“ለታክሲዎችና ሃይገሮች ነዳጅ ቅድሚያ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ”:- የኢትጵያ ነዳጅ ማደያዎች ማህበር

0
1459

አርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ለታክሲዎችና ሃይገሮች ነዳጅ ቅድሚያ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን የኢትጵያ ነዳጅ ማደያዎች ማህበር አስታወቀ።

በከፍታኛ ኹኔታ በቀጠለው የነዳጅ ሰልፍ ምክንያት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የህዝብ ማመላለሻ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መስተጓጉሎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም ይህንን ችግር ከግምት ዉስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ነዳጅ ማደያዎች ማህበር የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች (ታክሲዎችና ሃይገሮች) ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ነዳጅ እንዲያገኙ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ማህበሩ እየተስተዋለ ያለው የህዝቡ መጉላላት አሳስቦኛል ያለ ሲሆን፤ ያለውን ረጃጅም የትራንስፖርት ሰልፎች ፋታ ለመስጠት እና የህዝብ ትራንስፖርት ችግሩን ለማቃለል ይህንን መላ መዘየዱን ተናግሯል፡፡

በየማደያዎቻችን አሁንም የተሸከርካሪ ሰልፎች እንደቀጠሉ ናቸው ያሉን የማህበሩ ቦርድ አባል ደሳለኝ አበባየሁ፤ የህዝብን እንግልት ለመቀነስ በማሰብ ማህበሩ ይህንን ለመተግበር መወሰኑን ለኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ተናግረዋል፡፡

ደሳለኝ ይህ እቅድ የህዝቡን ችግር የሚፈታ በመሆኑም የመንግስትን እና የፖሊስን ድጋፍ ካገገኘን በየማደያዎቹ አሰራሩ ይተገበራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ ማደያዎች ማህበር አሁን ካለው የነዳጅ ችግር ጋር በተያያዘ ከሌሎች ዘርፎች በበለጠ ለህብረተሰቡ ትኩረት መሰጠት እንደሚገባው በማመን ያቀረበዉ ምክረሃሳብ መሆኑን ገልጿል፡፡

አሽከርካሪዎች እና የመንግስት አካላት ይህንኑ እንዲረዱም ጠይቋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here