መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅለማይቀረው ጦርነት ዝግጁ እንሁን!

ለማይቀረው ጦርነት ዝግጁ እንሁን!

ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን የእርስ በእርስ የሥልጣን ሽኩቻም ሆነ የመንግሥት ለውጥ በምናካሂድ ወቅት የውጭ ተንኳሽ ተለይቶን የሚያውቅ አይመስልም። ኢምፔሪያሊዝም የሚሉት የተስፋፊ ስርዓትን የሚያራምዱ ቅኝ ገዢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ጎረቤቶቻችንም ደካማ በመሰልናቸው ጊዜ ገብተው ያማራቸውን ለመውሰድ ከመጣር ቦዝነው አያውቁም፤ ዛሬም ድረስ ሲጥሩ ይታያል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላና በደቡብ ክልሎች ውስጣዊ ሰላም ለማምጣት ተቸግሮ እንዲህ በሚንከላወስበት ወቅት፣ ሱዳን ያዙኝ ልቀቁኝ እያለች እንደምትገለገል እየተመለከትን ነው። የሱዳን ወረራ በሰላማዊ መንገድ ይፈታል እያልን ወረራዋን ለዓመታት ታግሰን የውስጥ ችግራችንን ለመቅረፍ በምንሯሯጥበት ጊዜ ትዕግስትን ፍርሃት አድርጋው እያደር የበለጠ እየገፋች ትገኛለች።

ሲነገር እንደምንሰማው 70 ኪሎ ሜትር ገብታ ምሽግ ቆፍራ ለማይቀር ጦርነት ተዘጋጅታ መጠበቁ አላስችል ብሏት፣ አሁንም ለተጨማሪ መሬት ፍላጎቷ ጦርነት እየቆሰቆሰች እንደሆነ ይታወቃል። ጠብ አጫሪ የሆነ አካል ጠቡ እስካልተቀጣጠለ አርፎ የሚቀመጥ ባለመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለማይቀረው ኹሉን ዐቀፍ ጦርነት እንድንዘጋጅ አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች።

ሁሌ ከመከላከል አስተሳሰብ ወጥተን ዝግጁነታችንን አጠናክረን በአንድነት የማያስደፍረንን እርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅብን ግልፅ ነው። የአጸፋውን ድንገተኛነት በተመለከተ ለባለሙያዎቹ መተው የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ መደበኛው አካል ብቻውን የሚወጣው ባለመሆኑ፣ ኅብረተሰቡም እንዲዘጋጅ ማድረጉ ጠቃሚ ይሆናል።

የአገር ጦር ሠራዊትን ማጠንከርና የተዋጊውን ሞራል ከፍ ማድረግ በሚያስፈልግበት በአሁኑ ወቅት፣ ሞራልን ከሚያላሽቅ ተግባር መንግሥት መታቀብ እንዳለበት ማሳሰብ ያስፈልጋል። ተዘናግተዋል ብለው ንቀው ምሽጋቸውን በድጋሚ አልፈው ይበልጥ ወደ እኛ እንዲገቡና የሞት ምድርን እንዲረግጡ ማድረጉን ለባለሙያዎች ብንተወውም፣ ድንበርንም ሆነ ቦታን ያለጠባቂ ትቶ መቀመጡም ዝግጅታቸውን እንዲያጠናክሩ ስለሚያድረግ ለድሉ የሚያስከትለው መስዋዕትነት ከፍተኛ ይሆናል።

በጉዳዩ ላይ የተለያዩ መንግሥታትም ሆኑ የአፍሪካ ኅብረትን የመሳሰሉ ተቋማት “ኹለቱም አካላት ጉልበትን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ” በማለት ወታደራዊ እርምጃ ከማድረግ ይልቅ በዲፕሎማሲ ውዝግቡን እንዲፈቱት ሲመክሩ ይደመጣል። ሠላማዊው መንገድ መፍትሄ ቢሆን ኖሮ፣ የዛሬ ኹለት ዓመት ችግር ላይ መሆናችንን ዐይታ ሱዳን በጉልበት ባልወረረችን ነበር። እንወያይ ብላ መሬት ስጡኝ ብላም ብትደራደር ምላሻችን ምን ይሆን እንደነበር ግልፅ ነው።

“እሾህን በእሾህ” ነውና ብሂሉ፣ የወጋንን የምናስወጣው በልመናና በምልጃ ሊሆን አይገባም። ሲሆን እሾሁን በመርፌ ቀይረን ሰውነታችን እንዳይጎዳ አደንዝዘን የምናስወጣበት ቢሆን ይመረጣል። ሰውነታችን ውስጥ የገባው እሾህ ተመልሶ ቆይቶ እንዳይገባ አርቀን መጣል እንጂ በአካባቢው ዝርያው እንዳይኖር የበቀለበትን ግንዱን ብንቆርጠው፣ እሾሁ ተበትኖ ለመልቀም ስለሚያዳግት ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።

ሱዳናውያን ጦርነት አይችሉም እየተባለ በተደጋጋሚ የሚነገረው ጦራቸውንና ዝግጅታቸውን እንድንንቅና የእኛም እንዲዘናጋ ስለሚያደርግ ሊቆም ይገባዋል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። የጎንደርን ቤተመንግሥት ያፈረሱት ተንቀው የነበሩት ደርቡሾች እንደነበሩ፣ የአፄ ዮሐንስም ሕልፈት ምክንያት የሆነው የእነሱ ወረራ መሆኑን ሳንዘነጋ፣ ኃያላን አገር እንደወረረችን አስበን ነው መዘጋጀት የሚኖርብን።

መብትና ነፃነትን፣ ነፋጊው አካል በፍላጎቱም ሆነ በውትወታ እንደማይሰጥ ረጅም ታሪካችን ያስተማረን ሕዝብ እንደመሆናችን፣ ኅብረተሰቡን እየመራ ያለው መንግሥት የሕዝቡን ሥነልቦና ተረድቶ እርምጃ ከመውሰድ ሊዘገይ አይገባም። መንግሥት ዝም ያለ የመሰለው ሕዝብ፣ ነገሩን በራሱ ለመፍታት ሲል የማይሆን ተግባር ውስጥ ከመግባቱ በፊት ይመለከተናል ያለው የመከላከያ ኃይል ጊዜ ሳይወስድ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

በወንድማማችነት በጋራ የሚፈታ ችግር፣ የጋራ ሦስተኛ ወገን የሆነ ጠላት ሲመጣ ብቻ እንደመሆኑ መንግሥት ያያዘውን አቋም በመፈተሽ አካሄዱን ሊያስተካክል ግድ ይለዋል። ነገሩ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አንዳይሆን፣ ለመጣበት ወረራ ምላሹ ጉልበት ብቻ እንደሆነ ሊገነዘበው ያስፈልጋል።

የአባይ ግድብን ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን ደፋ ቀና በሚባልበት በዚህ ወቅት ትኩረታችንን ለማስቀየር ግድቡን ሰበብ የሚያደርጉ አልያም በደፈናው ግዛት እናስመልስ የሚሉ አካላትም ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል። ውሃ ሞልተን እስክንጨርስና በግድቡ ላይ ጉዳት ቢደርስ ጊዜያዊ ተጎጂ የምትሆነው ሱዳን፣ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ተብሎ በግዛታችን እንድትፏልል ሊፈቀድላትም እንደማይገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ግብጽንም ሆነ ሱዳንን ለውስጥ ችግሮቻችን በመላ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ የቤት ሥራ እንዳይሰጡ ማድረግ የእኛው ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝበን፤ እነሱን ሰበብ ማድረጋችንን ማቆም አለብን። እነሱን ማንም ይደግፋቸው፣ ከእኛ ጎን የሚሰለፍ አንድም የውጭ ኃይል ባይኖርም ጠላቶቻችንን በየተራም ሆነ በተናጥል አንድ ላይ የምናስወግድበት መንገድ የራስ ጥንካሬ መሆኑን ልንረዳ ያስፈልጋል።

በአነስተኛ የአሰብ አካባቢ መሬት ግዢ ጀምራ እየተስፋፋች ምጽዋና አስመራ ይገቡኛል ብላ አቅማችን በደከመበት ወቅት አለሳልሳ አጠቃላይ የወረራ ዘመቻ ካካሄደችው ጣሊያን መማር ይገባል። “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” ብላ ዛፉ የበቀለበትንም መሬት ቆርጣ ለመውሰድ ቡራ ከረዩ ማለት የጀመረችው ሱዳን፣ ኢትዮጵያን የናቀችበትን ምክንያት በግልጽ ልንወያይበት ይገባል።

የተጣሉ ባለሥልጣኖቿን ለማስታረቅ ደፋ ቀና ያሉት የኢትዮጵያ ልዑካን ሥራቸው ፍሬ አፍርቶ ያጎረሱበት እጃቸው ተነክሶ እሪታቸውንም ለማሰማት ሳይችሉ ውጠው ይዘውታል። ሕመሙ የጠናባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ኹለት ዓመት ሙሉ መሬታቸውን ማረስ ሳይችሉ ከመቅረታቸው ባሻገር፣ አሁን ባሉበትም እንዳይቆዩ በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጥቃት ሲከፈትባቸው ነበር። ይህ እንደ ሕዝብ ሊያስቆጣን ሲገባ፣ እሷ የከሰሰችውን በማስተባበል በእሷ አጀንዳ ከመጓዝ መቆጠብ እንዳለብን አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች