በኢትዮጵያ ያሉ የዐይን ንቅለ ተከላ ሐኪሞች 8 ብቻ ናቸው
በኢትዮጵያ የዐይን ንቅለ ተከላ ከሚጠብቁ 300 ሺሕ በላይ ሰዎች ውስጥ እስከ አሁን ለ2 ሺሕ 824 ሰዎች ብቻ ንቅለ ተከላ የተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ዐይን ባንክ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ባንኩ ከ14 ዓመታት በፊት በተጠና ጥናት በኢትዮጵያ በዐይን በሽታ በመጠቃታቸው ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ከ300 ሺሕ በላይ ሰዎች ያሉ መሆኑ ቢታወቅም፣ እስካሁን ግን በጣም ዝቅተኛ የዐይን ብሌን ለጋሽ በመኖሩ ንቅለ ተከላው ለጥቂቶች ብቻ መሰጠቱን አመላክቷል።
በዚህም አሁን ላይ ጥናት ቢደረግ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የዐይን ንቅለ ተከላ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የለጋሾች ቁጥር በጣም አነስተኛ በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል መሥራት አልቻልኩም ነው ያለው።
የኢትዮጵያ ዐይን ባንክ የግንዛቤ ማስጨበጫ አስተባባሪ ነጋ ደምሴ፣ የዐይን ንቅለ ተከላ የሚጠብቁ ሰዎችና የለጋሾች ቁጥር እጅግ በጣም የተራራቀ ነው ሲሉ ገልጸዋል። በጥናት ከታወቀው ከ300 ሺሕ በላይ ታማሚዎች እስከ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ለ2 ሺሕ 824 ሰዎች ብቻ ነው ንቅለ ተከላ የተካሄደው ብለዋል።
በዚህ ዓመትም ከጥር ወር ጀምሮ እስካሁን 90 ለሚደርሱ ሰዎች ብቻ ንቅለ ተከላ መከናወኑንና የተለገሰው ይህን ያህል መሆኑን ያነሱት አስተባባሪው፣ ይህም የሆነው የለጋሾች ቁጥር አናሳ መሆኑን ተከትሎ ነው ብለዋል።
ባንኩ በሦስት መንገድ የዐይን ብሌን እንደሚሰበስብ በመግለጽም፣ የመጀመሪያው ፍቃደኛ የስልክ ጥሪ ሲሆን፣ ይህም አስቀድመው ቃል የገቡ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ኑዛዜያቸውን በቤተሰቦቻቸው ደውለው ተፈጻሚ የሚሆንበት መንገድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኹለተኛውም ፈቃደኛ የስልክ ጥሪ ሆኖ፣ ለጋሹ አካል ስለ ዐይን ባንክ ግንዛቤ ኖሯቸው ቃል ሳይገቡ ቢያርፉ፣ በቤተሰቦቻቸው ፍቃድ አማካኝነት ልገሳ የሚደረግበት ዘዴ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሦስተኛው ሆስፒታልን መሠረት ያደረገ የዐይን ብሌን ስብሰባ መርሃ ግብር ሲሆን፣ ይህም ለጋሾች አስቀድመው በግንዛቤ ማነስ ወይም ቃል የሚገባበት ማዕከልም አዲስ አበባ ብቻ በመሆኑ በቦታና ጊዜ አለመመቻቸት ቃል ሳይገቡ በሆስፒታል ቢያርፉ፣ የዐይን ባንክ አማካሪዎችን በመላክ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመመካከር ፈቃደኛ ከሆኑ የሚፈጸም የዐይን ብሌን ልገሳ መሆኑን አስረድተዋል። ይህንንም ለጊዜው እየተሠራ ያለው በጥቁር አንበሳ፣ ቅዱስ ጳውሎስና ራስ ደስታ ሆስፒታል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አስተባባሪው ስለ ዐይን ባንክ ማኅበረሰቡ ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው ካሉ በኋላም፣ ‹‹አብዛኛው ሰው ሙሉ ዐይኑ የሚነሳ ነው የሚመስለው። ይሁን እንጂ ብሌኑ ከተነሳ በኋላ ለባለሙያ ካልሆነ በስተቀር መነሳቱ አይታወቅም›› ነው ያሉት።
የሚለገሰው እጅግ ስስ የሆነ ጥፍር የሚያህል መስታወት ነው፤ ይህም የሰውን ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ የሚለውጥ በመሆኑ፣ ሰዎች ከሞቱ ከሦስት ቀን በኋላ የሚፈሰውንና ለአፈር የሚሆነውን ዐይናቸውን ለወገናቸው እንዲለግሱ ሲሉ አሳስበዋል።
የንቅለ ተከላ ማእከላትና የሐኪሞች ቁጥር ቢጨምር፣ እንዲሁም ብዙ ለጋሾች ቢኖሩ ኹሉም የታመመ ሰው ዐይኑን መሠራት ይፈልጋል ያሉት አስተባባሪው፣ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ያሉት የዐይን ንቅለ ተከላ ሐኪሞች ስምንት ብቻ ናቸው ብለዋል።
ከእነዚህም ባለሙያዎች በክፍለ አገር የንቅለ ተከላ ማእከል በሆኑት በጅማ፣ ጎንደር እና ሐዋሳ ካሉት በስተቀር ሌሎች አዲስ አበባ የሚገኙ ሲሆን፣ በመማር ላይ ያሉ ባለሙያዎች በመኖራቸው ወደፊት ቁጥራቸው ይጨምራል ነው ያሉት።
ይህም የሆነው ኹሉም የዐይን ሐኪም የንቅለ ተከላ ሐኪም መሆን ስለማይችል፣ ትምህርቱ ልዩ ሥልጠና የሚፈልግና በውጭ አገር የሚሰጥ፣ ‹‹sub specialty›› ኢትዮጵያ ውስጥ የማይሰጥ በመሆኑ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ስለሆነም፣ የዐይን ባንኩ ዋና ኃላፊነት የዐይን ብሌን መሰብሰብ፣ ጥራትና ጤንነቱን ማረጋገጥ፣ ወደ ንቅለ ተከላ ማእከላት ማሰራጨት፣ ያሰራጨውንም መቆጣጣር ሲሆን የንቅለ ተከላ ማእከላትንና ባለሙያዎችን ማብዛት የሆስፒታሎች ተቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል።
የዐይን ባንኩ ወደ ክልሎችም በመሄድ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለመሥራት ቢያስብም፣ በፋይናንስ ችግር ምክንያት ይህን ማድረግ ባለመቻሉ ዋና ዋና ተግባራትን አስቀድሞ እየከወነ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ዐይን ባንክ ለማኅበረሰብ ከሚሰጠው አገልግሎት የተነሳ በፈረንጆች 2020 በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተፅዕኖ ፈጣሪ አሸናፊ እንደነበርም ይታወሳል።
ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014



