“ሜቴክ የስኬት ታሪክ አለው።”

0
964

ብርጋዴር ጀነራል አሕመድ ሐምዛ የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክትር ናቸው።
በአሁኑ አጠራሩ ደቡብ ወሎ ዞን በቀድሞ አጠራሩ ወሎ ክፍለ ሀገር፣ ወረኢሉ አውራጃ፣ ለጌዳ ወረዳ የተወለዱት አሕመድ፥ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ወይን አምባ ኹለተኛ ደረጃን ደግሞ ወረኢሉ በሚገኘው አባውባየው ትምህርት ቤት ተከታትለው አጠናቀዋል።
አሕመድ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ባጠናቀቁበት በ1982 መጨረሻ በቀጥታ ወደ ትግል በመግባት በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ወደ ኋላም ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የተባለውን ድርጅት በመቀላቀል ከላብ አደር ክፍለ ጦር አባልነት እስከ ብርጌድ አዛዥነት አገልግለዋል።

በ1985 የጸረ ሽምግ ውጊያ ሥልጠና ወስደው ጎንደር ተመድበዋል፤ በኋለ አየር ኀይልን በመቀላቀል በጠቅላላው ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል። በአየር ኀይል ውስጥ በራዳር ሜካኒክ በዲፕሎማ እንዲሁም በኤልክትሪካል ኢንጅነሪንግ የኤሌክትሮኒክስ ዎርፌር ሥልጠናም ተከታትለዋል። ለአጭር ጊዜም የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ክፍል ሆነው አገልግለዋል።

ወደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (‘ኢንሳ’) በመዘዋወር በአጠቃለይ ለዐሥር ዓመታት ያገለገሉት አሕመድ፥ በኤጀንሲው የኤሌክትሮኒክስ ዎርፌር ክፍል ኀላፊ፣ የኢንፎርሜሽን አሹራንስ ምክትል ዳይሬክተር፣ የፋይናንስና አስተዳደር ኀላፊ እንዲሁም የአቅርቦት ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሠርተዋል።

ሚያዚያ 16/2010 በምክትል ዳይሬክትርነት ሜቴክን የተቀላቀሉት አሕመድ፥ ኅዳር 4/2011 በዋና ዳይሬክትርነት ተሾመው እስካሁን በዚሁ ኀላፊነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ሜቴክን ግዙፍ ኮርፖሬት ኩባንያ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሥሩ ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎችን፣ 12 በማስፋፊያ ላይ ያሉትን ሳይጨምር 56 በሥራ ላይ ያሉ ፋብሪካዎችን እንዲሁም 12 ሺሕ 777 ሠራተኞችን እያስተዳደረ ይገኛል።

ስድስት ልጆች ካሏቸው ወላጆች የተገኙት አሕመድ ሐምዛ፥ እሳቸውም የስድስት ልጆች አባት ናቸው።
የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከአሕመድ ሐምዛ ጋር በወቅታዊ የሜቴክ ተቋማዊ ቁመና፣ ሊሠሯቸው ስላሰቧቸው እንዲሁም ተያያዥ ስለሆኑ ጉዳዮች ሰፊ ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ በአገራችን ለሥም ትልቅ ግምት ይሰጣልና፤ አሁን ሜቴክ ሲጠራ አሉታዊ የሆኑ መልኮቹ ናቸው በሰው አእምሮ የሚፈጠሩትና እዚህ ላይ ለውጥ ለማምጣት ምን እያደረጋችሁ ነው?
ጀነራል አሕመድ፡ እንደምናምነው መልካም ሥም ጠቃሚ ነው፤ በግብር ካልተመራ ግን ትንሽ ይሔድና ተመልሶ ይፈርሳል። ግብን ማስተካከሉን ቅድሚያ ሰጥተነዋል። ግብር ምንድን ነው ካልን፤ ይኼ ተቋም የፖሊሲ መሣሪያ ነው፤ የመንግሥት የልማት ተቋማት ሁሉ የመንግሥትን ፖሊሲ ማስፈጸም ነው ያለባቸው። ይኼንን ሲሠሩ ደግሞ የሕዝብ ተቋም መሆናቸውን አውቀው ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለባቸው። ይኼን ግብር ነው አሁን እየሠራን ነው ያለነው።

የመንግሥት ሚድያም ይምጣ ማንም ሚድያ የሚያቀርበው ለሕዝብ ስለሆነ፤ ያለንበትን እውነት ለሕዝብ እየተናገርን ነው። አሉ ያልናቸውን ችግሮችም እያስተካከልንም፤ እንደገና መልሰን እያቀረብን ነው። የመጀመሪያው ግብሩን እያስተካከልን በስርዓት ውስጥ እንዲገባ እያደረግን ያለነው።
በነገራችን ላይ ስርዓት የሥልጣኔ ምልክት ነው። ከሠለጠኑ አገራት አንድም በስርዓት የማይመራ የለም። እነሱ ደግሞ ሀብታም ናቸው። አፍሪካውያን ደግሞ ስርዓት ለሚባል ነገር ትኩረት አይሰጡም፤ እነርሱ ደግሞ አልሠለጠኑም። ስለዚህ ስርዓት ማክበር የሥልጣኔ ምልክት እንጂ ሌላ ነገር አይደለምና ወደ ስርዓት መግባት ነው ያለብን።

ሜቴክ ምን እንደሚሠራ፣ እንዴት እንደሚሠራ፣ መቼ እንደሚሠራ፣ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያወጣና ገንዘብ እንዴት እንዳወጣም ኅብረተሰቡ ማወቅ አለበት፤ ወደዛ እየሔድን ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት ኦዲት ተደርጎ አያውቅም፤ አሁን የአምስት ዓመት ኦዲት ጨርሰናል።
2011 እኛ ነን ያለንበት፤ የቀደመው የሜቴክ ሰው እዚህ ላይ ምንም ጥያቄ የለበትም፤ ስህተት ካለም፣ ጥሩም ሠርተን ከነበረ እኛ ነን የምንጠየቀው። እርሱን ደግሞ እስከ የካቲት በደንብ አድርገን ጨርሰን 2012ን የተጣራ የኦዲት ሪፖርት ያለው፣ ሕዝብ የሚያውቀው፣ አጥፍተሃል ካለ የሚጠይቀው ተቋም እንዲሆን አድርገን ሠርተናል። ያለፈውን ዓመት ተቋም በማስተካከል ላይ ነበር ትኩረታችን።

ኹለተኛው ግን ሥሙ ስለጠፋ መቀየር አለብን። ስንቀይረው ደግሞ የአገሪቱ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ የሚገልጽ አድርገን ነው። ግን ሲቀየር የሚሟሉ ነገሮች አሉ። በስሜት ቢሆን ኖሮ 2010 እንደመጣን አቅርበን ነበር። አልሆነም፤ ለምን መሟላት ያለበት ነገር አለ። አንደኛ እዳው በትክክል መለየት አለበት። ይኼ ተቋም እዳውን አያውቅም፤ ሰነድ የለውም። የመንግሥት ተቋም ነው ለማለት በሚቸግር ደረጃ ሰነድ የለውም።

ዘንድሮ እዳችንን ጨርሰናል፤ ተሰብሳቢንም አውቀናል። አሁን የቀረን ሀብትና እዳ ማወቅ ሲሆን ጨረታ አውጥተን ሰሞኑን ከአሸናፊ ድርጅት ጋር እንፈራረማለን፤ በአርባ አምስት ቀን ውስጥ እንጨርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በእኛ በኩል ኅዳር ላይ ለመጨረስ ነው ያቀድነው። ሌላው በሙሉ ያለቀ ስለሆነ ታኅሣሥ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሥም ማስቀየሩንና ተቋሙን እንደገና የማቋቋሙን ነገር ይገባል። በእቅዳችን መሠረት ጥር ላይ አዲስ ተቋም ይኖረናል ማለት ነው።

መዋቅሩም እንደ አዲስ ተሠርቶ ማለት ነው?
ሳይሆን ስለስሙ ነው ያወራሁት፤ ሥሙ አዲስ ይሆናል። ተቋማዊ መዋቅሩን በተመለከተ አሁንም እየተሠራ ነው። ኅዳር ላይ ሁሉም ነገር ያልቅልናል። የተቋም መዋቅር። የፋይናንስ መዋቅር ማሻሻያም ይደረጋል። ይህም ለመንግሥት ቀርቧል። እርሱን ሲወስኑበት ካፒታል የሚሆነው ካፒታል ይሆናል፤ መሰረዝ ያለበትም አለ። ሁሉም የቀረቡት ግን በምክንያት ነው የሚሆነው።

ለምሳሌ መሰረዝ አለበት ብለን ያቀረብነው፤ አንድ ገንዘብ የሚሰዘረው ባለቤት ኖሮት ነው እንጂ በወረቀት ላይ ዝም ብሎ መሰረዝ አይደለም። አንደኛ ሰዎቹ አጥፍታችኋል ተብለው ተጠይቀዋል። ይኸው ሰነድ ማስረጃ ሆኖ ቀርቦባቸዋል።

ኹለተኛ ይኼ ሀብት ተቆጣጣሪ አልነበረውም፤ መንግሥትም ይህን ሀብት ሲሰጥ አምስት ዓመት ኦዲት አላስደረግም። አንድ ተቋም የመንግሥት ሀብት ይዞ አምስት ዓመት አይደለም አምስት ወር ካልተጠየቀ ምኑን ግልጽነት አለ ይባላል። ይኼ ራሱ የመንግሥት ሚና ነው። ባንኩም እያበደረ የነበረው ኮርፖሬሽኑ ካለው ካፒታል በላይ ነው። አሁን የባንክ እዳ ያለበት ግን ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። ስለዚህ ተጠያቂ አይደለም ማለትኮ ነው።
ገንዘብ ሚኒስቴር ተገቢ ያልሆነ ድጋፍ እየሰጠ ነው ተቋሙ በጣም በእዳ እንዲሰጥም ያደረገው። ለዚህ ነው ተቋሙን ከማስጨነቅ ገንዘብ መሰረዝ አለበት የሚል ሐሳብ ነው ያቀረብነው። አንዳንድ እዳዎች ደግሞ መራዘም አለባቸው። ምክንያቱም የተቋሙ አቅም መታየት አለበት።

ከሥሙ ጋር በተያያዘ የሜቴክ ሠራተኛው መሆን በራሱ የሥነ ልቦና ጫና ያሳድራል፤ ምርታማነትም ላይ እንደዛው አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። የሠራተኞችን ሥነ ልቦና ከፍ ለማድረግ የሠራችሁት ነገር አለ?
በተቋሙ ውድቀት ላይ ሠራተኞች አይኖሩም ብቻ ሳይሆን በፍጹም የሌሉት በጣም ብዙ ናቸው። በነገራችን ላይ ከሜቴክ ውድቀት ጋር ሠራተኛው የለበትም። እንደ ሕግ የቆጠራቸው ሕጋዊ ያልሆኑ ነገሮች ግን አሉ፤ እሱም ስላለማመዱት እንጂ ፈልገው የወሰዳቸው አይደሉም። ስለዚህ ይህንን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ላይ በደንብ ሠርተናል። ያለፈው አንድ ዓመት ትልቁ ፈተናም ይኼው ነበር። አትሰናበትም እየተባለ ሰው የሚያስበው ስለመሰናበት ነው፤ አትታሰርም እየተባለ የሚያስበው ስለመታሰር ነው፤ እንነሳለን እያልነው የሚያስበው ስለ መውደቅ ነው። ይህን የማስተካከል ሥራ ባለፈው ስለሠራን የዘንድሮ ችግራችን አይደለም።

ዘንድሮ ሠራተኞች 24 ሰዓት ይሠራሉ፣ በምሳ ሰዓት ከ20 ደቂቃ በላይ የሚቀመጥ የለም። አምና ሁሉም ተጨናንቆ ነበር። ያንን ዘመን አልፈነዋል። ከዚህ በኋላ ሥም ቢቀየር ባይቀየር ማንም የሚጨነቅ የለም። ሜቴክ ቢቀጥልም ሠራተኛው አይፈራም። ለምን በተግባር አሳይቷል፤ ቢሾፍቱ፣ አቃቂና በፓወር በተግባር መሥራት እንደሚችል አሳይተዋል። በስርዓት መምራት ብቻ ነው የሚያስፈልገው እንጂ ሌላ ችግር እንደሌላ አረጋግጠዋል።
ሥሙንም ሰዉ ራሱ አይፈልገውም፤ በዛ ላይ ኮርፖሬሽኑንም ገላጭ ስላልሆነ መለወጣችን ግን አይቀርም።

በከባድ ችግር የተተበተበ፣ ሥሙ በመጥፎ የሚነሳ ድርጅት ኀላፊ ሆኖ መምራትንስ እንዴት ይገልፁታል? አያስፈራም?
እኔ ምንም አልፈራሁም። ምን መሰለህ! እንዲህ ዓይነት ነገሮች ብዙ ጊዜ እየገጠሙኝ ያለፍኳቸው ናቸው። መውጣት መውረድ፣ ስርዓት አልበኝነት አለ። ኢንሳ ውስጥ ሆኜ እዚህም ሜቴክ ውስጥ ግዢ የፈጸመ ሰው፤ ለምን እንደ ሜቴክ አትሆንም ይለኝ ነበር። ይኼኮ አንድ ቀን ይጠየቃል ነበር የምለው። ከስርዓት መውጣት ስላለመደብኝ፤ እዛም በስርዓት ነው የምኼደው፣ እዚህም በስርዓት የምኼደው።

የትም እንደምሔድ እርግጠኛ ስለነበርኩ፤ ይህንኮ ማንም በግሉ አላሳደገውም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ያሳደገው። ድሮም የካፒታሉ ምንጭ ሕዝቡ ነው። አሁንም የእርሱ ሀብት አለ፤ ስለዚህ መሥራት የሚችል ሰው ብቻ ነው የሚፈልገው። እና ስመጣ አልፈራሁም፤ የፈራሁት ግን የነበረውን ሰው እንዳለ አድርጎ ትንሽ ሰው ስትጨምርበት በድምጽ ስለምትበለጥ የምትፈልገውን አትወስንም። ደግሞ ስድስት ወር ሙሉ ጊዜያችንን የገደልነው በዚህ ነው። የነበሩት እንዳሉ ሦስት ሰዎች ብቻ ነው የተጨመርነው። ሰባት ነን፤ በትንሹ አዲሶቹ እንኳን አንድ አቋም ቢኖረን፣ በአራት ድምጽ እንሸነፍ ነበር። መፍራትም ሳይሆን የተፈተንኩባት ጊዜ የመጀመሪያው ስድስት ወር ነበር።

ከዛ በኋላ ነገሮችን እየጻፍን፣ እያስጠናንና እያጠናን፤ ነገሮቹ ወደ እውነታው እየመጡ ሲኼዱ ከስድስት ወር በኋለ ወደምንፈልው እየመጣን ሔድን።
እንደመጣን አምስት የትኩረት አቅጣጫ መርጠን ጥናት አስደረግን። አንደኛ ፋይናንስና ቁሳዊ ሀብት ነው። ኹለተኛው ትኩረታችን ምን ዓይነት ቴክኖሎጂና የተማረ የሰው ኀይላችንን አለን የሚለውን መለየት ነው። ሌላው የፕሮጀክት አመራር ነው። የያዝናቸውን ፕሮጀክቶች ማስተዳደር እንችላለን ወይ የሚለውን ምላሽ መስጠት ላይ አጠናን።

በማስከተል መልካም አስተዳደር ውስጥ ገባን። እሱንም ተከትሎ ምንድነው የምንሠራው የሚለውን ለመመለስ ጥናት አካኼድን፤ ገበያ እናጠናለን ወይስ ሽያጭ ብቻ ነው ሥራችን የሚለውን ለመመለስ።

ጥናቱን እየሠራን እንደምንነሳ ያኔ በጣም ግልጽ ሆነልኝ። ከዛም ሪፎርም እቅድ አቀድን። አቅምን ለየን ማለት ነው፤ ቢሾፍቱ በቀን አንድ አይደለም ስድስት ታመርታለህ፤ ይኼም ይቻላል አልን። ግብዓት ነው የታጣው እንጂ ቢኖር ኖሮ በእርግጠኝነት እንችል ነበር። አንዳንዶች የወደቀ አራግፈን ወደ ሥራ ስናስገባ አንድ የሚያመርቱ አራት አመረቱ። ፓወርም እንደዚሁ ተፈነጠረ፣ ኢትዮ ፕላስቲክም ቀደሙልን።
በመሆኑም ምንም የፈራኹት ነገር አልነበረም።

ሜቴክ የስኬት ታሪክ አልነበረውም ማለት ይቻላል?
የስኬት ታሪክ አለው። አንድ ተቋምም ይሁን ሰው ሲኖር ጥፋት ብቻ ሲያጠፋ አይኖርም። እርሱን ሲያደርግ የማይኖርበት አንዳንድ ጊዜ ሕግም ስላለና በዙሪያውም ሌላ ስላለ ጥፋት ብቻ እያጠፋህ እንድትኖር የሚፈቅድልህ የለም። ሜቴክን የማመሰግነው ፓወር ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪን ሠርቷል። የደርግም የኃይለሥላሴም አይደለም።

ይገባሉ ካልናቸው ኹለት ኢንዱስትሪዎች ሜቴክ የገነባው አንዱ ነው። ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ በደርግ የተገነባ ነው። በደርግ ሲሠራ በጣም ጥሩ ተደርጎ ነው የተሠራው። ትንሽ ነበር መጨመር የሚያስፈልገው ሜቴክ ትንሽ ጨምሯል። በአንጻሩ የገደላቸው አሉ። ለምሳሌ ጋፋት፤ ጋፋት በደርግ ጥሩ ነበር በሜቴክ ወደቀ። አቃቂ፤ የስኳር ፋብሪካን እንዲደግፍ ተደርጎ የተሠራ ነው፤ ሜቴክ ያን ያህል አላስኬደውም። አንድ ቦታ ጥንካሬ አንድ ቦታ ድክመት አለ።

ሜቴክ ይዞት የነበረው ግብና ርዕይ መቼም ሊጣል የሚችል አይደለም። እንደዛ ዓይነት ድፍረት መኖሩ በራሱ ራሱ ሜቴክ ያለውን አለማድረጉ ጣለው እንጂ በማኅበረሰቡ ውስጥ መነቃቃት ፈጥሮ ነበር። እናም ብዙ የስኬት ታሪኮችም አሉ። እኔ ትልቁ የውድቀት ታሪኩም የአመራር እንጂ የሠራተኛ አይደለም ነው የምለው።

ሜቴክ በወታደሮች ነው የሚመራው፤ ወታደር ደግሞ በዲሲፕሊኑ ነው የሚታወቀው። የሜቴክ አመራሮች እንዴት በዚህ ደረጃ ሊወርዱ ቻሉ?
እኔም የሚያናድደኝ እሱ ነው። ወታደር ስለሆንኩ ዘራፊ ተብለን መጠራታችን ያናድደኛል፤ ያሳፍረኛል። ግን የኔትወርክ ጉዳይ ነው የሚመስለኝ። የሚቀበልህ ሰው ከላይ ታደርጋለህ፤ አንተ ያልከው ነገር ሁል ጊዜ ነብይ የተናገረው እየመሰለ ተቀባይ እንዲሆን ታስገድዳለህ። ይህ ደግሞ የግለሰቦች ወይም የቡድኖች ፍላጎት ነው።

ለምሳሌ ሜቴክ ሲገዛ ይፈጥናል፣ ሲሠራ ይዘገያል። ፓወር ላይ ያለውን ድል እንዳየነው ደብረማርቆስ ላይ አምስት ዓመት ሳያስፈጽም የዘፈዘፈውን ንብረት ማንሳት ይቻላል። ጅቡቲ ላይ ስድስት ዓመት፤ ሞጆ ላይ ደግሞ አራት ዓመት የተቀመጠ እቃም አለ። ከገዛህ በኋላ የማትጠቀምበትን ለምን መጀመሪያውኑ ትገዛለህ።

አስተያየትህን ስጥ ካልከኝ፤ ግዢው ኮሚሽን ስላለው ይፈጥናል፣ መሥራት ግን አቅም ስለሚጠይቅ ስትንደፋደፍ ታሳልፈዋለህ። የነቀምቱን ስታይ 43 ሚሊዮን ዩሮ ነው። የውጪ ምንዛሬ የደም ዝውውር ሆኖብን ያዙኝ ልቀቁኝ እያልን ይህን ያህል ዩሮ ለአምስት ዓመት ያህል እዚህ ቢሾፍቱ ቁጭ ማድረግን ምን ይሉታል።

ሙስና አገሪቱን የወረረበት ዘመን ስለነበር ትስስር በዝቶ ይመስለኛል። ስትሠራ አይገኝም ስትገዛ እንጂ። ለዛ ይመስለኛል ሜቴክ እየተንሸራተተ የኼደው፤ ሌላው ዝግ ነው። ብዙ ጊዜ የሚፈሩ ሰዎች ችግር ያለባቸው ናቸው። ጋዜጠኛ ይጠይቃል እንጂ ምን ያመጣል። ዝግ የሆኑ ሙስናው ጣሪያ ነክቶ ስለነበር ይመስለኛል። የግዢና የተግባር ፍጥነትም ወደዛና ወደዚህ ስለሆነ ይመስለኛል። መከላከያን እንደሽፋን ተጠቅመውበታል፤ እንጂ መከላከለያ አውቆ አይመስለኝም።

በመከላከለያ የምንመራባቸው መመሪያዎችና የምንሠራቸው ሥራዎች ይታወቃሉ። ለአገር መከፈል ያለበትን ትልቁን መስዋዕትነት እንከፍላለን፤ እንደገና በትንሽ ወራዳ ነገር ትልቅ ሠራዊት ማሰደብ ያናድደኛል፤ ሰው ሲጠይቀኝም ደስ አይለኝም። መከላከያን መንካት ያመኛል።
አባላት የሚጠበቅባቸው የሥነ ምግባር ልህቀት አለ። መከላከያ የሚያስተምረውም የሚፈጽመውም ይኼን ነው። መከላከያ ሠራዊት የመጣው ከኅበረተሰቡ ነው። ኅብረተሰቡ ሌብነት ያወግዛል፤ ሌቦችን ግን ኅብረተሰቡ ውስጥ አሉ። ከዛ ውስጥ የመጣ ስለሆነ አንድ ኹለት ሊኖር ይችላል። ሜቴክ እንደተቋም ስለምናየው፣ መከላከያን እንደሚመራ፣ ያን ያህል የጀነራል ማዕረግ ይዘህ ነው የምትመራው። በዚህ ሆነህ የሠራዊትን ሥም የሚያጎድፍ ነገር መሥራት ወራዳ ነገር ነው። ሜቴክ ላይ ያየሁት ነገር ሲገዛ ይፈጥናል፤ ሲሠራ ይዘገያል። ይህ ተራ የመለቃቀም ነገር ካልሆነ የምትሠራውን ብቻ ብታመጣ ምን አለበት። ስድስት ዓመት ወደብ ላይ!

እኛ ከመጣን በኋላ ለይተን 360 ሚሊዮን ብር ነው የኮንቴነር ቆይታ ክፍያ የነበረው። እቃውን ሳትጠቀም ይህን ያህል ኪራይ መክፈልም አያስፈልግም ነበር።

በወደብ ላይ የተከማቹ ከ400 በላይ ኮንቴነሮች ጉዳይስ እንዴት ሆነ?
ሁሉንም አውጥተን ጨርሰናል፤ 19 ቀርተዋል፤ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን ነው። እነርሱን እናወጣለን። ሌላውን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ያስተላለፍነው አለ፤ ሕዳሴን ስናስረክብ ያስረከብነው ንብረት አለ። እነርሱ ከፍለው ያወጡትም አሉ። ከዚህ በኋላ ይህ ክምችት ጉዳያችን አይሆንም። ዘንድሮ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የገዛነው፣ አምና አንድም ግዢ አልነበረም። የምንገዛውን እቃ አላወቅንም። አንዳንዱ እዚህ ቀኑ አልፎበት ነበር። ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ቀኑ ያለፈባቸው ኬሚካሎች ነበሩ። እና ዘንድሮ ነው መግዛት የጀመርነው፤ አሁን አርብ ሞጆ ገብቷል፤ ሰኞ ይወጣል። ከዛ ሲነሳ ጀምሮ የአቅርቦት መስመር ተስተካክሏል፤ የመጀመሪያው ነው አሁን የመጣው። ቀጥሎ የሚመጡትም ቅዳሜና እሁድ ካልሆነ በቀር ወደብ ላይ ወይም ሞጆ ላይ ከኹለት ቀን በላይ አናቆይም።

ለሜቴክ ውድቀት በመጀመሪያውኑ የተነሳበት ዓላማና ተልዕኮ ትክክለኛ አልነበረ ይሆን?
ተልዕኮው በጣም ትክክለኛ ነው፤ የተሳሳተ ከሆነ አሁንም እየተሳሳትን ነው ማለት ነው። በተልዕኮ ደረጃ አሁንም አንነካም። በቃል ደረጃ የምናስተካክለው ይኖራል፤ መንግሥት አደረጃጀታችን ላይ የነካካነው ነገር ካለ እንጂ የተልዕኮ ችግር የለበትም፤ አገሪቱን ኢንዱስትራላይዝ ማድረገው ነው ተልዕኮው። የሁሉንም ኢንዱስትሪ ሳይሆን ክፍተት ያለበት፣ በግል ባለሀብቱ የማይሸፈን ግን ለኅብረተሰቡ እና ለአገር የሚያስፈልገውን። አሁንም ይህን ይዞ ይቀጥላል።

የሜቴክ ርዕዩ በኢንዱስትሪ የበለጸገች ኢትዮጰያን ማየት ነው። ይህ ርዕይ ጉድለቱ፤ መቼ? የእኛ ድርሻ ምንድን ነው? በኢንዱስትሪ የበለጸገች ሲባል ግብርና፣ ብረታብረት፣ ጨርቃጨርቅም አለ፤ የትኛው ኢንዱስትሪ ነው የእኛ ርዕይ የሚሆነው የሚለውን መለየት ነው።

እናም በመነሻውና በርዕዩ ምንም ስህተት አለ ብዬ አላስብም፤ በጣም ምርጥም ነበር። እንደውም የተወሰነ ጊዜ ድረስ በምርጥ ሁኔታ ወስደታል። ሜቴክ የወደቀው መጀመሪያ ጀምሮ አይደለም። ጥቂት ሰዎች ኮሚሽን ሲቀማምሱ አቅማቸውም እየወረደ የመጣ ነው የሚመስለኝ። መጀመሪያ ልክ የሠራዊቱን ባሕሪ ይዘው ነው የመጡት። ሠራዊቱ በእልህ፣ ሞትም ቢሆን ለዚህች አገር የሚጠቅም እስከሆነ፤ መድፍ እየበተነም ለቀብርም በማይበቃበት ደረጃ ይሞታል። ይህቺን አገር ለማልማት ብለው እንደተቋቋሙ የሠሩት በጣም ብዙ ጥሩ ነገር አለ። እነ ፓወርን ያቀዱበት መንገድም እንደዛ ነው። እንወጣለን ብለው ነው የተነሱት፤ እየወጡም ነበር። ሕዳሴን ያሰቡበት መንገድ ጥሩ ነበር። ሕዳሴ ከተደረሰ በኋላ ግን የወደቁ ኩባንያዎች መደገፊያ ገንዘቡን እስከማጣት ነው የደረሰው። ማንም ይመጣና ይገባል፤ ሥራ አይፈጽምም፤ ገንዘብ ይበላል።
በዚህ መንገድ እየቀዘቀዘ መጣና ወደኋላ ውድቀታቸው ሆነ እንጂ የተልዕኮ ችግር የለም። እንደውም እነርሱ በጀመሩት ፍጥነት ቢወስዱት ኖሮ ተልዕኮው አገር ያነቃንቅ ነበር። ውድቀቱ በኋላ መጣ እንጂ የተልዕኮን ችግር አይደለም።

ሜቴክ አርዓያ አድርጎ የተነሳው የአገራት ወይም የሌላ ተቋማት ልምድ አለ?
በዚህ ጉዳይ ላይ እርግጠኛ ባልሆንም በአብዛኛው የቻይና ኩባንያዎች እንደዚህ ዓይነት ሞዴል አላቸው። በአገራቸው ላይ አይደራደሩም። በነገራችን ላይ የቻይና ሥነ ምግባር (‘ኤቲክስ’) ለየት ያለ ነው፤ ሌላ አገር ያሳስቱ ይሆናል እንጂ ለራሳቸው አይሳሳቱም። ከዛ የተወሰደ ነገር ይኖራል ብዬ አስባለሁ።

ከሩስያ የወሰዱት ሞዴል አለ። ለምሳሌ ቢሾፍቱና ደጀን ከዛ የተወሰደ ነው። የራሻዎቹ አገራቸውንም አሳድገውበታል። ሜቴክም ማሳደግ ጀምሮ ነበር። ቢሾፍቱን ከተራ መጠገኛነት ከፍ አድርጓል፤ ከዛ ተነስቶ ወደ መገጣጠምና ጥገና አሳደገው። ሜቴክኮ መነሳት ጀምሮ ነበር፤ እንደገና ራሱን ጣለ እንጂ። ሌሎቹም ከቻይና ከደቡብ ኮርያ ኩባንያዎች የተወሰዱ ናቸው። ያው ልማታዊ የሚባሉ መንግሥታት የሚከተሏቸው ናቸው። እነሱ ግን ምርጥ በሚባል ሥነ ምግባር ነው የፈጸሟቸው። እነ ደቡብ ኮርያ በሥነ ምግባር ግራ ቀኝ የለም፤ እኛ ጋር በሥነ ምግባር መዋዠቅ ስንጀምር ያሰብነው ደረጃ አልደረስንም እንጂ ሐሳባችን ስህተት ነበር የሚል ዕይታ የለኝም። ሜቴክን በዚህ በኩል በግሌ አልወቅስም፤ ሌላው ሊተቸው ይችላል።

ሜቴክ ተወዳዳሪ ሆኖ እንደአዲስ ለመውጣትና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ባላችሁ ግንኙነት ላይ መተማመንን ከፍ ለማድረግ ምን እያደረጋችሁ ነው?
በ2011 የሠራነው የሪፎርም ሥራ አንዱ ይኼ ነው። መጀመሪያው ኮርፖሬሽኑ ባለቤት ሕዝብ ነው ብሎ ማመን ያስፈልጋል። እኔ እንደውም ሦስተኛና አራተኛ ባላደራ ነኝ፤ መጀመሪያ ለመንግሥት ነው የሰጡት፤ መንግሥት ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ለልማት ድርጅት፤ ልማት ድርጅት ነው ለእኔ የሰጠኝ። እና መጀመሪያ ባለቤቱን ማወቅ ነው፤ ለባለቤቱ ታማኝ የሚያደርጉንን አሠራሮች በሙሉ ዘርግተናል። በማንኛውም ጊዜ መጥቶ ሊጠይቀን ሊጎበኘን ይችላል። ሰራን የምንለው እውነት ወይ ውሸት መሆኑን መገምገም ይችላል።

ኹለተኛ ለደንበኞቻችን ታማኝ መሆን ነው። ደንበኞቻችን በአብዛኛው የኢትዮጵያ መብራት ኀይል፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪ፣ የክልል መንግሥታት፣ የፌዴራል የመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች፣ ልማት ድርጅቶች ናቸው። ጉዳት የደረሰባቸውና ሜቴክ ይዟቸው የሞተውም እነዚህን ነው።

በመጀመሪያ ሁሉም ጋር ውይይት አድርገናል፤ ንግድ ባንክንም ብሔራዊ ባንክም ኼደን አስረድተንናል። አለ የሚባለውን ችግር አውርተውናል። እኛም ያሉት እውነት እንደሆነ በአምስቱ የትኩረት ሐሳቦች ላይ ባጠናነው ጥናት እንዴት እውነት እንደሆነም ጭምር ነግረናቸው በጣም ተግባብተናል።
አሁን እንደውም እየደረሱልን ያሉት እነርሱ ናቸው፤ የእኛ ጥረት አንዱ ነው። ነገር ግን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት አለብን። ሠራተኞቻችን ሞራላቸው የወደቀ፣ ደሞዛቸው የቀነሰ ነው። በዚህ መልክ ከፍተኛ አምራች መሆን አይቻልም። ስኳር ኮርፖሬሽ እያደረገልን ያለው ድጋፍ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የነበረን የገዢና የሻጭ ብቻ ግንኙነት አሁን የደጋፊነት ሚና አለው፤ በማሠልጠን፣ በማማከር ይደግፈናል፤ በብዙ ነገር እየደገፉን ነው ያሉት። ሁሉም ያስመረርናቸውም ለውጥ እውነት መሆኑን አውቀው ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉልን ነው።

ብዙ ከተሞችን አቋርጠው ሱዳን ድንበር ላይ የተያዙ ጦር መሣሪያ የያዙ የተባሉ ከባድ መኪናዎች ነበሩ። ጉዳያቸው እንዴት ተፈታ?
አንዳንድ ነገሮች ይጋነናሉ እንጂ የነበሩ ነገሮች ናቸው። እኛ ከውጪ እንገዛለን፤ ወደ ውጪ የምንሸጣቸው ነገሮችም አሉ። ማንም አገር ቢሆን ከውጪ የሚያስገባው አለ፤ የሚያስወጣውም አለ፤ አሜሪካም ብትሆን። እኛ የተለየ ነገር አላደረግንም፤ ግን የሆነ ቡድን ተነሳና፤ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከመንግሥት ይልቅ የሆነ ቡድን መርማሪ፣ ፈታሽ፣ ስርዓት አስከባሪ የሚመስልበት ሁኔታ አለ። እና በድንገት አስቆሙን። እኛ ሁሉንም አሟልተናል፤ አሁንም ወታደራዊ ተቋማቱ በሕግ እስከመሚወጡ ድረስ ዛሬም ራሱ እኛ ጋር ናቸው። እነርሱ የሚሠሩትን፣ የሚያመርቱትን፣ የሚሸጡትን የሚልክም የሚያመጣም ሜቴክ ነው።

ከሱዳን ጥይቶች ተጠይቀን ነበር፤ እኛም ከእነርሱ የጠየቅነው ነበር። ሕግ አለመጣስ ነው እንጂ አለመሸጥ አይደለም የሚያስፈልገው። በሕግ መሠረት መከላከያም ብሔራዊ ደኅንነትም በሚያውቀው፤ በመረጃ ይህን ሁሉን ነገር አሟልተን ሰነድ አስይዘን ነው የላክነው። ተማርኳል አንለቅም ተባለ።
አንዱ በጣም ከሚያሳዝነኝ ነገር የኢትዮጵያ ሠራዊት በቀበሮ ጉድጓድ እየኖረ፣ የትኛውም ቦታ ላይ ሰላም ጠፋ ሲባል ፖሊስ እየሆነ መከራ እየበላ አምስት መኪና ይዞ ማረክኩት ሲባል ያሳፍራል። የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲህ በሰፈር የሚማረክ አልነበረም። ግን ሕዝብ ማክበር አለብን። ማረክኩት የሚሉት ሰዎች ሕዝብ ስላልነበሩ ለሕዝብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ጥሩ አልነበረም።

ያስወሩብን መትረየስ፣ ስናይፐር እና ዶላር ተጭኗል ብለው ነው። እዛ ያለው ወጣት በዚህ ነው የተነሳው። እኛ ሜቴክ ያለነው ብቻ ሳንሆን የመከላከያ ሠራዊት በጠቅላላ ለሕዝብ ጥቅም የሚጎዳ ምስጢር ሲሆን ይይዛል እንጂ ከሕዝብ አይደብቃቸውም። የምንሠራው ለእናንት ነው፤ እናንተ ካላችሁ ፈትሹት አልናችሁ። ምስጢርም የምንለው የሚጎዳችሁ ከሆነ እንጂ ምስጢር የለም አልናቸው። አይደለም ስናይፐር ትንሽ ሽጉጥ እንኳን አልነበረም። ሕዝብ ባለበት ተፈተሸና አለፈ።

ይህን ያደረግነው ይኼ ሠራዊት በየሔደበት ማስቆም ተገቢ ነው ብለን አይደለም። ግን ሁልጊዜ ከራስ በፊት ለሕዝብ ነው የመከላከያ የመጀመሪው እሴት ነው። ከራስ በላይ ለሕዝብ ነው። ሕዝብ ካለ ግን ለእርሱ ካልጠቀመ ምን ያደርግልኛል። እና አሳየናቸውና አለፈ፤ ከሕዝቡ ጋር ተስማማን።
የተፈታበት መንገድ ሕዝቡ ጋር ወርደን ነው፤ ክልል ላይ ተነጋግረን አልፈታንም። ይፈቱልን ነበር፤ ማን ነው የላከው ይምጣና ያነጋግረን አሉ፤ ኼድኩ። በእኔ ፊርማ ነው የኼደው። በሙቀት ጊዜ ካልቀዘቀዘ መነጋገር ስለማይኖር፣ ከቀዘቀዘ በኋላ መደማመጥ ስንጀምር የሚፈገለውን ማውራ ወደ ቁምነገር ይወሰዳል ብዬ ኼድኩ፤ በሰላም ነው ያለቀው።

ከሜቴክ ጋር የተያያዙት የመርከብና የአውሮፕላን ግዢዎች የት ደረሱ?
መርከቦቹ በ2009 ያለቀ ጉዳይ ነው፤ ተሸጠዋል። እንደውም ዕድለኞች ነን፤ እኛ መርከቦቹን ከሸጥን በኋላ አንዷ መርከብ ሰጠመች። እኛ ይዘናት ብትሰጥም ኖሮ ኪሳራችን ይበዛ ነበር። መርከቦቹ በጣም አሮጌ ናቸው፤ ባሕር ትራንስፖር ሊያስወግዳቸው የነበሩ ናቸው። ሜቴክን አንዳንድ ጊዜ ድፍረቱን እናደንቅለታለን ግን ድፍረቱን ልክ ያሳጣዋል። መርከቦቹን ወደ ንግድ አስቀጥላቸዋለሁ አለ፤ ይሁንና አንድም ሳንቲም ለሜቴክ አላስገቡም። በኋላ ላይም 600 ሺሕ ዶላር አክስረው ተሸጠዋል።
የአውሮፓላኗ ጉዳይ በሜቴክ ሥም ስለመጣች ነው። በኋላ ስናጣራ ሜቴክ ከውጪ ለመከላከያ አውሮፕላኖች ሊገዛ ይስማማሉ። ካስገባቸው በኋላ አውሮፕላኖቹ የመከላከያን ፍላጎት አያሟሉም። ከዚህ ግዢ ጋር በተያያዘ አንድ ሰው ጣልቃ ገብቷል፤ የሚያገናኝ ነው መሰለኝ። አውሮፕላኗን ድርጅቱ ላገናኘው ሰው ይሰጠዋል። ያገናኘው ሰው ሊያስገባ አይችልም፤ ስለዚህ በሜቴክ በኩል ገብታ በጋራ የሆነ ነገር ለመሥራት አስበው ነበር። ከዛ ገቢው እንዴት ለመንግሥት ገቢ እንደሚሆን አላውቅም፤ ብቻ እንደዛ ታስቦ ለሌላ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጥ ድርጅት ይሰጡታል። ስትገባ በሜቴክ ስለሆነ አውሮፕላናችን ጠፋች አሉ። ምክንያቱም በእኛ ነው የገባችው፤ በኋላ ተገኘ። የወሰዳትም አካል በጋራ እንድንሠራባት ነው የመጣችው፤ አትሠራም ቆማለች አለ። አሁን ጉዳዩ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንደያዘው ነው፤ ባለእዳዎችም አልተከፈለባቸውም።

የሜቴክ መጻዒ ዕድል ምንድን ነው?
የሜቴክ መጻኢ ዕድል ይዞት የነበረውን ርዕይ እንዳለ ሆኖ ወደ ራሱ ይወስድና በዛ ርዕይ ይቀጥላል፤ ያሳካዋል። የተሰጠው ተልዕኮ እንደነበረ መንግሥት በርትታችሁ ሥሩ ነው ያለው። ይህን ሕዝብ እንዳስከፋነው እንክሰዋለን፤ በእርግጠኝነት ደግሞ በቅርብ ጊዜ ለውጡን ያያል ብዬ እገምታለሁ።

በኢንዱስትሪ ማስፋፋት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ እንችላለን፤ እናደርገዋለን። ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው ኢንዱስትሪዎች በተለይ ብረታብረት ላይ፤ ዘላለም ብረት እያስገባም የምንቀጥልበት ሁኔታ መቆሚያው ሩቅ አይሆንም። ብዙ መሥራት ይጠይቀናል፤ መንግሥትና ኅብረተሰቡም እኛን ብዙ መደገፍ ይኖርበታል። ግን እዛ ለመድረስ የምንችልበት ዘመን ሩቅ አይሆንም። መጻኢ ዕድሉም ጥሩ ነው፤ መንግሥትም እየደገፈው ነው እኛም በኀይለኛው እየሠራን ነው።

አብዛኞቹ ኢንደስትሪዎች እያደጉ እንደሆነ የሚያሳይ፤ በቁጥር የሚገለጥ እቅድ ከ9.5 ቢሊዮን በላይ ገቢ ማስገባት አለበት ቴክ፤ ከ607 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ ማትረፍ አለበት፣ ኹለት ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ ማስገባት አለብን። በዘንድሮው ዓመት የእሴት መጨመርን ወደ 30 በመቶ እናሳድጋለን፤ እያልን በመንግሥት ግዢ 45 በመቶ ከደረስን ‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’ ተብሎ ነው የሚታወቀው። እኛ ግን ስልሳ ለመድረስ የሚያቅተን ነገር የለም፤ እንደርሳለን። ሙሉ በሙሉ አንድን ነገር የሚያመርት የትም ስለማይገኝ እሴት እየጨመር ስልሳ በመቶ እንደርሳለን። ለዚህም እየተሟሟትን ነው፤ ኮርፖሬሽኑ እንዲኖር መንግሥት ይደግፋል፤ እኛም ጥረት እያደረግን ነው። ለመኖር ግን የሕዝብ መሆኑን ማሳወቅ ይኖርበታል። ክልሎች ላይ በማኅበራዊ አገልግሎት በመሳተፍ እንዲሠሩ ዘጠኙም ክልልና ኹለቱ ከተማ አስተዳደሮች ላይ መድበናቸዋል። ሁሉም ቦታ አለን ማለት ነው፤ በምንችለው ከትንሽ ጀምረን ወደ ላይ እናድጋለን። ለየክልሉ ወጣቶች ሥራ ዕድል በመፍጠር እንጀምራለን።

አነስተኛ እና ጥቃቅን ፋብሪካዎችን በማቋቋም ወጣቶች የግላቸው እያደረጓቸው እንዲሔዱ በማድረግ እንቀጥላለን። ስለዚህ ሁሉም ክልሎች የእኛ ነው እንዲሉት እናደርጋለን። መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ይዘህ ገበያው አያሳስብም። መጀመሪያ የምትሸጠው ለእሱ መሆኑን፤ የምንሠራለት እሱን እንዲጠቅመው መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ አለብን። አሁን ሁሉን ስለማንደርስ ከትንሹ ነው የምንጀምረው፤ እየጨመርን መኼዳችንን ለሕዝቡና ለወጣቱ ለራሱ እንዲሰማው እናደርጋለን፤ የመንግሥትን ፖሊሲ እናስፈጽማለን። በእርግጠኝነት ሜቴክ በዚህ ይቀጥላል። ርዕዩንና ግቡን አሁንም አደንቃለሁ ስለዚህ እሱን ለማስቀጠል ትንንሽ ነገሮችን ማስተካከል ካልሆነ እንቀጥላለን ብዬ አስባለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here