ሐሰተኛ የብር ኖት ስርጭት

0
1708

ኢትዮጵያ እንደ መንግሥታት መለዋወጥ ሁሉ የገንዘብ ኖቶቿንና ሳንቲሞቿን ከዚህ ቀደም ባሉ ጊዜያት መቀየሯ የታወቀ ነገር ነገር። አሁን ላይ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው መንግሥትም ከዛሬ አንድ ዓመት ከዐስር ወር በፊት የገንዘብ ኖቶችን ቀይሯል።

የገንዘብ ኖቶች የመቀየራቸው ምክንያት መካከል አንደኛው ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ከመከላከል ጎን ለጎን ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎች እንደሚፈጥር በመታመኑ ነው።

ነገር ግን፣ ሐሰተኛ የብር ኖቶችን የሚያትሙ ግለሰቦች ለማተሚያነት የሚገለገሉባቸውን ማሽኖች ከሌሎች አገራት ወደ ኢትዮጵያ በሚያስገቡበት ወቅት፤ ማሽኖቹ ለምን ዓላማ እንደሚውሉ፣ ወንጀል ሲሠራባቸው ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን ማነው የሚወስደው የሚለው በትኩረት የተጤነ ነው ለማለት አያስደፍርም።

በተጨማሪ እነዛን ማሽኖች አስመጪ አካላት እነማን ናቸው፣ የአስመጪ ፍቃድስ አላቸው ወይ የሚሉ ጉዳዮችን በደንብ ተከታትሎ እርምጃ የሚወስድ አካል ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ግለጽ ነው። ይህንን ተከትሎም ሐሰተኛ የብር ኖቶች ታትመው እየተሰራጩ ኅብረተሰቡን ማደናገራቸው ቀጥሏል። በተለይ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖረውን አርሶ አደሩን እያሳሳቱ መሆኑንም ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል።

አዲሱ የብር ኖት ከተቀየረበት ጊዜ ጀምሮም ቢሆን የብር ኖቶችን በማስመሰል ሕገ ወጥ ሥራ የሚሠሩ እና እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት አሉ። ከእነዚህም በተለያዩ ቦታዎች ኅብረተሰቡን ሲያታልሉ የሚያዙ እና በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉ አሉ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኮምዩኒኬሽን እና የሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እንደገለጹት፣ በመዲናዋ የግለሰብ ቤቶችን በመከራየት ሐሰተኛ የሆኑ የብር ኖቶችን የሚያትሙ ሕገ ወጥ አካላት እንዳሉ ይናገራሉ።

ከዚህ አንፃር በወንጀሉ ላይ ተባባሪ አካላት ያሉ ቢሆንም፣ በወንጀሉ ላይ ብዙ ጊዜ የሚሳተፉት የውጭ አገር ዜጎች እንደሆኑ እና በዚህ ዓይነት መንገድ ወንጀሎች የሚፈፀሙበት ሁኔታ እንዳለ የመረጃ መዝገቦች እንደሚያስረዱ ኃላፊው ጠቁመዋል።

ለአብነት በየካ ክፍለ ከተማ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወንጀሉ በስፋት የሚፈፀምባቸው ናቸው።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ ወንጀሎችን ለመከላከል እየሠራ ሲሆን፣ በቀጣይ ቅድመ ወንጀል መከላከል ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ተነግሯል።

ኃላፊው ወንጀሎችን ለመከላከል እና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከተፈለገ መረጃ በቅድሚያ ሊጎለብት ይገባል ብለዋል። አያይዘውም ወንጀሉን ለመፈፀሚያ ሆቴሎችን የሚያከራዩ፣ ከውጭ አገር መጥተው የተለያዩ ማሽኖችን የሚያስገቡ አካላት በሚያጋጥሙበት ወቅት ፍተሻ በማድረግ እና ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት ኅብረተሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠይቋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርህ ተስፋ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት ሐሰተኛ የብር ኖቶች በሕገ ወጥ አካላት ታትመው የሚሰራጩበት ሁኔታ አለ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል ይላሉ።

አክለውም ሱዳንን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሳይቀር መደበኛ የአገራቸውን መገበያያ ገንዘብ ራሳቸው የሚያትሙበት ሂደት አለ። ኢትዮጵያ ግን በአገር ውስጥ የመገበያያ ገንዘቧን ብር እስከ አሁን ባለው ጊዜ ማተም ያልቻለች ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ለሚያትሙ አካላት መመቻቸት አንድ እድል እንደሚፈጥርላቸው ለአብነት በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል ብለዋል።

መንግሥት ይህን የሐሰተኛ ብር ህትመት ለመከላከል የቁጥጥር ሥራው ላይ በትኩረት መሥራት አለበት ያሉት ባለሙያው፣ መደበኛ የኢትዮጵያ መገበያያ ብርም በአገር ውስጥ እንዲታተም ለማድረግ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው በተጨማሪ ሲያስረዱ፣ ሐሰተኛ ብሩን ለመሥራት የሚያገለግሉ ማሽኖች በሕገ ወጥ መልክ በማስገባት ለሥራው የሚውሉበት ሂደት አለ ብለዋል። ወንጀሉን ለመግታት ከታሰበም የቁጥጥር ሥራው ሊጎለብት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተጨማሪ፣ በሌሎች አገራት የኢትዮጵያ ብር በሐሰተኛ መልክ ተሠርቶ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገባበትም ሂደት ያለ ሲሆን፣ እዚህ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ያስፈልጋል ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓትን በማስፋፋት ረገድ በትኩረት እንዲሠራም መክረዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ያሬድ ኃይለመስቀል በበኩላቸው፣ ሐሰተኛ የብር ኖቶች እየታተሙ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ኅብረተሰቡን እያሳሳቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ለዚህም የቁጥጥር ክፍተት በመኖሩ እና ለሐሰተኛ ብሩ ማተሚያነት የሚያገለግሉ ማሽኖች ከውጭ አገራት በሚገቡበት ወቅት ቁጥጥር ማድረግ፣ እንዲሁም ለምን አገልግሎት አገር ውስጥ እንደሚገቡ ጠይቆ መቆጣጠር ባለመቻሉ ለወንጀሎች መስፋፋት በምክንያትነት እንደሚጠቀስ ያስረዳሉ።

ይህ ዓይነቱ ወንጀል ከደረቅ ወንጀሎች ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፣ ለአብነት ባንክ መዝረፍን ከመሳሰሉ ከሌሎች ተያያዥ ደረቅ ወንጀል ምድብ ውስጥ ይካተታል ይላሉ። ወንጀሉን ለመቆጣጠር የሚያግዝ የፀጥታ ኃይል መዳከምም አንዱ ለወንጀሉ መስፋፋት ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል።

በቀጣይ፣ መንግሥት የዚህን ዓይነት ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ካሰበ በቅድሚያ የፀጥታ ኃይሉን በማጎልበት እና በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ መሥራት እንዳለበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ይናገራሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አክለውም፣ ከላይ የተጠቀሰውን ወንጀል በወቅቱ መቅረፍ ካልተቻለ የማጭበርበር ወንጀሉ ሊስፋፋ የሚችልበት እድል ይጨምራል። ቁጥጥሩን በሚገባ ማጎልበት አስፈላጊ ነው ሲሉ አስምረዉበታል።

የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ሐሰተኛ የብር ኖት ስርጭት፣ ሐሰተኛ የብር ኖት ማተም፣ ይዞ መገኘት እና ለመገበያያ ማዋል በመደበኛ የወንጀል ሕግ ከፍተኛ ቅጣት ያስቀጣል።

የኢትዮጵያ ብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ታትሞ የራሱ የሆነ ቅደም ተከተል ያለው እና ሕጋዊነቱ የተረጋገጠ መሆኑ እየታወቀ፣ በዚያው ልክ ሕጉን ወደ ጎን በመተው ሐሰተኛ የብር ህትመቶችን በማተም የሚያሰራጩ አካላትም እንዳሉ እና በሕግ ቁጥጥር ስር የሚውሉበት ሂደትም እንዳለ የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል።

ከዚህ አኳያ በዚህ የወንጀል ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አካላትን ሕጉ ላይ በሰፈረው አንቀጽ መሠረት ተጠያቂ እንዲሆኑ ከመንግሥት በተጨማሪ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የሕግ ባለሙያው አክለውም፣ ለሐሰተኛ ብር ማተሚያነት የሚያገለግሉ ማሽኖች ከውጭ አገር በሚገቡበት ወቅት የጉምሩክ ኮሚሽን ለምን ዓላማ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ መጠየቅ አለበት ብለዋል። በተጨማሪም አስመጭው ማነው እንዲሁም ማሽኑን ለማስገባት ሕጋዊ ፍቃድ የሰጠው ተቋም ማነው የሚለውን ተመልክቶ ኃላፊነት ወስዶ መሥራት ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ይታያል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች በሚገኙ የድንበር በሮች ላይ የቁጥጥር ሥራውን አጎልብቶ ሊሠራ ይገባል ሲሉም አመላክተዋል።
በተጨማሪ ሐሰተኛ የብር ኖቶችን በማተም ለሚያሰራጩ አካላት ምንም እንኳን ተባባሪ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ሁሉ፣ ብዙ ጊዜ ግን ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በቱሪስት እና በሌሎች ምክንያቶች ወደ አገር ውስጥ የገቡ በዚህ ወንጀል ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን እንዳስተዋሉ የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል።

ለዚህም በወንጀሉ ላይ የሚሳተፉ አካላት በሕግ ቁጥጥሩ ላይ ክፍተቶችንም የሚያጤኑበት ሁኔታ እንደመኖሩ መጠን፣ መንግሥት የቁጥጥር ሥራውን በማጠንከር ሂደቱን መቆጣጠር የሚችልበት ሁኔታ እና ወንጀለኞችንም ተጠያቂ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከኹለት ዐስርት ዓመታት በላይ ስትገለገልባቸው የነበሩ የ10፣ የ50 እና የ100 ብር የገንዘብ ኖቶች ዓይነቶችን ሙሉ ለሙሉ በመተካት ነበር አዲስ የገንዘብ ኖቶችን የቀየረችው። የተቀየሩ የብር ኖቶች ቀደም ሲል ከነበሩት በተሻለ አጠቃቀም ምቹና ረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ ተደርገው ነው የተሠሩት ተብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ኖቶችን አስመስለው የሚሠሩ ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ለመከላከልና ለመለየት በሚያስችል ሁኔታ የተለያዩ የደኅንነት መጠበቂያ ገጽታዎች እንዲኖሯቸው ተደርጓል ማለቱም አይዘነጋም።

ለዐይነ ስውራንም የእውቅና ምልክት ያላቸው ሲሆን የብሩን ዋጋ በእጅ ዳሰሳ ማወቅ የሚችሉበት የደኅንነት መጠበቂያ ያለው ነው። ለአብነት የ100 ብር እና የ10 ብርን ስንመለከት፤ ገንዘቡ ወደ ላይ ወይንም ወደታች ሲዞር የሚንቀሳቀስ ደማቅ የቀለም ፍንጣቂ የደኅንነት መጠበቂያ ምልክት እንዳለውም ተነግሯል።

እንደ ብሔራዊ ባንክ ገለጻ ከሆነ፤ ገንዘቦች የሚሽከረከር ደማቅ ቀለም ኮኮብ አዲስ የደኅንነት መጠበቂያ ክር፤ በክሩ ውስጥም NBET፣ ኢብባ እና የገንዘቡ መጠን ተፅፎ ይገኝበታል ነው ያለው።

ገንዘቡ ወደ ብርሃን አቅጣጫ ተደርጎ ሲታይ በላይ ከሚገኘው ምስል ፊት ለፊት ተመሳሳይ ደብዛዛ ውሃ መልክ ያለው ምልክት እንደሚታይ ተጠቁሟል።

የብር ኖቶቹ በብርሃን አቅጣጫ ሲታዩ ኳስ መሳይ ምልክት ከኖቶቹ በስተኋላ ካለው ተመሳሳይ ምልክት ጋር በፍፁም ትይዩ ሆነው በአንድ ቦታ ላይ ያርፋሉ ይላል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here