በደቡብ ክልል ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሲሊካ የተሰኘ ማዕድን ከአሽዋ በማውጣት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ማውጫን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።
በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ የሚገነባው ይህ የማዕድን ማውጫ 200 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና ለተለያዩ የፋብሪካ ግብዓቶች የሚውል የ“ሲሊካ” ማዕድን ምርት ከአሸዋ ውስጥ በማጣራት እንደሚያመርት የኩባንያው ባለቤት ዳዊት ሽብሩ ተናግረዋል።
ኘሮጀክቱ በአንድ ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ምርቱን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ያቀርባል ተብሏል። ፕሮጀክቱን ለመጀመር በተለያዩ የሥነ ምድር ባለሙያዎች ጥናት ሲደረግ እንደቆየም ተመላክቷል።
በሥነ ስርዓቱ የተገኙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ፥ ‹‹የብዙ ፀጋዎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ጠላቶቻችን በሚሰጡን አጀንዳዎች ፀጋዎቿን ሳትጠቀምበት ቆይታለች›› ብለዋል። በደቡብ ክልል በዓለም እጅግ ውድ የተባሉ የማዕድን ዓይነቶች ያሉ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ ማቅረባቸውንም ፋና ብሮድካስት ዘግቧል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ መንግሥት ለማዕድን ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አገር የሚፈለገውን የ”ሲሊካ” ምርት ከማዕድን ዘርፉ ባለፈ ለግብርና፣ ለግንባታ፣ ለፋብሪካ የሚውል በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋልም ተብሏል።
“ሲሊካ ሳንድ” ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች የሚያገለግል ሲሆን፣ በተለይም ለብርጭቆ እና ለጠርሙስ፣ ለፅዳት ዕቃዎች፣ ለውሃ ማጣሪያ እና ማከሚያ፣ ለቀለም ፋብሪካ፣ ለብረታ ብረት እና አልሙኒየም ሥራ፣ ለዘይት እና ጋዝ አምራቾች እንዲሁም ለተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እንደ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014


