርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 ተቀጥሯል።

ክሱ በትናንትናው ዕለት የተከፈተ ሲሆን፤ በዛሬው ቀጠሮ ግን ክሱ ለተከሳሽ ደርሶ በችሎት ተነቧል።

ክሱን በንባብ ያሰማው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረሽብርና የህግመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ነው።

በዚህም ክስ ዓቃቢህግ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 44(1) (2) እና 336(1) በመተላለፍ በአንደኛው ክስ የቀረበ ሲሆን በ2ኛ ክስ ደግሞ አንቀጽ 337(1) ስር የተደነገገውን ድንጋጌ እና በ3ኛ ክስ ደግሞ የወንጀል ህግ አንቀጽ 257 በመተላለፍ ሲል ዓቃቢህግ ተደራራቢ ክስ አቅርቧል።

በክሱ ከ2011 ጀምሮ በሚሰራበት በፍትህ መጽሔት በተለያዩ የህትመት ቀናት የመከላከያ ሰራዊትን ሚስጥራዊ ተግባራትን በማውጣትና እና ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት የሚል በክሱ ተካቷል።

ክሱ በችሎት ከተነበበ በኋላ የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ጋዜጠኛ ተመስገን በወ/መ/ስ/ህ 67/ሀ እና በህገመንግስቱ አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 6 መሰረት የዋስትና መብት መጠበቅ እንዳለበት ድንጋጌውን አብራርቷል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ሀሳብን ከመግለጽና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ ከመጻፍ ባለፈ ምንም ወንጀል ፈጽሞ እንደማያውቅ ገልጿል።

ከዚህ በፊት በነበረ ሥርዓት ታስሮ ዋስትና ተፈቅዶለት ለሦስት ዓመት ህግን አክብሮ እየተመላለሰ ፍርድ ቤት ይቀርብ እንደነበር ጠበቃው ጠቅሷል። ይህም ህግን አክብሮ እንደሚመጣ ማሳያ ነው ሲል አብራርቷል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ከአገር እንዲወጣ በተለያዩ አካላትና መንግስታት ሳይቀር ግፊት ተደርጎ እንደነበር የጠቀሰው ጠበቃ ሄኖክ በጋዜጠኛ ተመስገን በኩል ግን ሥራዬና ሞቴ በአገሬ ላይ ነው ብሎ ከአገር ሳይወጣ መቀመጡን ገልጿል።

ቋሚ አድራሻ ያለው እና ህግን የሚያከብር መሆኑን ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን እንዲፈቅድለት ጠበቃው ጠይቋል።

ከሳሽ ዓቃቢህግ በበኩሉ በተደራራቢ ክስ በመከሰሱና በልዩ ሁኔታ ዋስትና ሊሚያስከለክል እንደሚችል የወንጀለኛ መቅጪያ ሥነ ሥርዓት ህግ ድንጋጌ መኖሩን በመግለጽ እንዲሁም የሰበር ውሳኔ ድንጋጌዎች ዋስትናን ሊያስከለክል እንደሚችል በማብራራት ተከራክሯል።

በተጨማሪም ከሳሽ ዓቃቢህግ በአንደኛና በሦስተኛ ክስ ከብዶ ከታየ እስከ 10 ዓመት በሚያደርስ እስራት ያስቀጣል ሲል የገለጸ ሲሆን፤ በኹለተኛ ክስ ደግሞ ከብዶ ከታየ እስከ እድሜ ልክ በሚያደርስ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ እንደሚችል ገልጾ የዋስትና ጥያቄውን መቃወሙን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ መርምሮ ዋስትናው ብይን ለመስጠት ለፊታችን አርብ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱም ታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here