አማራ ክልል ባለፉት 11 ወራት ከኹለት ቢሊዮን ብር በላይ ከቱሪዝም ገቢ ማግኘቱ ተገለጸ

0
1134
Courtesy Image

የአማራ ክልል ባለፉት 11 ወራት ከ2 ቢሊዮን 182 ሚሊዮን ብር በላይ ከቱሪዝም ማግኘቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ቢሮው እንደገለጸው፣ ባለፈው ዓመት ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ የዘንድሮው ገቢም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት የለውም።

ይህም እስካሁን የተገኘውን ገቢ ሪፖርት ያላደረጉ በጦርነቱ የቆዩ ዞኖች በመኖራቸው ልዩነቱ ተቀራራቢ እንደሆነ ተመላክቷል።

ይሁን እንጂ የተገኘው ገቢ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ገቢ ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያነሰ ነው ማለት እንደሚቻል ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳሙ፣ ከኮሮና ወረርሽኝ እና ከጦርነቱ በፊት የቱሪዝም ዘርፉ በአምስትና ዐስር በመቶ እድገት እንደነበረው በመግለጽ፣ ያን መሠረት አድርገን ብናቅድ ኖሮ ዘንድሮ ያገኘነው ከ50 በመቶ በታች ነበር ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህም ከኹለት ዓመት በፊት በክልሉ የነበረው የአገር ውስጥ የቱሪስት ፍሰት 14 ሚሊዮን ይደርስ እንደነበር አውስተው፣ በዚህ ዓመት ግን ዘጠኝ ሚሊዮን ገደማ ነው ብለዋል።

የውጭ አገር ቱሪስት ፍሰቱም 24 ሺሕ ገደማ ይደርሳል ተብሎ ስምንት ሺሕ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመትም እስካሁን ባለው ከ9 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች በክልሉ ያሉ ወደ 45 የሚደርሱ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንደጎበኙ ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም ስምንት ሺሕ ገደማ ከሚደርስ የውጭ አገር ቱሪስት ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተገኘ አመላክተዋል። ከዓመታዊ የቱሪዝም ገቢው 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን የሚደርሰው ከአገር ውስጥ ቱሪስት የተገኘ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ የውጭ አገር ቱሪስቱ ዝቅተኛ መሆኑን ነው ያሰመሩበት።

ለዚህም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በአገር ደረጃ የነበረውን የፀጥታ ችግር እንደ ምክንያት አንስተው፣ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ይህን ለማስተካከል በሰፊው የማስተዋወቅ ሥራ እንሠራለን ነው ያሉት። በተለይም ለአገር ውስጥ ቱሪስቱ ትልቅ ትኩረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖችና ኹለት የከተማ አስተዳደሮች በጦርነት ውስጥ መቆየታቸውን በማንሳትም፣ ከ91 ያላነሱ ቋሚ ቅርሶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ደግሞ የተዘረፉና የወደሙ መሆኑንም በመግለጽ፣ ሙዚየሞቻችን ላይ ጉዳት ደርሷል ሲሉ አስረድተዋል። በዚህም በደሴ ሙዚየምና መረሆ በሚባለው የአፄ ኃይለሥላሴ ልጅ አልጋ ወራሽ ቤተ መንግሥት ጉዳት እንዳስተናገዱ ነው ያስገነዘቡት።

በተፈጥሮ የመስህብ ሥፍራዎች ላይም ጉዳት መድረሱን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ በሚቀጥለው ዓመት ጉዳት የደረሰባቸውን መስህቦች የተጓደለውን በማሟላት ለቱሪስት ክፍት ለማድረግ እንደሚሠራ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

አዲስ ማለዳ የበጀት ዓመቱን የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገቢ ለማወቅ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ብትጠይቅም ሪፖርት ያልላኩ ክልሎች አሉ መባሉን ተከትሎ ማቅረብ አልተቻለም።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here