ኹለተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት በይፋ ተከፈተ

0
928

ሐሙስ ሰኔ 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) “ንቁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ለዲሞክራሲና ለልማት” በሚል መሪ ቃል ኹለተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት በዛሬው ዕለት በሂልተን ሆቴል በይፋ ተከፍቷል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን መስሪያ ቤት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ባዘጋጁት በዚህ ኹነት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ፤ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፤ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ኤርገዶ ተስፋዬን እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል።

የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱም በአገራችን ባለፉት ጊዜያት በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮአዊ አደጋዎች ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያዊያን የህሊና ፀሎት በማድረግ ተጀምሯል።

በመድረኩ የተገኙት ሚኒስትሮችም፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት መከበሩ፤ ማህበረሰቡ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያለውን አመለካከት የሚያቀና መሆኑን በመግለፅ፤ ድርጅቶቹም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸውን የእርስ በእርስ ትስስርም የሚጠናክር እንደሚሆን ተናግረዋል።

ያለፉት ዓመታት በአገሪቱ ተደራቢ ችግሮች በመፈራረቃቸው የምኞታቸውንና የሚጠበቅባቸውን ያህል ለመስራት እንዳላስቻላቸው የገለፁት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን መስሪያ ቤት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሥራ ሀላፊዎች፤ እነዚህ ችግሮች ሙሉ ሙሉ እስኪቀረፉና ሰላማዊ በሆነ አካሄድ ምላሽ እንዲሰጣቸው አጥብቀን መታገላችንን አናቆምም ብለዋል።

በመድረኩም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ያጠናከሩ የመመስረት ሂደቱ ላይ አስተዋፅኦ ላበረከቱና ኹነቱን ላዘጋጁ ግለሰቦች እና ተቆማት የእውቅና ሰርተክፌትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከ100 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚሳተፋበትና እሰከ ቅዳሜ በሚዘልቀው ሥነ-ሥርዓትም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚያስተዋውቁ የፓናል ውይይቶች፣ ኤግዚቢሽን፣ የመገናኛ ብዙሀን መርሃ ግብሮች እና ሌሎች የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱም የተያዘው መርሃ ግብር ያመለክታል።

         

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here