መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናከጎረቤት አገራት የሚገቡ ምርቶች በየጊዜው እየጨመሩ መሆኑ ተገለጸ

ከጎረቤት አገራት የሚገቡ ምርቶች በየጊዜው እየጨመሩ መሆኑ ተገለጸ

ከጎረቤት አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳዩ መሆኑ ተገለጸ። የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ምርቶቹ በዋናነት ተሽከርካሪዎች፣ ብረታ ብረት፣ መለዋወጫዎች (spare parts)፣ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለአብነትም በ2013 ከአጠቃላይ አገራዊ የገቢ መጠን (import volume) 41 በመቶውን እንደሸፈነ እና መጠኑም 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን እንደሚደርስ አንስተው፣ የባለፈውን ዓመት መጠን ባላስታውሰውም ከዚህ ያነሰ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ መልኩ የሚገቡ ምርቶች አሉታዊ ተፅዕኗቸው የጎላ መሆኑን አንስተውም፣ ለአብነትም ከቻይና በቀጥታ መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ ምርቶች ጅቡቲ ላይ እንዲቆዩ ይደረጋል። ይህም ከጅቡቲ ፍላጎት የመነጨ ሊሆን ይችላል አልያም በተቋሞቻችንና በአስመጭዎች ድክመት ሊሆን ይችላል ካሉ በኋላ፣ በዚህ ግን ዕቃዎች ወደብ ላይ ሲቆዩ የመወረስ ወይም የአገልግሎት ዘመን ማብቃት ሊያጋጥማቸው ይችላል ነው ያሉት።

አገርን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጭ እንደሚዳርግ አመላክተውም፣ አላስፈላጊ ዕቃዎችም በዚሁ መንገድ ከጎረቤት አገራት ወደ ኢትዮጵያ ሊጓጓዙ እንደሚችሉ ነው ያስገነዘቡት።

ይህ የሆነው በዋናነት በተቋማት አለመናበብና ድክመት የተነሳ እንደሆነ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ ይህን የንግድ ስርዓት የሚመሩ ኹሉም ተቋማት ብቁና የተናበቡ ካልሆኑ፣ አንዱ ፈቃድ ሲሰጥ ሌላው የሚያጓትት ከሆነ ችግሩ ይባባሳል ሲሉ ተደምጠዋል።

በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር መሆኗን እንደ ምክንያት ያነሱት ደበሌ፣ ነፃ የንግድ ቀጠና ያላቸው ጎረቤት አገራትም ሌላ ችግር መሆናቸውንና እስከ አሁንም እንደ አገር ነፃ የንግድ ቀጠና እንዳንመሠርት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

አጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱን ለማሳለጥ ጠንካራ የተቋማት ቅንጅት እየተፈጠረ አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ተቋሞቻችን በተለይ በብቃት ማነስ ይህን መቋቋም ሳይችሉ ቀርተዋል ሲሉ አንስተዋል። ጉዳዩ መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ስለሆነም፣ ይህን ችግር በማቃለል በኩል ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የተነገረለት እና ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የተባለው ነፃ የንግድ ቀጠና በኢትዮጵያ ለመመሥረት መታቀዱ ታውቋል።

በዓለም ላይ በርካታ አገራት በዚሁ ዘዴ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን፣ ጎረቤት አገራትም ነፃ የንግድ ቀጠና ስርዓትን ቀድመው በመጀመራቸው ተጠቃሚዎች መሆናቸው ነው የተገለጸው።

በኢትዮጵያም ብሔራዊ የሎጅስቲክስ ካውንስሉ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን (special economic zone) መቋቋም አለበት የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ፣ ይህን ለማስጀመር ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በቅርቡም በድሬዳዋ ከተማ ነፃ የንግድ ቀጠናው ይቋቋማል ተብሏል።

ይህን አስመልክቶ በቅርቡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ውይይት፣ ድሬዳዋ ከተማ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧና ለዘርፉ ካላት መሠረተ ልማት አንጻር መመረጧን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ተናግረዋል።

በዚህም ለጅቡቲ ወደቦች ያላት ቅርበት እንዲሁም በባቡር ትራንስፖርት የተሳሰረች መሆኗ፣ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ በከተማዋ በመኖሩ ብሎም በርካታ ሼዶች ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርክ በመኖሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

እንዲሁም፣ በከተማዋ ያለው ደረቅ ወደብና የገበያ እድል ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው ድሬዳዋ ላይ ተጀምሮ እየሰፋ እንደሚሄድ አንስተዋል።

ነፃ የንግድ ቀጠና (free trade zone) ሲባል ዓለም ዐቀፍ ኩባንያዎች በአንድ ቦታ ላይ ምርቶቻቸውን ለሽያጭ የሚያቀርቡበት ከቀረጥ ነጻ የሆነ የግብይት ስርዓት መሆኑ ተመላክቷል። በዓለም ላይ በበርካታ አገሮች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የነፃ ንግድ ቀጠናዎች እንዳሉ ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች