ትምህርት ሚኒስቴር ‹የጭቆና አሠራር በመፍጠሩ› ቅሬታ እንዳደረባቸው የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት ባለሙያዎች/መምህራን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
አካዳሚክ መምህራን ስታፍና የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት ባለሙያዎች በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ትምህርትን በንድፈ ሐሳብ ከማስተማር ባለፈ በተግባር እና በምርመራ እንዲሰጡ በአዋጅ መጽደቁ የሚታወቅ ሲሆን፤ አዋጁ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እየተከናወነ ባለመሆኑ ዘርፍ ብዙ ጉዳት አስከትሏል የሚል ቅሬታ እየተነሳ ነው።
ቅሬታው የተነሳው የቀድሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 2፣ 3፣ 30 (1/ለ) እና አንቀጽ 42 (1/መ)፤ በአሁኑ አዋጅ ቁጥር 1152/2011 አንቀጽ 2 (13)፣ 35 (1 እና 2) ተገን በመደረጉ፤ ከአካዳሚክ መምህራን ስታፍ ጋር እኩል ተግባርና ኃላፊነት ያላቸው የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት መምህራን አስተዳደራዊ የመዋቅር በደል፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ የጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም ፍትሐዊ ባልሆነ የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም አከፋፈል ላይ መሠረታዊ ችግር እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
ለዘርፈ ብዙ ችግሮች መከሰት አዋጁ ላይ ‹ኹለት ዋና ዋና ሴራዎች ስለተሠሩ› ነው ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ የአዋጅ ቁጥር 1152/2011 አንቀጽ 2(17)ን “የአካዳሚ ቴክኒካል ረዳት “ባለሙያዎች”/መምህራን ማለት የመማር ማስተማርን፤ ምርምርና አገልግሎት ሥራ በሙያው ለማገዝ የተቀጠረ ሠራተኛ ነው” በማለት በራሱ ትርጉም እንደሰጠው ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት መምህራን ከአካዳሚክ ስታፍ ጋር ተመሳሳይ ተግባር እና ኃላፊነት ኖሯቸው ሳለ፤ ቀጥተኛ ተሳትፎው “ማገዝ ወይም መርዳት” በሚል ትርጓሜ ተቀይሮ ሠራተኛው በአካዳሚክ ተግባርና ኃላፊነት ላይ ያለውን ቀጥተኛ ተሳትፎ በመደበቅ እውቅና እንዲነፈግ ተደርጎበታል ብለዋል።
በኹለተኛ ደረጃ፤ አዋጅ ቁጥር 1152/2011 አንቀጽ 35(1) “የመንግሥት ተቋማት የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት መምህራን ቅጥር፤ አስተዳዳር እና ጥቅማጥቅም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ የሚወሰን ይሆናል” ተብሎ መደንገጉን አስታውሰው፤ ነገር ግን የአካዳሚክ ረዳት መምህራኑ የሥራ መደብ መመሪያና መዋቅር እንዳይኖር በማድረግ ነገሮችን በግለሰቦች በጎ ፈቃድ እንዲሰሩ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በአዋጅ ቁጥር 1152/2011 ላይ የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት መምህራን ምንነት በማሳጣት፤ ክብርና እውቅና በመንፈግ እንዲሁም የሥራ መደብ መመሪያና መዋቅር በማድረግ በግለሰቦች በጎ ፍቃድ እንዲገዙ ተደርገው የተሠሩ ‹ሴራዎች› በኹለንተናዊ መብታቸው ላይ ጥስት እንዳስከተሉባቸው ነው የተናገሩት።
በመሆኑም፤ የአካዳሚ ቴክኒካል ረዳት ባለሙያዎች የሥራ ደንብ/መምሪያ በአዋጁ አንቀጽ 35(1) እንደተመለከተው፣ እንዲሁም በአሠሪና ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 2(6) ላይ በተደነገገው መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ መምህራኑ ጠይቀዋል።
እንዲሁም፤ የአደጋ ኢንሹራንስ አበል፤ ነፃ ሕክምና፤ አደጋ መከላከያ ዕቃዎችን የማግኘት መብት በአዋጁ መሠረት እንዲከበርላቸው፤ የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት መምህራን ‹አካዳሚክ ቴክኒካል ኢንስትራክተር› በሚል ሥያሜ እንዲቀየርላቸው፤ የትምህርት ዕድልና አጭርና ረጅም ሥልጠናዎችን የማግኘት መብት እንዲከበርላቸውና የጭቆና አሰራር የታየባቸው አንቀጾች ማስተካከያ እንዲደረግባቸው አሳስበዋል።
መምህራኑ ቅሬታቸውን ለሚመለከተው አካል ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ እንዳልተሰጣቸውኑ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ከትምህርት ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሀረጓ ማሞ ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይካተት ቀርቷል።
በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡ ትምህርቶችን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ከማስተማር ባለፈ ተግባርና ምርመራ ተኮር በሆነ መልኩ ለማስተማር ሌክቸረሮች፤ የአካዳሚክ መምህራን ስታፍ እና የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያዎች በመባል በኹለት ተከፍለው በተሰጣቸው ኃላፊነት አገልግሎት እንዲሰጡ አዋጅ ቁጥር 1152/2011 አንቀጽ 28(1 እና 2) ይደነግጋል።
በአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳትነት እንዲያገለግሉ ኃላፊነት የተሰጣቸው በኢትዮጵያ በሚገኙ 45 ዩኒቨርሲቲዎች የተሰማሩ ከአምስት ሺሕ በላይ መምህራን መኖራቸው ተመላክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014



