ሐሙስ ሰኔ 30 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዛሬው ዕለት እያካሄደው በሚገኘው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ በርካታ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
በምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል፦
* መንግስት የህዝቦችን ዘላቂ ሰላም ለማስከበርና የሽብር ቡድኖችን ከአገራችን ጨርሶ ለማጥፋት ምን እየሰራ ነው?
* የፌደራል እና የክልል መንግስት ባለስልጣናት የሽብር ቡድኖችን እኩይ ተግባር ቸል ከማለትም በላይ፤ መረጃ የመስጠትና የመደገፍ ሥራ ይሰራሉ የሚባለውን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?
* የክልል መንግስታት በክልላቸው የሚኖሩ ዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻሉ ለምን አይጠየቁም?
* በለውጡ ሥም የገቡ ከላይ እስከታች ያሉ ቀን ቀን መሪ ማታ ማታ አሸባሪ የሆኑ ሰዎች አሉ፤ እነዚህ ሽብርተኞች በፈጸሙት ወንጀል ልክ ምን እርምጃ ተወሰደ፤ ለወደፊቱስ ጭፍጨፋው እንዳይፈጸም ምን ታስቧል?
* በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ከመፈጠሩ በፊት አስቀድሞ መከላከል አይገባም ነበር ወይ? የንጹሀንስ ሞት መቼ ያቆማል? በቀጣይስ እንዳይከሰት መንግስት ምን አቅዷል?
* የሱዳን ወታደራዊ መሪዎችን ዛቻ፣ ትንኮሳና እብሪት መንግስታችን እንዴት ይመለከተዋል?
* አሁንም ድረስ ትህነግ በአገራችን በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ ያለው ስጋት፤ በአሸባሪው ሸኔም ዜጎቻችን እየተጨፈጨፉ ነው፤ መንግስት ኹሉም ሸኔን ተደመሰሰ ይላል፤ ጥቃቱ ግን ቀጥሏል፤ ይሄ ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን ለበርካታ አመታት የተዘራ መሆኑን እንረዳለን፤ የመንግስት ቀዳሚ ስራ ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ ነው፤ ይህ ግን አልሆነም፤ መንግስት የዚህን ዘር ተኮር ጥቃት ማስቆም ያልቻለው ለምንድን ነው፤ የወገኖቻችን ሲቃና መከራ የሚቆመው መቼ ነው፤
* ከትግራይ ህዝቡ በህወሃት ቡድን የሚደርስበትን ጭቆናና ግፍ ለማስቀረት መንግስት ምን እየሰራ ነው? በቀጣይስ የትግራይ ተወላጆችን ለመደገፍ ምን እየተሰራ ነው?
*በቀጣይ ዓመት በኦንላይን ይሰጣል ለተባለዉ አገር አቀፍ ፈተና ይገባሉ የተባሉ 1 ሚሊዮን ታብሌት ኮምፒውተሮች ሂደት ተስተጓጉሏል፤ ለ 2015 ፈተና ለዚህስ መንግስት ምን እያከናወነ ነዉ?
* ከስደት ተመላሽ ዜጎችን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት መንግስት እየሰራ የሚገኘው ሥራ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
* በውጭ አገራት ያሉ ዜጎቻችን መብት እንዲከበር፤ በመላው ዓለም ያላቸው ተፈላጊነት እንዲጨምር ለማድረግ ምን ታስቧል?
* “አሸባሪው ኦነግ ሸኔ በተደጋጋሚ የሚፈፅመውን የሽብር ድርጊቶች ለማውገዝ ዳተኝነት ያሳያሉ ተብለው በበርካታ ኢትዮጲያውያን ዘንድ ይታማሉ። ከፍ ሲል በተከበረው ምክር ቤት አሸባሪው ተብሎ የተፈረጀውን ኦነግ ሸኔን ታጣቂ ሀይል ኢ መደበኛ ብለው ሲጠቅሱ እና የሽብር ቡድኑ የሚፈፅማቸውን ዘር ተኮር ጅምላ ፍጅት ግጭት በማለት ሲጠቅሱ ይስተዋላሉ” በዚህ ላይ ያሎት አስተያየት ምንድን ነው?
* የአገር አቀፍ ፈተናዎች ከትምህርት ምዘና ይልቅ ፖለቲካዊ ቅርጽ እየያዘ አገራዊ አደጋ እየሆነ መጥቷል፤ ፈተናውን ኦንላይን ለመስጠት ምን ታስቧል?
* የአገር መከላከያ ሰራዊት ከአገር አልፎ ለአፍሪካ ኩራት የሆነ የተመሰከረለት ሰራዊት ነው፤ ለዓለም ሰላም ዋጋ ከፍሏል፤ ነገር ግን ዓለም ይሄንን ውለታ ክዷል፤
* ምዕራባዊያን ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጎን ቆመዋል፤ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ገብተዋል፤ ይህ ለምን ይሆናል?
* በሶማሌ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርክ የለምና ምን ታስቧል?
* በአገሪቷ ውስጥ በቅርቡ የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን ለመከላከል የአገሪቷ የደህንነት ተቋም ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ ምን እየሰራ እንደሆነ ማብራሪያ ቢሰጥ?
* በአገራችን ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች ምርጥ ዘር፣ ማደበሪያና የውሃ ፓምፕ እጥረተ አጋጥሟልና ችግሩን ለመፍታት ምን ታስቧል፤
* ከአዋሽ ወደ አፋር ያለው መንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ ምን እየተሰራ ነው?
* በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሄድ ይከለከላል፤ በወጡ ዜጎች ላይም ጥቃት ተፈጽሟል ለምን ይሄ ሆነ? የሚሉና ሌሎችም ወቅታዊና አገራዊ ጥያቄዎች ከም/ቤቱ አባላት ተነስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በአሁኑ ሰዓት ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።





