ግልጽ ደብዳቤ ለኢ/ር ታከለ ኡማ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ከመዲናዋ ግፉአን ወጣቶች

0
1131

ጉዳዩ፡- ተዘዋዋሪ ፈንዱ በጭንቀት ሳያፈነዳን በፊት ድረሱልን የሚሉ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ሴቶች የኡኡታ ድምጽ!

ክቡር ከንቲባ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ እንድጽፍልዎ እና በቀጥታ በጋዜጣ ላይ እንዲወጣ መነሻ የሆነኝን ምክንያት እንዲህ ነው። ባለፈው እሁድ፣ መስከረም 18/2012 ጠዋት እኔና ባለቤቴ እቤት ሆነን ቁርስ እየተመገብን ሳለ በራችን ተንኳኳ። ሠራተኛችን ፈጥና ከፈተች። ኹለት ወጣቶች ናቸው፤ ሴት እና ወንድ። ፊታቸው ለእኔ እንግዳ ባይሆንም ላስታውሳቸው አልቻልኩም። ግቡ አልናቸው። አይሆንም ብለው አንገራገሩ። አንዴ ልናናግርዎ ፈልገን ነው አሉ ወደ እኔ እየተመለከቱ እና ፈራ ተባ እያሉ። እኮ ግቡና አናግራችኋለሁ። በሉ የደረሳችሁት ቁርስ ላይ ነውና አብራችሁን ቅረቡ አልናቸው። ቢግደረደሩም እንደምንም አብረውን ገበታ እንዲቋደሱ አደረግን። ከዛም የማን ልጆች እንደሆኑ እና ለምን እንደፈለጉን አጫወቱን።

ልጆቹ የጎረቤቶቻችን ልጆች ናቸው። ጉዳዩን በአጭሩ ለመግለፅ ልጆቹ ወደ እኛ የመጡት ብድር ፍለጋ ነው። የያዟቸውን ሰነዶች እያመለከቱ ነገር ግን ከፍርሃታቸው የተነሳ ንግግራቸው እየተቆራረጠ እና እንባ እየተናነቃቸው ነበር ያናገሩን።

ልጆቹ የወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድን ለመጠቀም ወረዳችን አደራጅቷቸዋል። በአንድ ሰፈር የሚኖሩና የሚተዋወቅ እነዚህ ወጣቶች ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ነበር አምስት ሆነው የተደራጁት። የወረዳው ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ሲያደራጃቸው ለማምረቻ የሚጠቀሙበትን የመሥርያ ቦታ እንዲፈልጉ እና አዲስ ብድር ተቋም ከሚፈቀድላቸው ብድር ላይ የስድስት ወር የቤት ክራይ እንደሚከፍልላቸው ይነግሯቸዋል። እነርሱም ወረዳው ያዘጋጀላቸውን መመስረቻ ጽሑፍ እና መተዳደርያ ደንብ ውልና ማስረጃ ወስደው በማፀደቅ የሽርክና ማኅበሩን አቋቋሙ።

ቀጥሎም የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (Tax Identification Number-TIN) አወጡ። እነዚህን ሕጋዊ ሰነዶች ይዘው ወደ ወረዳው ተመለሱ። ዋና ምዝገባ እና ንግድ ፍቃድ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ይሁንና ግን ዋና ምዝገባውን ከጨረሱላቸው በኋላ ንግድ ፍቃዱን የምታወጡት የክራይ ውል ስታመጡ ነው አሏቸው። ወደ አዲስ ብድር ላኳቸው። ቤቱን ፈልገው ማግኘታቸውን ተናገሩ። ከዚህ ቀደም በተገባልን ቃል መሰረት ክፍያውን ለአከራዩ ፈጽሙ እና የኪራይ ውሉን ንግድ ፍቃድ እናውጣበት አሉ። አበዳሪው ተቋም የሰጣቸው ምላሽ ግን ያልጠበቁት እና ግራ የሚያጋባ ነበር። ንግድ ፈቃድ ሳታወጡ የብድሩን ሒደት መጀመር አትችሉም ብሏቸው እርፍ አለ። ደነገጡ። እንዲህ እንዲያ ብላችሁን ነበር እኮ ቢሉም የሚሰማቸው አጡ። ከወዳጅ ዘመድ ተበድራችሁ ተከራዩ እና ብድሩ ሲለቀቅላችሁ ትመልሳላችሁ ሆነ የመጨረሻ መልሳቸው።

የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር እና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ጭምር ሲጓጉ የነበሩት እነዚህ ወጣቶች ሌላ ያልጠበቁት ደንቃራ ገጠማቸው። ብድር ፍለጋ የወደጅ ዘመዶቻቸውን ደጅ ጠኑ። የቅርብ እና የሩቅ ቤተሰቦቻቸውን ለምነው እና አስቸግረው በብድር ያገኙት ገንዘብ ግማሹን ያህል ብቻ ሆነ። እነርሱ ደግሞ ያገኙት ለማምረቻ የሚሆን በወር ዐሥር ሺሕ ብር የሚከፈልበት ቤት ነበር። በዛ ላይ አከራዩ የስድስት ወር ቅድምያ ካልከፈላችሁ አላከራይም ብሏቸዋል። አሁን ያላቸው አማራጭ እንደምንም ብለው አከራዩን በማሳመን የሦስት ወር ከፍለው መከራየት ነው። እናም ችግራቸውን በማስረዳት እና ለምን ሥራ እንደፈለጉት በመግለጽ በብዙ ልምምጥ አሳምነው የሦስት ወር ቅድምያ ክፍያ 30 ሺሕ /ሰላሳ ሺሕ ብር/ ከፍለው ውል ተዋዋሉ። ቤቱንም ከነጊቢው ተከራዩ።

ውላቸውን ይዘው ወደ ወረዳው የአንድ ማዕከል አገልግሎት አቀኑ። መጀመርያውኑ ንግድ ፍቃድ ለማውጣት ምን ምን ማሟላት እንዳለባቸው ያልነገሯቸው ሰዎች አሁን ደግሞ የብቃት ማረጋገጫ ካላመጣችሁ ፈቃዱን ልንሰጣችሁ አንችልም የሚል ሆነ ምላሻቸው። ልጆቹ ማረጋገጫውን ፍለጋ ወደ ምግብ እና መድኀኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አቀኑ። በክፍለ ከተማ የሚገኘው ይህ ቢሮ ቤቱ ለተባለው ሥራ መሆን አለመሆኑን ለሚያረጋግጡ ባለ ሙያዎች ትራንስፖርት አቅርቡ አለ። ለደርሶ መልስ ኮንትራት ከፍለው ወስደው አሳዩ። የወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ለማስተዳደር በተዘጋጀው መመርያ መሰረት ብድሩ ተለቆላቸው የማምረቻ መሳሪያዎችን ገዝተው እስኪያሟሉ ድረስ ለሦስት ወር የሚያገለግል እና ወረዳው ንግድ ፍቃድ በትብብር እንዲሰጣቸው ሲል የድጋፍ ደብዳቤ ጻፈላቸው።

ያንን ይዘው ወደ ወረዳው አቀኑ። እዛ ሲደርሱ ግን ንግድ ፈቃድ ሰጭው አካል የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ካላመጣችሁ በቀር በድጋፍ ደብዳቤ አላስተናግዳችሁም አለ። የቅርብ አለቃው የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ኀላፊው ሥራላቸው ቢለው እምቢ አለ። የወረዳው ሥራ አስፈጻሚ ጋር ቅሬታቸውን አቅርበው እርሱም ጠርቶ ቢያዘው አላደርገውም ብሎ ደረቀ። ልጆቹ ወደ ክፍለ ከተማው አቀኑ። ለሥራ አስፈጻሚ ቢሮ ቅሬታቸውን አቀረቡ። ከዛም ወረዳው አልሰጥምያላቸውን ንግድ ፈቃድ ክፍለ ከተማው ሰጣቸው። ተመልሰው ወደ ወረዳው የአዲስ ብድር ተቋም ቅርንጫፍ ሔዱ። የተሟላ ሰነድ አስገቡ። መጥተን እናያለን ትራንስፖርት አቅርቡ አሏቸው። መጥተው አዩ። የብድር መጠየቂያ ቅጽ ሙሉ አሏቸው። ሞሉ። ወደ ክፍለ ከተማው አዲስ ብድር ተቋም ተላከላቸው። ከዚህኛውም ቢሮ የክፍለ ከተማው ብድር ተቋም ተወካዬች በሌላ ቀን መጥተው የተከራዩትን የማምረቻ ቦታ ተመለከቱ።

ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ ደግሞ ሥልጠና ውሰዱ ተባሉ። በክፍለ ከተማቸው በሚገኘው የቴክኒክ እና ሙያ ተቋም ስለ ሥራ ፈጠራ ጥበብ፤ ስለ ገንዘብ አጠቃቀም፤ ስለ ንግዱ ስርዓት እና ስለ ራዕይ የአራት ቀናት ሥልጠና ተከታተሉ። ሰርተፍኬቱ ግን ወዲያው አልተሰጣቸው። ከኹለት ሳምንት በኋላ እንጂ። ኮፒ አድርገው አስገቡ። ከዛ ከወረዳው የአዲስ ብድር ቅርንጫፍ ተደወለላቸውና 300 ሺሕ /ሦስት መቶ ሺሕ/ ብር ጸድቆላችኋል የቀበሌ መታወቅያ ያለው ለእያንዳንዳችሁ ዋስ አምጡና ፈርሙ ተባሉ። የብድር መጠየቅያ ፎርሙ ላይ የሞሉት ግን አንድ ሚሊዮን ብር ነበር። ማሽን መግዧ ፕሮፎርማውን ጭምር አያይዘው ነበር ያስገቡት። ሆኖም እንኳን የጥሬ እቃ መግዣ፤ የሠራተኛ ደሞዝ፤ የቤት ኪራይ እና መሰል ወጪዎችን ጨምሮ ሊሸፍን ቀርቶ የተፈቀደላቸው የገንዘብ መጠን የማምረቻ ማሽኖችን እንኳን ለመግዝት የሚበቃ አልነበረም። እናም ቅሬታቸውን ለወረዳው ተናገሩ። እኛ ጋር ሳይሆን ክፍለ ከተማ ሔዳችሁ ቅሬታችሁን ማቅረብ ትችላላችሁ ተባሉ።

ክፍለ ከተማ ሔዱ። የቅሬታ ፎርም ሞሉ። ውጤቱ ከኹለት ቀናት በኋላ ተነገራቸው። ከዚህ በላይ ልንፈቅድላችሁ አንችልም የሚል ሆነ መልሱ። ግራ ቢገባቸው “ብልህ ልጅ የያዘውን ይዞ ነው የሚያለቅሰው” ብለው እናታቸው በሰጡአቸው ምክር ተበረታተው ወረዳ ሔደው ዋሶቻቸውን አቅርበው ተፈራረሙ። ከዛም የወረዳው ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ አካውንት እንዲከፍቱ ደብዳቤ ጻፈላቸው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ከፈቱ። ቀጥሎም ብሩ እንዲለቀቅላቸው ሐሙስ፣ መስከረም 15 ሲሔዱ ወረዳው አገልግሎት እንደማይሰጥ ነገራቸው። ምክንያቱን ሲጠይቁ ደግሞ በቂ ምላሽ የሚሰጣቸው አላገኙም። ወዲያው ወደ ክፍለ ከተማ አቀኑ። እዚያም ተመሳሳይ ምላሽ ተሰጣቸው። ቢሮው ላይ ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎት አንሰጥም የሚል ድፍን ያለ ማስታወቅያ ተለጥፏል።

በማግስቱ አርብ ተመልሰው ሲሄዱ ማስታወቅያው ተሻሽሎ እስከ ሰኞ፣ መስከረም 26 አገልግሎት አንሰጥም የሚል ቀኑን ከመጥቀስ በቀር ከቀድሞ ምንም የማይለይ ድፍን ያለ ማስታወቅያ ተለጥፏል። ይሁን እንጂ ተቋሙ ያደራጃቸው በርካታ ወጣቶች በረንዳው ላይ እንደ አሸፋ ፈስሰው እና የቢሮው በር ላይ እጅብ ብለው አልሔድ ሲሉ አንዲት ኀላፊ ወጥተው ኦዲት እያደረግን ነው። ገንዘብ አልቋል። ምንም ማድረግ አንችልም የሚል ምላሽ ነበር የሰጧቸው። ይሔኔ አካባቢው በቁጣ እና በጫጫታ ተሞላ። በአቅራቢያ ሕንጻ ውስጥ የነበሩ ፖሊሶች በኀይል በተኗቸው። እንግዲህ ይህንን ውጣ ውረድ ካለፉ እና ይህ ተስፋ አስቆራጭ ምላሽ ከተሰጣቸው በኋላ ነው ወጣቶቹ ወደ እኛ ቤት የመጡት። በሰነድ እያስደገፉ እና ሲቃ እያነቃቸው ግራ መጋባት እየናጣቸው ነበር የሆነውን ሁሉ ለእኔ እና ለባለቤቴ ያጫወቱን።

እንደነገሩን እና በውልና ማስረጃ በፀደቀው የኪራይ ውሉ ላይ እንደሰፈረው ቅድምያ የከፈሉት ገንዘብ የተጠናቀቀው መስከረም 7 ነው። ከዚህም የተነሳ አከራዩ ወርሃዊ ክፍያውን ጠይቋቸዋል። እጃቸው ላይ ደግሞ ዜሮ አምስት ሳንቲም የለም። በዛ ላይ ቀደም ብለው ሰላሳ ሺሕ ብር ያበደሯቸው ሰዎች ገንዘቡን እንከፍላለን ያላችሁበት ጊዜ አልፏልና ክፈሉን ብለው ጠይቀዋቸዋል። እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር አጨናንቋቸው ነው ወደ እኛ የመጡት። የሰፈር ሰው ስለሆንን ምናልባት አንዳንድ ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን የሚያስችላቸውን የተወሰነ ገንዘብ ካገኘን ብለው ብድር ጥየቃ ነው የመጡት።

እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ወረዳው እና ክፍለ ከተማ ያደረገው ነገር እጅግ አሳዝኖን ለጊዜው ልጆቹን አረጋጋናቸው። በማግስቱም አብረን ሔደን ሁኔታውን ካጣራን በኋላ የተወሰነ ድጋፍ እንደምናደርግላቸው ተስፋ ሰጥተን እና አብረውን ቁርስ እንዲበሉ ካደረግን በኋላ አሰናበትናቸው። በቀጣዩ ቀን በቀጠሯችን ቦታ ተገናኘን። በቀጥታ ወረዳ እና ክፍለ ከተማ ሔደን ጉዳዩን ለማጣራት መከርን። ወጣቶቹ የነገሩን ሁሉ እውነት ከመሆኑ ባሻገር የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ድርጊት ደግሞ እጅግ የሚያበሳጭ ሆኖ አገኘሁት። እኔም ሆንኩ ድርጅቴ በሚቀርብልን የድጋፍ ጥያቄ መሰረት በተለያዩ የልማት እና የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ እንሰማራ ስለ ነበር የምኖርበት ወረዳም ሆነ የክፍለ ከተማው ሰዎች ያውቁኛል። እናም በሔድኩበት ጊዜ ጠብ እርግፍ ሲሉ ነበር። በእርግጠኝነት ይህ ሁሉ መሽቆጥቆጥ ከአገልጋይነት መንፈስ የመነጨ እንዳልሆነ ይገባኛል። ያ ቢሆንማ ኖሮ እነዚህን ወጣቶች እና መሰሎቻቸውን ባላንገላቷቸው ነበር።

ከልጆቹ ጋር ወረዳም ሆነ ክፍለ ከተማ ጎራ ባልኩበት ሰዓት ያገኘኋቸው በተለያየ ሥራ ላይ ለመሰማራት የሽርክና ማኅበር ያቋቋሙ ሴቶች እና ወጣቶች ብሶት እና ምሬት ተመሳሳይ ነው። የተወሰኑትንም ለማናገር ሞክሬያለሁ። በማኒፋክቸሪንግ ወይም በከተማ ግብር ለመሰማራት ብለው በርካታ አከራዬች ዋጋ ሲያሶድዱባቸው እና ከሥራ ባሕሪ የተነሳ አናከራይም ሲላቸው አንዳንዶቹ ከወላጆቻቸው ጋር የሚኖበትን ቤት ለሥራ ቸው ለማድረግ እነርሱ ላቋቋሙት ድርጅት ለቤት ክራይ ሊያውሉት በአሰቡት የገንዘብ መጠን ልክ መኖርያ ቤት እስከ መከራየት የደረሱም አሉ። ይህ የራሳቸውን ሥራ ሰርተው ለመለወጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

ይሁንና ግን የወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድን ለማስተዳደር ክፍለ ከተማው ያዘጋጀው ሰነድ ከአፈጻፀሙ ጋር ጨርሶውኑ የሚገናኝ አይደለም። አስገራሚው ነገር ሰነዱ በጥናት ላይ የተመሰረት አለመሆኑን የሚያሳየው መመርያው ከወጣ ከ10 ቀን በኋላ ግንቦት 23/2011 በተጻፈ ደብዳቤ ማሻሻያ መደረጉ ነው። የሚገርመው ይሔው ማሻሻያ ደግሞ ከ7 ቀን በኋላ ግንቦት 30/2011 በተጻፈ ሌላ ደብዳቤ ተሻሽሏል። ኹለት ጊዜ ብቻ ደግሞ እንዳይመስላችሁ ከዚያ በኋላ ከአራት ጊዜ በላይ ተሻሽሏል። በእርግጥ ቢሮክራሲውን ለማሳጠር እና ሥራ ውን ለማቀላጠፍ ማሻሻል መደረጉ ተገቢ ነው። ይሁንና ግን ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚንቀሳቀስበትን እና የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ይቀርፋል የተባለ መመርያን ከስድስት ጊዜ በላይ ማሻሻል ውሳኔው ፖለቲካዊ ከመሆኑ ባሻገር በሙያ እና በጥናት የተደገፈ አለመሆኑን ነው የሚያሳየው።

ለውጡን እየመራ ያለው መንግሥት በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተንሰራፋውን የሥራ አጥ ችግር ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረገ መሆኑን ከማናችንም የተሰወረ አይደለም። የከተማ አስተዳድሩም በአዲስ አበባ የሚገኙ ሥራ ፈላጊዎች የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ይህንን ዕድል ማመቻቸቱ የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን ለሥራ አጥ ወጣቶችም ሆነ ለወላጆቻቸው እፎይታን የሚፈጥር ትልቅ የምሥራች ነው። ይሁንና ግን እኔ እንደተዛብኩት ሒደቱ ውስብስብ እና በችግሮች የተተበተበ ነው። ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ከንቲባው አንድጽፍ ያደረገኝ ይሔው ምክንያት ነው። ለዓመታት እንደተለመደውም ምናልባት ለከንቲባው የሚቀርብላቸው የውሸት ሪፖርት ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት ጭምር አለኝ።

በአንጻሩም እኔ ያለሁበትን ቦሌን ጨምሮ በየካ፤ በአራዳ እና በቂርቆስ ማለትም አራቱ ክፍለ ከተሞች እና በውስጣቸው በሚገኙ በአንዳንድ ወረዳዎቻቸው ያደረኩት ኢ-መደበኛ ዳሰሳዊ ጥናት የችግሩን ስፋት እና ተመሳስሎሽ የሚያመላክት በመሆኑ ምናልባት ለብዙዎች ድምጽ ልሆናቸው እችል ይሆናል ብዬ በማመን ነው ይህችን ጽሑፍ ወደ ኅትመት ሚድያው ይዤ ብቅ ያልኩት። በዚሁ መሰረት ሥራ ብዙ የሆኑት ክቡር ከንቲባውም ሆኑ የሚመለከታቸው የካቢኔ አባላት ቀጣዬቹን ዐበይት ነጥቦች እንዲያጤናቸው ለማሳሰብ እወዳለሁ። እኔ እንደ አንድ ዜጋ ቤቴ ድረስ መጥተው ብድር ለጠየቁኝ ወጣቶች ጊዜያዊ እፎይታ እንዲያገኙ በሚል ወደ አርባ ሺሕ ብር አካባቢ ሰጥቻቸዋለሁ። ይሁንና ግን በየወረዳው ያለው የተዝረከረከ፤ ግልጽነት የሚጎለው፤ የተንዛዛ እና ቀርፋፋ አሰራር ካልተወገደ በቀር እነዚህን ወጣቶች ጨምሮ ሌሎቹም ተስፋ ቆርጠው በአንድ በኩል በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ተሰደው ወጥተው ወገኖቻችን እንዳይጎዱ በሌላ በኩል የለውጡ እንቅፋት የሚሆን ነውጥ እንዳያስነሱ ለማሳሰብ ያህል ደግሞ ይህችን ደብዳቤ ጽፌያለሁ።

ይሁንና እንጂ የማስቀድመው ምስጋና እና አድናቆቴን ነው። እንደሚታወቀው እርስዎ የሚመሯት እኛም የምንኖርባት አዲስ አበባችን በበርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች የተተበተበች ናት። እነዚህ ችግሮች ዘርፈ ብዙ እና የተወሳሰቡ ከመሆናቸው ባሻገር በአጭር ጊዜ እና በቀላሉ የማይፈቱ እንደሆኑም ከማንም የተሰወረ አይደለም። እርስዎም አሁን ወደ አሉበት ኀላፊነት ከመጡ በኋላ ባለፉት ዐሥራ ሦስት ወራት እነዚህን የከተማይቱን ሥር የሰደዱ እና ለዓመታት ሲንከባለሉ የቆዬ ችግሮችን ለመፍታት ነዋሪዎቿን፤ ባለሐብቶችን እና የልማት አጋሮችን በማስተባበር ለውጥ ለማምጣት ብርቱ ጥረት እያረጉ መሆኑን በቅርበት አውቃለሁ። በዚህ አጋጣሚም እነዚህን አበይት ችግሮች በመለየት እንደ ክብደታቸው እና አንገብጋቢነታቸው መጠን ተራ በተራ ለመቅረፍ የሚያደርጉትን እልህ አስጨራሽ ጥረት ማድነቅ እፈልጋለሁ።

ክቡርነትዎ አሁን ባሉበት ኀላፊነት በቆዩባቸው ጊዜያት በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን በማስለቀቅ ለአቅመ ደካሞች እና ለአካል ጉዳተኞች በመስጠት፤ በጎፈቃደኞችን በማስተባበር የአቅመ ደካሞችን ቤት የመጠገን፤ በየወሩ መደበኛ የጽዳት ዘመቻ በማከናወን፤ በሊዝ ተወስደውም ሆነ አለአግባብ በሕገወጥ መንገድ ታጥረው የተቀመጡ ሰፋፊ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ በማስመለስ፤ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ዓርማ የሆነውን የአድዋ ሙዚየም እና ብሔራዊ ቤተመጽሐፍት ግንባታ በማስጀመር፤ በዐሥሩም ክፍለ ከተማ ከሚገኙ አዲስ አበቤዎች እና ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በልማት ሰበብ ከተፈናቀሉ ነዋሪዎች ጋር በመወያየት፤ አዲስ ለሚገነቡ የጋራ መኖርያ እና የማኅበር ቤቶች የሚገነቡባቸውን ቦታ በማዘጋጀት፤ በጎ አድራጊዎች በማስተባበር በከተማዋ የሚገኙ የሕዝብ ት/ቤቶችን ከማሳደስ ባሻገር በእነዚህ የመንግሥት ት/ቤቶች ለሚማሩ ከስድስት መቶ ሺሕ ለሚልቁ ተማሪዎች የመማርያ ቁሳቁሶችን እና የደንብ ልብሶችን በማዘጋጀት የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻልም ሆነ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር ከሥራ ባልደረቦችዎ ጋር በትጋት እየሠሩ መሆኑ ይታወቃል።

አስተዳደርዎ እነዚህን እና መሰል ተግባራትን በማከናወኑ የሚመገሰውን ያህል በተቃራኒው የሚወቀስበት ጉዳዮች መኖራቸውም አይካድም። በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ኮዬፈጬ የተገነቡ የጋራ መኖርያ ቤት ዕጣ የወጣላቸው ዜጎች እስከ ዛሬ ድረስ ቤቱን እንዲረከቡ አለመደረጉ እርስዎም ሆኑ የሾመዎ ኢሕአዴግ የሚወቀስበት ኢ-ፍትሐዊ ተግባር ነው። ምን ያህል እውነት እንደሆነ ከገለልተኛ ወገን ገና ማረጋገጫ ባይገኝለትም በአስተዳደርዎ ውስጥ የተረኝነት ስሜት የሚንጣቸው እንዳሉ ይነገራል። ሰሞኑን ያስገባችኋቸው አንድ መቶ አዳዲስ አውቶብሶች ችግሩን ምን ያህል እንደሚያቃልሉት ወደ ፊት የሚታይ ቢሆንም የከተማዋ የትራንስፖርት እንቆቅልሽ አሁንም አልተፈታም። የኑሮ ውድነቱም የዜጎችን ይልቁንም የመንግሥት ሠራተኞችን ክፉኛ እየተፈታተነ መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትም ሆኑ ያልተጠቀሱት ጥሩ ነገሮችም ሆኑ እንከኖች እንደተጠበቁ ሆነው ሥራ አጥነትን ዋነኛው የማኅበራዊ ቀውስ መንስኤ መሆኑ ይታወቃል።

በእርግጥ ችግሩ አገር ዐቀፍ ነው። መንግሥትዎም ይህንን ጊዜ የማይሰጥ እና በፍጥነት ካልተፈታ አደጋ የሚደቅን ችግር ለመፍታት በያዝነው 2012 ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ሥራ የሚያገኙበትን ዕድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ነው። ከመላው አገሪቱ በርካታ ዜጎች ሥራ ፍለጋ በየቀኑ የሚዘልቁባት አዲስ አበባ በርካታ ሥራ አጦች እንደሚገኙባት ጥናቶች ያመላክታሉ። አስተዳደርዎች ይህንን እውነታ በመረዳት እና በፌደራል መንግሥቱ ዕቅድ ጋር በማሰናሰን ቢያንስ ለ250 ሺሕ አዲስ አበቤዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ደፋ ቀና እያላችሁ መሆኑ ይታወሳል።

ይህንን ችግር በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ ከነደፋችሁት ዕቅድ መካከል አንዱ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በመስጠት በመረጡት ዘርፍ ለራሳቸው ሥራ ከመፍጠር አልፈው ለሌሎች እንዲተርፉ ማድረግ ነው። በእርስዎ የሚመራው ካቢኔም ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ከላይ በመግቢያዬ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ባለፈው ዓመት መጋቢት ውስጥ ለዚሁ ዓላማ ማስፈፀሚያ የሚውል 2 ቢሊዮን ብር ማጽደቁ ይታወሳል። ይህንን እቅድም የአዲስ አበባ አስተዳደር የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ከአዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ጋር በመተባበር እንዲተገብሩት መመርያ መጥቷል። የወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ለማስተዳደር የተዘጋጀው ሰነድ እንደሚያመለክተው እና እርስዎም በተለያዩ ሚድያዎች እንደገለፁት ይህ እቅድ ዘርፈ ብዙ ግቦችን እንዲያሳካነበር የተቀረፀው።

አስተዳደርዎ ባወጣው መመርያ ላይ ዓላማ ውብ ከተማ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ድህነት እና ሥራ አጥነትን መቀነስ ዋነኛ ግቡ መሆኑን በመግለጽ በዚህ ሒደት ውስጥ ወጣቶቹ የራሳቸውን ሥራ ከመፍጠር ባሻገር ሌሎችን ሊቀጥሩ እንደሚችሉ፤ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት እንደሚተኩ፤ ለማስመጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስቀሩ እና የአገር ውስጥ ፍላጎትን አሟልተው ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኙ ይተነትናል።

ይቀጥልና የፌደራል መንግሥቱን ተሞክሮ ተንተርሶ የከተማዋ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የ2 ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ መመደቡን ይገልጻል። የአዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ይህንን በበላይነት እንደሚያስተዳድር ከጥቃቅን እና አነስተኛ አንተርፕራይዝ ጽ/ቤት እንዲሁም ከሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት አብሮ እንደሚሠራ ይዘረዝራል። በተቻለ መጠን የተጠቃሚውን ፍላጎት ማዕከል አድርጎ እንደሚተገበርም ይናገራል። በገጽ ኹለት ላይ የመመርያውን ዓላማ ሲያስቀምጥ የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፤ የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሳደግ፤ ምቹና ቀልጣፋ በሆነ ሁኔታ በማስተናገድ በቤተሰብ ደረጃ የገቢን መጠን ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ይዘረዝራል።

የመመርያውን አስፈላጊነትን በዋነኛነት ፈንዱን በትክክል ለተጠቃሚው እንዲደርስ ለማስቻል እና ግልጽ የፋይናንስ ሥነ ምግባርን በመከተል ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መሆኑንም ይጠቁማል። የመመርያው መርሆች የወጣቶችን እና የሴቶችን ተጠቃሚነት እንዲሁም የቤተሰብን ተሳትፎ ማረጋገጥ፤ ቁጠባ መር የብድር ስርዓት መከተልን፤ እድገት ተኮር ዘርፎች ላይ ማተኮር፤ የብድር አመላለሱን ማረጋገጥ፤ ፈጣን አገልግሎት መስጠት እና በተቻለ መጠን ቅሬታ መቀነስ መሆናቸውን ይገልጻል።
የብድር መጠኑ እንዴት እንደሚወሰን በሚገልፀው ክፍል ደግሞ የሚከተሉት ነጥቦች ተቀምጠዋል። የብድር መጠን በተመለከተ የሚወሰነው ኢንተርፕራይዙ የሚያቀርበው የሥራ እቅድ በዋናነት መነሻ ሆኖ ለአንድ ኢንተርፕራይዝ ለሚቀርበው የሥራ እቅድ እስከ ኹለት ሚሊዮን ብር ድረስ የሚፈቀድ ይሆናል ይልና ዘርፎቹን ከእነ ብድር ጣራው ድረስ ያስቀምጣል። የማኒፋክቸሪንግ ዘርፍን በኹለት ክፍሎች አስቀምጦታል። 1/ የኮንስትራክሽን ግብዓት ምርት የማምረት ዘርፍ ውስጥ ለሚሠማራ ኢንተርፕራይ እስከ 800 ሺሕ ሆኖ በመጀመርያው ዙር እስከ 400 ሺሕ በኹለተኛው ዙር እስከ 800 ሺሕ ይለቀቃል ይላል። 2/ በተለያዩ የማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ደግሞ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ድረስ ይፈቀዳል ይላል።

በመጀመርያው ዙር እስከ 600 ሺሕ በኹለተኛው ዙር እስከ 1 ሚሊየን በሦስተኛ ዙር እና ከዛ በላይ እስከ 1.5 ሚሊዮን እንደሚለቀቅ ይገልጻል። ይቀጥልና በኮንስትራክሽን የሥራ ዘርፍ የኮንስትራክሽን ንዑስ ካሉ ተቋራጭ እስከ 600 ሺሕ ይፈቅድና ግማሹን በመጀመርያ ዙር ቀሪውን በኹለተኛ ዙር እንደሚለቅ ይጠቁማል። በኮንስትራክሽን ግንባታ ለሚሰማሩ ደግሞ እስከ 1.5 ሚሊዮን እንደሚሰጥ ከዚህ ውስጥም 500 ሺሕ መጀመርያ፤ እስከ 1 ሚሊዮን የሚጠጋው በኹለተኛ ቀሪው ደግሞ በሦስተኛ ዙር ይለቀቃል ይላል። በንግድ እና አገልግሎት ዘርፍ ለሚሰማሩ ደግሞ እስከ 600 ሺሕ እንደሚፈቀድ፤ ይህም ግማሹ በመዘመርያ ቀሪው በኹለተኛ ዙር እንደሚለቀቅ ይገልጻል። የከተማ ግብርና ላይ ለሚሰማሩ ደግሞ እስከ 800 ሺሕ እንደሚፈቀድ 400 ሺሕ በመጀመርያ ዙር ቀሪው ደግሞ በኹለተኛ እና ከዛ በላይ ባለ ዙር ሥራቸው እየታየ ይለቀቃል ይላል። በከተማው አስተዳደር በልዩ ሁኔታ በአዲስ የፈጣራ ሥራ ለመጡና እንዲስተናገዱ ለፈቀደላቸው ደግሞ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ድረስ እንደሚሰጣቸው ይደነግጋል።

በብድሩ ላይ የሚታሰበው 8 በመቶ ወለድ እንዳለው፤ ብድር የመመለሻው ጊዜ ጣርያ እስከ 4 ዓመት እንደሚዘልቅ እና አራት ወራት የእፎይታ ጊዜ እንደሚሰጣቸውም መመርያው ያዝዛል። ዋስትናን በተመለከተ የሽርክና ማኅበሩ አባላት አንዳቸው ለሌላኛቸው እንደሚሆኑ ይጠቁማል። ይህንን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የኢንተርፕራይዙን ቤተሰብ ተሳትፎ ያረጋገጠ፤ ቅድመ ዝግጅት ያጠናቀቀ፤ የዓላማ አንድነት ያለው፤ ቁርጠኝነትን መሰረት ያደረገ ወዘተ መሆን እንዳለበት ይገልጻል።
በአጠቃላይ ክቡር ከንቲባ ቀጣዮቹን አንኳር እውነታዎች እንዲገነዘቡ እሻለሁ።

1/ የመመርያ እና የድርጊት አለመገናኘት
እኔ የእነዚያን ወጣቶች ብሶት ሰምቼ፤ በአካል ተገኝቼ የመሰሎቻቸውን ብሶት ጭምር አዳምጬ እና እጄ የገባውን መመርያ ከእነ ማሻሻያው ከመረመርኩ በኋላ የተገነዘብኩት አንድ ነገር የሚመለከታቸው የአደራጆቹም ሆኑ የብድር አቅራቢው ተቋም ድርጊታቸው በአብዛኛው መመርያቸው የተከተለ አይደለም።

2/የብድር መጠኑን እና አፀዳደቁን የተመለከተ ችግር
ከልጆቹ ጋር ወደ ወረዳው ጎራ ስል ካገኘዋቸው መካከል የአንዱ በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ማለትም በዳቦ፤ ኩኪስ እና ኬክ ማምረት ሥራ ላይ የተደራጁ የሽርክና ማኅበር አባላት የጠየቁት የብድር መጠን ለዘርፉ ከተፈቀደው ጣራው 1.5 ሚሊዮን ውስጥ 986 ሺሕ ብር ቢጠይቁም የተፈቀደላቸው 150 ሺሕ ብር ነው። ይህ ራሱ የሚለቀቀው በሦስት ዙር መሆኑን ነግረዋቸዋል። ከልጆቹ ሰነድ እንደታዘብኩት ለሦስት ወር ቅድምያ ክፍያ 45ሺሕ ብር ከፍለው ቤት ተከራይተዋል። በዛ ላይ ወሩ እየተጠናቀቀ ነው። ታድያ የተፈቀደላቸው አንድ ሦስተኛ እንኳን ቢለቀቅላቸው የቀጣዩን ወር የቤት ኪራይ ከፍለው በምትቀራቸው 30 ሺሕ ብር ማሽን ሊገዙበት ነው ወይስ የሸክላ ምጣድ ገዝተው ሽልጦ ጋግረው ሊሸጡበት ነው? አልገባኝም ክብር ከንቲባ!

ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ ክፍተቶች አሉ። ዓላማችሁ ገንዘብ ማደል አይመስለኝም። ግባችሁ ውጤቶች ሥራ እንዲያገኙ፤ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወገኖች ብሎም ለአገራቸው እንዲተርፉ ከሆነ ቢያንስ ተመጣጣኝ የሆነ መነሻ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። እኔ ዘንድ መጥተው የነበሩት ወጣቶችም 5 ሺሕ ብር ከፍለው በባለሙያ ያሠሩትን የአዋጪነት ጥናት፤ ቢዝነስ ፕላን እና ስትራቴጂ አሳይተውኛል። ሞልተው ያስገቡትን የብድር መጠየቅያ ቅጽ ኮፒውን ተመልክቸዋለሁ። በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ለማሽን ግዢ፤ ለቢሮ ኪራይ፤ ለጥሬ እቃ አቅርቦት፤ ለአንድ ወር የሠራተኛ ደሞዝ፤ የውሃ፤ ለመብራት እና ለተያያዥ ወጪዎች የሚያስፈልጋቸውን በጥንቃቄ አስልተው በፕሮፎርማ አስደግፈው ነው ያቀረቡት። መመርያውም ከላይ እንዳሰፈርኩት እነርሱ በተሰማሩበት ዘርፍ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ብድር እንደሚፈቀድ ይገልጻል። የተፈቀደላቸው ግን የጠየቁትንም አንድ አራተኛ እንኳን አያክልም። ታድያ እርስዎ ይህንን እውነታ እንዴት ይገነዘቡታል?

3/ የተጣራ እና ትክክለኛ መረጃ አለመስጠት
ይህ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቴክኖሎጂ እና የመረጃ ዘመን ቢሆንም ያደራጇቸውም ሆኑ አበዳሪ ተቋሙ የተጣራ እና ትክክለኛ መረጃ አለመስጠት አንዱ ችግር ነው። አሁንም ቢሆን የተደራጁ ወጣቶችም ሆኑ ወላጆቻቸው በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው። ገንዘቡ አልቋል ከሚለው ጀምሮ ብድሩ ተቋርጧል የሚል ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑን በተለያዩ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ከተደራጁ ከበርካታ ወጣቶች በገዛ ጆሮዬ ሰምቻለሁ። ምናልባት የግብር ከፋይነት ሰርተፍኬት እስካወጡት ድረስ እናስተናግድ ይሆናል የሚል ግርድፍ እና ያልተረጋገጠ ምላሽ የሚሰጥም አለ። እውነት ለመናገር እንዲህ አይነት ለዜጋ ክብር የሌላቸው የሥራ ኀላፊዎች ተሰግስገው እስከ መቼ ተገልጋዩን እያማረሩ እንደሚዘልቁ አይገባኝም። ለነገሩ አብዛኛው ለቦታው የማይመጥን እና የማይገባ የፖለቲካ ሹመኛ ስለሆነ ስለ ፓርቲው እና ስለ እንጀራው እንጂ ስለ ዜጋው ግድ የሚሰጠው ዓይነት አይመስልም። ለሆኑ እርስዎና አስተዳደርዎ ይኼንን ጉድ ያውቃል? በእንደዚህ ዓይነት የመልካም አስተዳደር እጦት ከዚህ በኋላ ለምን ያህል ዓመት ይሆን የገዛ ሕዝባችሁን እያማረራችሁ የምትዘልቁት?

ሌላኛው ችግር ደግሞ ለሚደራጁ ወገኖች ገና ከመደራጀታቸው በፊት በቃል ብቻ ሳይሆን በጽሑፍ የተደገፈ መረጃ አለመስጠት ነው። ከመመርያው የመነጨ እና በግልጽ የተዘጋጀ ብሮሸር መኖር አለመኖሩን ጠይቄ አለመዘጋጀቱን ነው የተረዳሁት። እያንዳንዱ ወጣት ከተደራጀበት ዕለት አንስቶ ብድሩ እስከሚለቀቅበት ጊዜ ድረስ ምን ያህል ቀን /ምን ያህል ሳምንት ወይም ወር/ እንደሚፈጅ እና ቅደም ተከተሉ ምን ምን እንደሆነ እንዲሁም አጠቃላይ ቅድመ ሆኔታውን ጨምሮ ማሟላልት ያለበትን ነገር በዝርዝር የያዘ ብሮሸር ቢሰጥ እንግልቱንም ሆነ ኪሳራውን መቀነስ በተቻለ ነበር።

4/ ወጣቱን ከእነ ቤተሰቡ ለጭንቀት እና ለኪሳራ መዳረግ
ወጣቶቹ ብድሩን ለማግኘት እና የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር በማሰብ ነው የተደራጁት። በሒደቱም መተዳደርያ እና መመስረቻ ጽሑፍ ለማፀደቅ፤ ዋና ምዝገባ እና ንግድ ፍቃድ ለማውጣት፤ ማኅተም ለማሰራት፤ ውል ለማጻፍ፤ ደረሰኝ ለማሳተም፤ የብቃት አረጋጋጭ ባለሙያዎችን እና የአዲስ ብድር ተቋም ተወካዮችን በተለያየ ጊዜ አድርሶ ለመመለስ የኮንትራት ትራንስፖርት ወጪ ያወጡ ሲሆን በትንሹ ከሦስት እስከ ስድስት ወር የሚሆን የቤት ኪራይ ተበዳድረው ከፍለዋል። እንግዲህ የሚመለከተው አካል ይህንን እውነታ እንዴት ከግምት ውስጥ ማስገባት ይሳነዋል? በዚህ የለውጥ እና የካሳ ዘመን ወጣቶችን ከነቤተሰቦቻቸው ኪሳራ ውስጥ መክተት ምን ይባላል? ወጣቶቹ ላይ የደረሰው ነገር አበው “አተርፍ ባይ አጉዳይ” የሚሉትን ተረት የሚያስታውስ ነው። ለመሆኑ በእርስዎ ቃል እና የለውጡ ኀይል በሰጣቸው ተስፋ ተማምነው ተበዳድረው ራሳቸውን ለሥራ ያዘጋጁ ወጣቶችን ከማበረታታት ይልቅ ይባስ ብሎ ያልታሰበ ዕዳ ውስጥ መክተት ለምን አስፈለገ?

5/ አድሎ እና መድሎ መኖር
እንደሚወራው ከሆነ የከተማዋ ነዋሪ ሳይሆኑ ሲፈለጉ የሚገኙበት አድራሻ የሌላቸው በርካታ ወጣቶች ጊዜያዊ መታወቂያ እየተሰጣቸው ተደራጅተዋል። ገሚሶቹም ጉዳያቸው እንደ ደሃ ፍታት በጥድፍያ ተከናውኖ ብድር ያገኙ ከመሆናቸው ባሻገር ተቀብለው ዱካቸውን ያጠፉ እንዳሉ የውስጥ ሰዎች ነግረውኛል። እርግጥ ስለ ተባለ ብቻ እውነት ነው ማለቴ አይደለም። በአንጻሩም ከምናየው እና ከምንታዘበው ተነስተን አድሎ እና መድሎ የለም ብለን ለመደምደምም እንቸገራለን። አስተዳደሩም ቢሆን ለእያንዳንዱ አሉባልታ መልስ መስጠት እንደሌለበት ቢገባኝም ይህንን የመሳሰሉ እያደር መዘዝ የሚያስከትሉ ችግሮችን ንቆ ባያልፋቸው መልካም ነው። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው የሚለውን ብሒል አመርሳት ደግ ነው። በራስ መተማመኑ ካለም በኹለት እግራቸው ለመቆም እየተንደፋደፉ ያሉትን እንደ እንባ ጠባቂ፤ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን፤ ፍርድ ቤት እና መሰል የዲሞክራሲ ተቋማትን በማስተባበር ወይም ሌሎች ገለልተኛ አካላትን በማሰማራት እውነታውን አጣርቶ እርምጃ መውሰዱ ይበጃል።

6/ ከተልባ ጋር የተገኘን ሰሊጥ አብሮ የመውቀጥ ችግር
ከሚሰሙት ተባራሪ ወሬዎች መካከል አንዱ ሌላ ቦታ ሥራ ያላቸው ሰዎች ተደራጅተዋል የሚል ነገር ይሰማል። ይህ እውነት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ግን ይህን የማጣራት እና የመለየት ሸክሙ የአደራጁ አካል እንጂ ሥራ አጥተው ሲሰቃዩ የከረሙ ወጣቶች እና ወላጆቻቸው አይደሉም። አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ እንዲሉ በእነዚህ ኢ-ፍትሐዊ ጥቅም ለማግኘት ባሰፈሰፉ ሕገ ወጦች ምክንያት ንጹሐን መጎዳት እና ለተጨማሪ ዕዳ ወይም ጭንቀት መዳረግ የለባቸው። ለነገሩ አደራጆቹ ራሳቸው በሌላ ሥራ ላይ የሚገኙ የቅርብ እና የሩቅ ዘመዶቻቸውን እንዲደራጁ እያደረጉ መሆኑን በማስረጃ አስደግፈው የሚናገሩ አሉ። ሥራ አጥ እስከ ሆኑ ድረስ እና መስፈርቱን እስካሟሉ ድረስ የአደራጆቹ አይደለም የሩቅ ቀርቶ የቅርብ ዘመዶቻቸው ቢደራጁ ምንም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ሁሉም አዲስ አበቤ እንደ ዜጋ መስፈርቱን እስካሟላ ድረስ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ይችላልና። ይሁንና ግን ሌላ ሥራ እያላቸው የተደራጂ አሉ በሚል ጥርጣሬ ንጹሐኑ ሥራ አጦች ከዚህ በላይ እንዳይንገላቱ ጥንቃቄ ይደረግ።

7/ አደራጅቶ ለስኬት እንዲበቁ ከመደገፍ ይልቅ በተቃራኒው ለሕግ ተጠያቂነት አሳልፎ የመስጠት ችግር
በርካታ ወጣቶች የሽርክና ማኅበር ካቋቋሙ በኋላ የግብር ከፋይነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት /ቲን ቁጥር/ አውጥተዋል። ከሚሰማሩበት የሥራ ባሕሪይ አንጻር ቫት የተመዘገቡም አሉ። እነዚህ ወገኖች ደግሞ በየወሩ ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሪፖርት ለማድረግ ሲሔዱ ደግሞ የካሽ ሬጅስተር ማሽን እንዲያስገቡ ይገደዳሉ። ይህንን ማሽን ለማስገባትም ቢያንስ ከ6 እስከ 12 ሺሕ ብር ያስፈልጋቸዋል፤ ሌላ ወጪ ሌላ ዕዳ። እንደሚታወቀው ካሽ ሬጅስተር ካልገዙ ከአንድ ኹለት ወር በላይ ገቢዎች አይታገሳቸውም። ዜድ ሪፖርት እስካልያዙ ወርሃዊ ሪፖርት ማድረግም አይችሉም።

በተጨማሪ ብድሩ መሰጠት ቆሟል እየተባለ ነው። ታድያ ምናልባት ወዳጅ ዘመድ አስቸግረው ካሽ ሬጅስተር ማስገቢያ ገንዘብ ቢያገኙ ምን ተማምነው ነው ማሽኑን የሚገዙት? የተሰጣቸው ተስፋ መና ሆኖ ቢቀርስ ድርጅት መዝጋት ጣጣው ብዙ መሆኑን አይደለም በንግድ ሥራ የተሰማራ ቀርቶ ሕግ አውጭው ራሱ መች ያጣዋል። የአገሪቱን የንግድ አመቺነት ደረጃ ውራ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱስ ይሔ አይደለምን? መጀመርያውኑ ለመደራጀት ያወጡት ወጪ አላንስ ብሎ ለመዝጋት ደግሞ ለተጨማሪ ወጪ መዳረግ አለባቸው? ምንም ዓይነት ሥራ ባይሰሩም ቢያንስ ያኑኑ ዜሮ ሪፖርት ለማቅረብ እና ክሪላንስ ለመውሰድ ተጨማሪ ገንዘብ ለተፈቀደለት የሒሳብ ባለሙያ መክፈል አለባቸውን? ይኼ ኡኡኡ አስብሎ ያስጮኻል። ወይስ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታልን ያስመረቃችሁት በገዛ እንዝላልነታችሁ ልታሳብዷቸው ጫፍ ላይ ያደረሳኋቸውን ወጣቶች ከዚህ አዲስ የአዕምሮ ሕሙማን የሕክምና ማዕከል ለማስተኛት ይሆንን?

እንዴት ነው ነገሩ? ክፍለ ከተማ በሔድኩበት አጋጣሚ በሁኔታው የተበሳጩት ወጣቶች “ድምጻችን ይሰማ ብለን ሰልፍ እንውጣ ወይስ አገራችንን ለቀንላችሁ እንሰደድ?” ብለው ካነሱት መሟገቻ መካከል አንዱን ይተግብሩት እንዴ? ከልጆቹ እንደሰማሁት መፍትሔ ካላገኙ ከወላጆቻቸው ጋር ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚወጡ ነው። ለማንኛውም እነዚህ ተበዳይ ወጣቶች በቁጣ ወጥተው ችግር እንዳይፈጠርም ሆነ ለተጨማሪ እንግልት እና ጉዳት እንዳዳረጉ በመስጋት ነው ከወዲሁ አውቃችሁ መልስ እንድትሰጧቸው ይህንን ግልጽ ደብዳቤ የጻፍኩት።

ክቡር ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ዑማ እባክዎ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች በመመርመር እና ፈጣን መፍትሔዎችን በማመንጨት ለእነዚህ ወጣቶች ይድረሱላቸው። ሌላው ቢቀር በዚህ ዓመት ይደረጋል በተባለው ምርጫ ፓርቲዎ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ያለው እቅድ እንዲሳካ ቢያንስ እነዚህ ብሶተኛ ወጣቶች እና ቤተሰቦቻቸውን ይበልጥ ባያስከፋ መልካም መሆኑን ጭምር ላስታውስዎ እወዳለሁ። ሻሎም!
ማርሴላስ ሚደቅሳ
የግሎባል ኢንቨስትምንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የዩንቨርሲቲ መምህር
ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው marselasgig@gmail.com ማግኘት ይቻላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here