መብት እና ግዴታ፣ የአንድ ሣንቲም ኹለት ገፅታ

0
596

የሰው ልጆች የተጎናጸፏቸው ማናቸውም መብቶች በውስጣቸው ግዴታን ወይም ኀላፊነትን ይዘው ይገኛሉ የሚሉት ካሳዬ አማረ፣ በኢትዮጵያ ኀላፊነትን ካለመወጣት ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችንና መዘዛቻን የሕግ ልዕልና መሸርሸርን፣ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ እና ማኅበራዊ ሚዲያ ጉድለቶችን ለአብነት በመጥቀስ ሙግታቸው አቅርበዋል። ለራስ ብሎም ለመጪው ትውልድ ኀላፊነት መወጣት ዴሞክራሲን ለመገንባ፣ ዕድገት ለማምጣትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ሲሉም ካሳዬ ይሞግታሉ።

የሰው ልጅ የተጎናፀፋቸው መብቶች እና ነፃነቶች ሰው በመሆኑ፣ ከፖለቲካዊ አካል ጋር ባለው ግንኙነት፣ ከሚያራምደው እምነት፣ ከተደነገጉ ሕግጋት የሚመነጩ እና የሰው ልጅ የተቀዳጃቸው ናቸው። እነዚህ መብቶች እና ነፃነቶች በስብኣዊ መብቶች፣ በዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ በሞራላዊ መብቶች፣ በሕጋዊ መብቶች … ወዘተ ሥር የሚጠቃለሉ ሆነው በሕገ መንግሥት፣ በሕግ ሰነዶች፣ በሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ውስጥ ተካተው ይገኛሉ። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ደግሞ በመግለጫ ውስጥ ተካተው ቀርበዋል፣ የቃልኪዳን ሰነዶች ተዘጋጅተውለት አገራት እንዲያፀድቁት ተደርጓል፣ እየተደረገም ነው። በዚህ መሠረት በኢትዮጵያ ፌደራል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 13 እስከ 44 ድረስ የስብኣዊ እና የዲሞክራሲያዊ መብቶች ተዘርዝረዋል፣ ኢትዮጵያም የቃል ኪዳን ሰነዶቹን ፈርማ አጽድቃለች።

ሊነጠሉ የማይችሉ
መብት/ነፃነት እና ግዴታ/ኀላፊነት ተነጣጥለው ሊታሰቡ የማይችሉ የአንድ ሣንቲም ኹለት ገፅታዎች ናቸው። መብቶቻችንም ሆነ ነፃነቶቻችንን ስንጠቀም በውስጣቸው ግዴታ እና ኀላፊነትን ይዘው እንደሚገኙ መገንዘብ ተገቢ ነው። መብት/ነፃነት እና ግዴታ/ኀላፊነት በጋራ መታሰብና መተግበር ከግለሰቦች ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን ተቋማትም፣ መንግሥትም በተመሣሣይ ተጋሪ ናቸው።

በአንድ የጋራ መኖሪያ ሕንፃ ላይ ያለ ኗሪ ሙዚቃ ማዳመጥ ፍላጎት ቢኖረው/ቢኖራት ማዳመጥ ይችላል/ትችላለች ነገር ግን ይህንን መብት ሲጠቀም/ስትጠቀም ከእሱ/ከእሷ መኖሪያ ውጭ ያሉ ጎረቤቶች ደግሞ ፀጥታ ማግኘት መብታቸው ስለሆነ ሁሉም ሳይረበሹ ሚዛን በመጠበቅ ማዳመጥም ሆነ ፀጥታ ማግኘትን ጎን ለጎን ማስኬድ ሲቻል መብት በግዴታ ውስጥ ሆኖ ሥራ ላይ መዋሉን ማስተዋል ይቻላል። የሙዚቃ ድግስ የሚያቀርቡ ድርጅቶችም ሥራቸው ስለሆነ ሙዚቃውን ለታዳሚዎቻቸው የማቅረብ መብት ሲኖራቸው በአካባቢያቸው ያሉ ኗሪዎች ሆነ ድርጅቶች ደግሞ ሰላም ማግኘት ስላለባቸው የሙዚቃ ድግስ አቅራቢው የሚያስተናግደብትን ክፍል/አዳራሽ ከመነሻው ድምፅ በማያሳልፍ ቁሳቅስ በመሥራት ሌሎችን ሳይረብሽ ፕሮግራሙን በማስኬድ መብት እና ግዴታን ማጣጣም ይችላል ማለት ነው።

ሠራተኞች ሥራ ሲቀጠሩ በሚገቡት ውል ውስጥ የውሉ አካል ከሚደረጉት መካከል የሠራተኛው እና የአሠሪ ድርጅቱ መብት እና ግዴታ በዝርዝር የተካተተ ነው። በዚህ መሠረት ሠራተኛውና አሠሪ ድርጅቱ መብት እና ግዴታ በእኩል እንዲያከብሩት ይጠበቃል። በአመዛኙ በተግባር የሚስተዋለው ግን አሠሪው ግዴታዎች ላይ ትኩረት ሲሰጥ በሠራተኛው በኩል ደግሞ መብቶች ላይ የማተኮር ነገር ይሰተዋላል። መብት እና ግዴታ በእኩል ሥራ ላይ የሚውሉ እንጂ በማበላለጥ ተግባራዊ የሚደረጉ አይደሉም።

ክፍተቶች እና መዘዛቸው
(ሀ) የሕግ ልዕልና መሸርሸር
የሕግ የበላይነት መከበር ለአገር እና ለሕዝብ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እና የልማት ሥራዎችን ለማከናወን መሠረት መሆኑ አሌ አይባልም። በአገር ውስጥ ስብኣዊ እና አገራዊ ደኅንነት ሲጠበቅ፣ ሕዝቡ የተረጋጋ ሕይወት ሲኖረው እና ሰላም ሲሰፍን የልማት ሥራዎች አመርቂ ውጤት ያስገኛሉ። ማንኛውም የልማት ሥራ የሕግ ልዕልና (የበላይነት) መከበርን ይጠይቃል፣ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ (ኢንቨስትመንት) እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል። በአገራችን ያለው አለመረጋጋት ለሕግ ልዕልና መስፈን ጋሬጣ እንደሆነ የምንታዘባቸው ኹነቶች ይናገራሉ።

በሌላ ጎን ደግሞ የበላይ ኀላፊ ወይም አካል ውሳኔን የበታች ኀላፊዎች፣ ሠራተኞች ለመተግበር ዳተኛ የመሆን፣ ላለመተግበር የመሞከር አዝማሚያ ይታያል። ያለውን ነፃነት ከኀላፊነት በማፋታት መሠራት ያለባቸው በወቅቱ ሳይከናወኑ በመቅረታቸው ሕዝብ/ድርጀት ማግኘት የሚገባቸውን ውሳኔ/አገልግሎት አያገኙም። የዚህ ድምር ውጤት ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።

ይህንኑ የሚያጠናክርልን በቅርቡ በአማራ ክልል፣ በምዕራብ ጎንደር፣ አርማጮሆ ወረዳ ፍርድ ቤት ውስጥ በችሎት ላይ ተሰይመው የነበሩ የፍርድ ቤቱ ዳኛ ለስምንት ተከታታይ ጊዜ የሰጡትን ትዕዛዝ ባለመፈፀም እና ችሎት በመድፈር አንድ የፖሊስ አባል ላይ ያሳለፉትን ውሳኔ የፖሊስ ክፍል ማስከበር ሲጠበቅበት እና በውሳኔው ላይ ቅሬታ ቢኖር እንኳን አቤት ማለት ሲገባ ዳኛውን ለማሰር በመሞከራቸው ጠፍተው ሌላ ከተማ ሸሽተው እንደሔዱ ከአዲስ ማለዳ የቅዳሜ መስከረም 10/2012፣ ዕትም ቁጥር 46 በወጣው ጋዜጣ ላይ ለማንበብ ችለናል። በሕግ ልዕልና ላይ ያለውን ችግር በተመለከተ በዚሁ ጋዜጣ ላይ “በዳኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም” የሚል ርዕሰ አንቀጽ አንብበናል። ከዚህ እውነታ የምንገነዘበው መብት እና ኀላፊነት ማዶ ለማዶ መሆናቸውን ነው።

(ለ) በፖለቲካው ውስጥ ያለ ተፅዕኖ
የፖለቲካ ድርጅቶች መብቶቻቸውን/ነፃነቶቻቸውን ሲጠቀሙ በጎኑ ግዴታ እና ኀላፊነት እንዳለባቸው ሊዘነጋ አይገባም። በየጊዜው የሚስተዋሉ ጉዳዮች ሲፈተሹ ግን ባላቸው መብት/ነፃነት የሚያስተላልፉት መልዕክት ግዴታን ያሽቀነጠረ እና ኀላፊነት በጎደለው መልኩ እየቀረበ እንደሆነ ነው። በሚያደርጉት ቅስቀሳ ከአገር እና ከሕዝብ ደኅንነት አንጻር የሚያመጣውን ጉዳት ትኩረት ባለመስጠት በዜጎች መካከል ጥርጣሬ እንዲኖር፣ እንዲጎለብትና በብሔራዊ አንድነት ላይ የጋራ መስመር እንዳይኖራቸው ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ይስተዋላል።

አገር የጋራ ሀብት ናት፣ ፖለቲካዊ አቋም የግል መሆኑ ተዘንግቶ ጠባብ ፍላጎትን ለማሳካት ሲባል ኹከት እና ሰላም ለማደፍረስ ቅርብ የሆኑ ሐሳቦችን በመሰንዘር መብትን በመጠቀም ላይ ብቻ ግዴታና ኀላፊነትን ወደ ጎን የማድረግ መንገድ ላይ የሚያስቀር መስመር ነው። በአንዳንድ የፓርቲ ፖለቲከኛች የሚሰተዋለው ደግሞ የበሰሉ ፖለቲከኞች ባለመሆናቸው የሚቀርቧቸው ሐሳቦች ጥሬ ከመሆናቸው ባሻገር ወጥነት የጎደላቸው ስለሆነ በአማራጭ እና በተሻለ ሐሳብ በመሞገት ሌላውን ተፎካካሪ ከመርታት ይልቅ በጎሳ/በቋንቋ ውስጥ በመደበቅ ወይም ሌላ አሰባሳቢ ስስ አጀንዳ በማራገብ ያልጠራ ሐሳብ ለመሸጥ ይሞክራሉ። መንግሥት ለመሆን የሚጥር የፖለቲካ ድርጅት መብት/ነፃነቱን እና ግዴታ/ኀላፊነቱን ሚዛን ጠብቆ ሊራመድ ግድ ይለዋል፣ የጠራ የፖለቲካ መስመርም ማራመድ ያስፈልገዋል።

(ሐ) የማኅበራዊ ሚዲያ ጉድለት
የማኅበራዊ ሚዲያው መብት እና ግዴታ የሚባሉ የማይመለከተው የሚመስል መድረክ ከመሆኑ ጎን ያልጠራ ሐሳብ የሚቀርብበት መሆኑ ማንም አይክደውም። ይህ ሲባል በሳል፣ አስተማሪ እና በሰለጠነ መንገድ ነጻነትና ኀላፊታቸውን በቅጡ የተረዱ ተጠቃሚዎች የሉበትም ማለት አይደለም። ብዙ ሊያስተምሩን፣ ሊገሩን የሚችሉ ተጠቃሚዎች አሉ። በዛው ልክ ግን ፀያፍ ቃላትን ከመደርደር ጀምሮ፣ የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት፣ ያልበሰለ ሐሳብ አልፎም የቀረበውን ሐሳብ ትተው የግለሰብ ስብዕናን የሚያጠለሹ ግለሰቦች እንዳለቡት ሁሉም የሚያውቀው ነው። በተጨማሪ አንዳንድ አክቲቪስቶች ማኅበራዊ ሚዲያውን በሕዝብ ሥም የራሳቸውን አጀንዳ ኀላፊነት በጎደለው መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያ እንዲራገብ ያደርጉታል። እየተፈጠረ ያለውን ውዥንብር ሁሉም የሚረዳው ነው። አገርን ቦታ ሳይሰጥ ለጎሣ ብቻ የሚደረግመው ተርተር ጥፋት እንጂ ለማንም የሚያመጣው ውጤት የለም።

ነገር ግን ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ እና መብት/ነፃነት እንዲሁም ግዴታ እና ኀላፊነትን ሚዛን ላይ በማድረግ የምንጠቀምበት ከሆነ አዎንታዊ አስተዋጽፆ የትየሌለ ነው። ይህ ሲባል በሚቀርቡ ሐሳቦች ላይ የሰላ ሂስ/ሙግት መቅረብ የለበትም ለማለት አይደለም። ሐሳብን በሐሳብ መሞገት የሰለጠነ መንገድ ስለሆነ ሊበረታታ የሚገባው ነው ። ለአፍራሽነት የምንሰነዝረው አስተያየት ለራሳችን የተሰነዘረ እና መዳረሻው መውደቅ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። በምንጠቀምበት የሐሳብ ነፃነት ውስጥ ኀላፊነት እንዳለ መታወቅ ያለበትና ሰው ክቡር ፍጡር በመሆኑ ከመናቆር የሚገኝ ትርፍ ስለሌለ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግን ሞጋች ሐሳቦችን ማቅረብ የሚያሻግረን አንዱ መንገድ ነው።

በኀላፊነት መኖር
ለማስተማር፣ ለማሳወቅ ኀላፊነቱ የጋራ ነው፣ በመብት/በነፃነት እና በግዴታ/በኀላፊነት መካከል ሚዛን እንዲጠበቅ የማስተማር፣ የማሳወቅ ኀላፊነት ከቤተሰብ ጀምሮ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሁለም ዓይነት የሚዲያ አካላት፣ ሲቪል ማኅበራት፣ አርዓያ የሆኑ ዜጎች እና ሌሎች ምንጮችን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው። የማሳወቁ አንዱ ክፍል የሆነው “ይመለከተኛል” የሚል አስተሳሰብን የሚያራምዱ እና የሚተገብሩ ዜጎችን በማፍራት በኩል ብዙ መድከም ይጠበቅብናል። በተጨማሪ መብትን/ነፃነትን እንዲሁም ግዴታና ኀላፊነትን በአርዓያነት ላይ በተመረኮዘ መንገድ ማሳወቅ እና ማስተማር የሚጠበቅ አገራዊ ግዴታ ነው።

ሁላችንም ራስን በራስ ከመምራት ጀምሮ በቤተሰብ፣ በጉርብትና፣ በአካባቢ፣ ተቀጥረን ወይም በግላችን በምንሠራበት ድርጅት እና በአገር ደረጃ በኀላፊነት መሥራት እና መኖርን ልንተገብረው ይገባል። የዴሞክራሲ ጅማሮ ራስን ከመምራት ይጀምርና በሒደት ዜጎች መብቶቻቸውን እና ነፃነቶቻቸውን ይጠቀማሉ፣ በአንጻሩ ደግሞ ግዴታዎቻቸውን እና ኀላፊነቶቻቸውን ይወጣሉ። ዲሞክራሲን በማጎልበት፣ ዕድገት እውን በማድረግ እና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ሒደት ውስጥ ሁሉም ተዋናይ በመሆን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ይቻላል።

ካሳዬ አማረ በአድማስ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ
በማስተማር ላይ ይገኛሉ። በኢሜል አድራሻቸው amarek334@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here