አብን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ጠየቀ

0
1327

ዕረቡ ሰኔ 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊ ጉዳይ እና የድርጅቱ ቀጣይ የትግል አቅጣጫን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ጠይቋል።

በመግለጫውም በምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ አሰቃቂ ጥቃት ተፈፅሟል ያለው አብን፤ ይህ ጥቃት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲፈፀም አዲስ አይደለም፤ ይልቁንስ የተሳሳተው ትርክት አንዱ ቅርንጫፍ ነው ብሏል።

አማራ ጠል ትርክት ከውጭም ከውስጥም ጠላት አፍርቶልናል እናም በዚህ ደግሞ እየተጎዳ ያለው ምስኪን ራሱን መከላከል የማይችል ሕዝብ ነው፤ የአሁኑን ጨምሮ ተከታታይ ችግሮችን ለማስቆም የሚመለከታቸው ኹሉ ሊያስቆሙት ይገባል ሲሉም የንቅናቄው ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

በአማራ ሕዝብ ላይ እየተደረገ ያለውን ዘር የማጥፋት ጥቃት የሚመለከታቸው ኹሉ ሊያስቆሙት ይገባል ሲሉ ያሳሰቡት ዶክተር በለጠ፤ ንቅናቄው በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ስልታዊ ዘር ማጥፋት ነው ብሎ እንደሚያምንም በመግለጫቸው ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብ ተከታታይ ግድያ ግድ ሊለው የሚገባው የመንግስት መዋቅር ችላ ማለቱን እንዲያቆም እና ባስቸኳይ ሕዝብን እንዲጠብቅ ሲልም አብን አሳስቧል።

ጥቃቱን እየተከታተለ እርምጃ ያልወሰደው መንግስት ይህንን ጥቃት እየሸፈኑ ያሉ እንዲሁም ሕዝብን መጠበቅ ያለባቸው ከክልል እስከ ፌደራል ቢሮዎች ተጠያቂ ናቸው ሲልም ፓርቲው አስታውቋል።

ጥቃቱን ለማስቆም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅና የአካባቢው ነዋሪዎች በፀጥታ አካልነት ተካትተው ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችል ሥራ እንዲሰራም አብን ጠይቋል።

አጥቂዎች በግልፅ ፍርድ እንዲበየንባቸው፤ ይህን ችላ ያሉ፣ እንዲባባሱ ያደረጉ ሚዲያዎች፣ ፓለቲከኞች እና ግለሰቦችን መንግስት ተጠያቂ እንዲያደርግ አብን ጠይቋል።

ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንዲታወጅም ፓርቲው ጠይቋል።

አማራ የመጣበትን ችግር ለመመከት እንደ ሕዝብ በአንድነት ለመመከት አንድነቱን ጠብቆ የመጣውን የዘር ማጥፋት ጥቃት ለመመከት እንዲሠራ አብን ጥሪ ማቅረቡን አሚኮ ዘግቧል።

በቀጣይ ሐሙስ የሀዘን ቀንን ለማሰብ የሻማ ማብራት፣ የፓናል ውይይት እና ሌሎች ዝግጅትን ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም ፓርቲው ገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here