መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየእናቱን ሸክም ወደራሱ ያዞረው ተመራቂ

የእናቱን ሸክም ወደራሱ ያዞረው ተመራቂ

ባለፈው ሳምንት መነጋገሪያ ከነበሩ አንኳር ጉዳዮች መካከል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ወጣትን የሚመለከተው አንዱ ነው። ይህ ወጣት የሰው አፍ ውስጥ የገባው ክፉ ሠርቶ ሳይሆን የሚያስመሰግነውን ምግባር በገሐድ በማሳየቱ ነበር።

የምርቃቱ እለት ጋውኑን ከነቆቡ ለእናቱ አልብሶ እሱ የሥራ ቱታ ለብሶ ከጀርባው እርጥብ የእንጨት ጨፈቃዎችን ከነቅጠላቸው አስሮ በጀርባው ተሸክሞ ነበር የታየው። የእንጨት ሸክም አዝሎ ዩኒቨርሲቲው ግቢ መግባት ተከልክሎ ይሁን አይሁን ባይታወቅም፣ በራፉ ላይ ከእናቱ ጎን ሁኖ የተነሳውን ምስል ብዙዎች ዐይተውት እየተቀባበሉት ውለዋል። ከብዙዎች አድናቆት ሲጎርፍለት ውሎ ያደረው ተመራቂ፣ የእናቱን ልፋት ለማሳየት ብቻ ሳይሆን ከእንግዲህ እኔ ነኝ የምደክምልሽ የሚል መልዕክቱን ለማስተላለፍና ሌሎችን ለማስተማር የወሰደውን እርምጃ ብዙዎች ደግፈውለት ነበር።

የወጣቱ ተግባር የሚያስመሰግን መሆኑን የተመለከቱና በአጭር ጊዜ የናኘ ዝናውን ተረድተው ሊጠቀሙበት የፈለጉ ግን፣ በድጋፍ አሳበው ወደ ተመራቂው ለመቅረብ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። “ማንነቱን አጣርተን እንነግራችኋለን” የሚሉና “አገኘነው” የሚሉ የማኅበራዊ ሚዲያና የግለሰቦች እሽቅድምድምም ወዲያው ነበር የተከተለው። ይህ የግለሰቦች ለጋሽነትም ሆነ ልታይ ባይነት ሳይበቃ በጉዳዩ ላይ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ለመግባት ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር።

ዝናውን ለመቋደስ ብለው መልካም ቢያደርጉ አትቅኑ እያሉ ሂደቱን ከትችት ለማፅዳት የሞከሩ ቢኖሩም፣ ጣልቃ ገብነቱን በማስረጃና በምክንያታዊነት አንተርሰው የተቹ ስለነበሩም ለቀናት ሳይሳካላቸው ዘልቋል። የአዲስ አበባ አስተዳደር ስንት ጠባቂና ቆጣቢ ያለበትንና ውዝግብ ያልተለየውን የኮንዶሚንየም ቤት እንደግል ሀብቱ መዥርጦ ለዚህ ለምስጉን ተመራቂ ሲሰጥ ሕዝብ እንዲያይ ለማድረግ ሚዲያዎች ጭምር ግብረ አበር ሆነው ተባብረው ነበር።

የልጁ ደስታ ላይ ውሃ መቸለስን ብዙዎች ባይፈልጉም፣ ሂደቱ ተገቢ ነው ወይ በማለት የአስተዳደሩን ባህሪ በግላጭ የሚያሳይ መሆኑን የተናገሩም ነበሩ። ወጣቱ አልቀበልም ማለት አይጠበቅበትም፣ ነገር ግን ሳይጠይቅ የሰጡት ሊወገዙ ይገባል ሲሉ ብዙዎች የሂደቱን ኢ-ፍትሐዊነት ለማሳየት ሞክረዋል።

ይህ ሂደት ሳይቋጭ ኢንሳ የተባለው ተቋም ደግሞ፣ ሰላይ ይሁን የተቋሙ ባለሙያ ሊያደርገው አስቦ እንደሆነ ባይዘረዘርም፣ ፈልጉልኝ ያላለውን ሥራ ሰጠሁ ብሎ በሚዲያ ቢያስነግርም፣ ተመራቂው ወጣት የራሴ ምኞት ስላለኝ አልቀበልም ማለቱን ብዙዎች አስተያየት ሰጥተውበታል።

በሌላ በኩል፣ ተመራቂው ወጣት ከዚህ በፊት የተመረቀ መሆኑን የሚያሳይ ፎቶ ለጥፈው እንደአዲስ የተመረቀ አስመስሎ ሸቀለበት በሚል ሊተቹ የሞከሩም ነበሩ። 100 ጊዜ ቢመረቅም የእናትን መከራ ለማሳየት በመሞከሩ ሊመሰገን እንጂ ሊወቀስ አይገባም በማለት ምንም ሳይጠይቅ እንደተደረገለት ያተቱም ነበሩ። ‹እናቱ ቅጠል ተሸክመው አያውቁም፤ ለትወና የተደረገ ነው› ያሉ ቢኖሩም፣ የሌላን እናትን መከራ ማሳየቱስ ቢሆን ምን ያስተቸዋል ያሉ አሉ።

ከዚህ ቀደም ከግል ተቋም ተመርቆ ጋውን ከለበሰበት ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ እንዴት ከመንግሥት ተቋም በሌላ ዲግሪ መመረቅ ቻለ ብለው የጠየቁ ቢኖሩም፣ ወጣቱ በ2012 በተመረቀበት ሙያው ባንክ ውስጥ እያገለገለ መሆኑንም በመጥቀስ ሕይወቱን ለአደባባይ አብቅተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች