በመኪና “ሰብሳቢነት” ታሪካቸው በአዲስ መልክ የተነሳው አጼ ኃይለ ሥላሴ

0
656

ብርሃኑ ሰሙ መንግሥት የቱሪዝምን ዘርፍ ትኩረት እየሠራ እንደሆነ የሕዝብ ተወካዮች ስብሰባን እና “ትልቅ ነገር እናልማለን፣ ትልቅ ነገር እናስባለን፣ ነገር ግን ከትንሽ እንጀምራለን፣ ያን በፍጥነት አሰናስለን ወደ ፈለግንበት እንደርሳለን” በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እያሠሩ ያሉትን እና ሐሙስ መስከረም 29 የተመረቀውን አንድነት ፓርክን በተመለከተ በቅርቡ የተለቀቀውን ቪዲዮ መነሻ በማድረግ ሌሎች መኪኖችም ለተመሳሳይ ዓላማ ሊውሉ የሚችሉ አሉ ሲሉ ጠቁመዋል።

 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የ2012 በጀትን ለማጽደቅ፣ ሐምሌ 1/2011 ተሰብስበው በተወያዩበት ወቅት፣ በቀጣዩ ዓመታት በአገር ውስጥ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ትኩርት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑ ተነስቶ ነበር። በዚህ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቤተ መንግሥቱ በአገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች እንዲጎበኝ ታስቦ እየተሠራ ያለውን የዕድሳት ሥራ ማዕከል አድርገው በ4 ኪሎ ብቻ ሳይሆን በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ውስጥ ቱሪስቶችን የሚስቡ በርካታ ታሪካዊ ስብስቦች እንዳሉ አጼ ኃይለሥላሴ ያሰባሰቧቸው 30 መኪኖች በማሳያነት አቅርበዋል።

ከበጀት ዓመቱ ኹለት ወራት ከ15 ቀናት ከተሸኘ በኋላ፤ ዓርብ፣ መስከረም 9/2012 የቤተ መንግሥት ሕዝብ ግንኙነት ሠራተኞችን ተክተው፣ የ“ግቢ”ው የልማት ሥራ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በየክፍሉ፣ በየመሰብሰቢያ አዳራሾችና መናፈሻ ፓርኮች በእግርና በመኪና እየተንቀሳቀሱ ማብራሪያና ገለጻ እየሰጡ በቴሌቪዥን የቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አጼ ኃይለሥላሴ ስላሰባሰቧቸውና የቤተ መንግሥት ቅርስ አካል መሆን ስለቻሉት መኪኖች በድጋሚ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአጼ ኃይለሥላሴ የመኪና ስብስቦች አንዱ “ካዲላክ” እንደሚባል፣ ንጉሠ ነገሥቱ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመን ወደ ብሪቲሽ በተሰደዱበት አጋጣሚ ከእንግሊዝ መንግሥት የተበረከተላቸው መሆኑን፣ መኪናው በንጉሠ ነገሥቱ በራሳቸው መነዳቱን፤ በዚህ ምክንያት የቅርስነት ደረጃው ከፍ ያለው “ካዲላክ” እና መሰል መኪኖችን “በመስታወት ቤት ውስጥ አስቀምጦ” በማስጎብኘት የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልብ መሳብ እንደሚቻል ሰፊ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“አቧራ የለበሱ” ቅርሶቻችንን፣ ብናኙን በመጥረግ ብቻ፣ በአዲስ መልክ መጠቀም የሚያስችል ብዙ ዕድል አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ይህ ገለጻቸው ስለ ቤተ መንግሥት መኪኖች ዋጋ ቢስነት የተሰጠን ምስክርነት የሚያስታውስ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት በተካሔደ አንድ የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ፣ “የባለሥልጣናት መኪና ይቅረብልን ጥያቄ ትኩረት ተሰጥቶት ምላሽ ያላገኘው ለምንድ ነው?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ዐፈሩ ይቅለላቸው) በሰጡት መልስ፤ መንግሥት ከፍተኛ መኪና ችግር እንዳለበት አመልክተው፣ ለዚህ አንዱ ማሳያ አድርገው ያቀረቡት “የውጭ አገር እንግዶችን የምንቀበልባቸው የቤተ መንግሥት አሮጌ መኪኖች በየዳገቱ መሔድ አቅቷቸው ወገቤን እያሉ በመቆም አስቸግረውናል” የሚል ነበር።

በእርጅና ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩት መኪኖች አሁን “አቧራቸውን በመጥረግ” ብቻ ሌላ አገልግሎትና ጠቀሜታ እንዲሰጡ መታቀዱ እየተነገረ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በቤተ መንግሥት ውስጥ ስለሚገኙት መኪኖች ያነሱት ሐሳብ ብዙ ጥያቄዎች ተነስተው ብዙዎች እንዲወያዩበት ዕድል የሚሰጥ ይመስለኛል። በመጀመሪያ ደረጃ አጼ ኃይለሥላሴ የነበራቸው የመኪና ፍቅር “ሰብሳቢ” (Car Collector) ደረጃ አድርሷቸው ነበር ወይ? የነበሯቸው መኪኖችስ ዓይነትና ደረጃ ምን ይመስላል? ከ “ካዲላክ” ውጭ ምን ያህሉን በስጦታ አገኙ? ምን ያህሉንስ በግዢ አሰባሰቡ? ከሰላሳዎቹ መኪኖች ውስጥ ደርግ፤ አጼ ኃይለሥላሴን ከኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት በማስወጣት ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ የወሰደበት ቮልስዋገንም ትገኛለች ወይ? መስከረም 13/1969 የደርግ ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩት ሻለቃ (በኋላ ኮሎኔል) መንግሥቱ ኃይለማርያም ላይ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ዕለት ያመለጡበት ላንድሮቨር መኪናስ ቤተመንግሥቱ ውስጥ ካሉት ስብስቦች አንዱ ነው ወይ? መኪኖቹ ታሪካዊ ናቸው የተባለውስ በምን መስፈትና መመዘኛ ይሆን?

“የአውቶሞቢል አመጣጥ ታሪክ በኢትዮጵያ” ምን እንደሚመስል የታሪክ ባለሙያ በሆኑት በአቶ ክንፈ በርሔ የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ በ2005 ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ ታትሟል። “የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ኢንታንጀብል ባሕላዊ ቅርሶች እና የታሪክ ጥናት” በሚል ርዕስ በታተመው ጥራዝ ከቀረቡ የምርምር ሥራዎች አንዱ በሆነው የአቶ ክንፈ ጽሑፍ፤ የኢንዱስትሪ አብዮት መስፋፋት ካስገኛቸው የሰው ልጅ ድንቅ ሥራዎች መሀል አውቶሞቢል አንዱ መሆኑን፤ በ1769 ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቆ ለሕዝብ ዕይታ የበቃው አውቶሞቢል በመጀመሪያ የሚንቀሳቀሰው በእንፋሎት ኃይል እንደነበር፤ በ1806 በናፍጣ፣ በ1885 በቤንዚን አሁን በኤሌክትሪክ ኃይል ማንቀሳቀስ የሚቻልበት ዘመን ላይ መደረሱን ይገልጻሉ።

የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ወደ አገራቸው ለማስገባት ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው አጼ ምኒልክ መኪና ለማስመጣት ያላቸውን ፍላጎት ያዩት እንግሊዛውያን፣ ፈረንሳውያንና ጀርመናውያን ከተለያየ አቅጣጫ በመነሳት መኪና ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ባደረጉት ጥረት፤ ዲ.3130 መለያ ቁጥር የያዘችውና “ሲድሌ” የሚል መጠሪያ የተሰጣት መኪና የአገሪቱን ምድር በመርገጥ ቀዳሚና ታሪካዊ መሆን መቻሏን አቶ ክንፈ በርሔ ያብራራሉ።

ሲድሌ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው መኪና እንደሆነች ሁሉ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የመኪና ሹፌር አጼ ምኒልክ መሆናቸውን፤ ቀዳሚው የቤተ መንግሥት ሹሬር ሕንዳዊ ዜግነት የነበረው ኢዳልጂ እንደነበር፤ የቤተ መንግሥት ወፍጮ ቤት የቴክኒክ ሠራተኛ የነበረው ጣልያናዊው ሲኞር አልዋቲየ “ሲድሌ”ም መካኒክ ሆኖ በመመደቡ በዘርፉ የተሰማራ ቀዳሚው ባለሙያ ስለመሆኑ፤ በአገሪቱ የመጀመሪያው ጋራዥም በቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ መከፈቱን … በጥናታዊ ጽሑፋቸው በስፋት ያቀረቡት የታሪክ ባለሙያው፤ የመኪኖች፣ የሹፌሮች፣ የመካኒኮች፣ የጋራዦች … ቁጥር በምን መልኩ እያደገ እንደመጣ ታሪኩን በስፋት ዳስሰዋል።
“ስድሌ”ን ወደ ኢትዮጵያ ማን እንዳመጣት፣ ከየትና እንዴት እንደመጣች … የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንዳሉ ያመለከተቱ አቶ ክንፈ በርሔ፣ ያ ታሪካዊ መኪና በኋላ ላይ ምን ሆነ? ለሚለው ጥያቄም አንድ ወጥ ምላሽ የለም ይላሉ። …

ከአጼ ምኒልክ በመቀጠል በንግሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት መኪኖች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡም ራስ ተፈሪ መኮንን አልጋ ወራሽ ከሆኑና በተለይ በ1916 አውሮፓን ጎብኝተው ከተመለሱ በኋላ በርካታ መኪኖችን ገዝተው ለመኳንንትና መሳፍንት በመስጠት ጭምር አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ምሁሩ ያመለክታሉ።

በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስለገቡ መኪኖች በሰነድ የተደገፈ ዝርዝር መረጃ የማግኘት ችግር አለ የሚሉት አቶ ክንፈ በርሔ፤ በቅርስነት ተመዝግባ ብሔራዊ ሙዚየም መግባት ስለቻለችው መኪና በምርምር ያገኙትን እውነተኛ መረጃ በጥናታዊ ጸሑፋቸው አቅርበዋል። “የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ለበርካታ ዓመታት የአጼ ምኒልክ የመጀመሪያዋ መኪና ናት የተባለችውን ተሸከርካሪ በንብረትነት ይዞ” መቆየቱን የሚገልጹት የታሪክ ምሁሩ፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በ2003 የሲኤምሲ አደባባይና መንገድን ሲያስመርቅ፣ መኪናዋን ለዕይታ አብቅቷት በዚያ አጋጣሚ ለብሔራዊ ሙዚየም መስጠቱን አስታውስው፤ ሆኖም “በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ሳይሆን የአውራ ጎዳና ንብረት መሆኗን፣ በ1955 መሥሪያ ቤቱ ከሞተርና ከኢንጅነሪንግ ካምፓኒ (ሞይንኮ) እንደ ተገዛ በሰነድ ማረጋገጥ ተችሏል” ይላሉ።

የአጼ ኃይለስላሴ “ስብስብ” ናቸው የተባሉት መኪኖች በታቀደላቸው መሠረት “ሙዚየም በሚሆነው” ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ውስጥ ለዕይታ ከመቅረባቸው በፊት፣ እያንዳንዱን ተሸከርካሪ አንዱን ከሌላኛው ልዩ የሚያደርው መረጃ ከወዲሁ ማፈላለጉ፤ የመኪኖቹን ታሪካዊነትና ደረጃ ከፍ ከማድረጉም ባሻገር “የበሬውን ዋጋ ፈረሱ” እንዳይወስደው ለመከላከል ያስችላል። በነገራችን ላይ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በመጨረሻው የሥልጣን ዘመናቸው የተገለገሉበትና “ለቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ቤተሰቦችና ወዳጆች ማኅበር” ተሰጥቷል የሚባለው መኪናስ (አፈ ታሪኩ እውነት ከሆነ) ለኤግዚቢሽን ከሚቀርቡት መኪኖች አንዱ መሆን አይገባውም ወይ?

ስለአጼ ኃይለሥላሴ መኪኖች ሲነሳ፣ ሮልስሮይ መኪናቸው በብዙዎቹ የዘመናቸው ሰዎች ይታወቃል። ይህ መኪና ለንጉሠ ነገሥቱ የተበረከተው ከእንግለዝ መንግሥት ነበር። እንግሊዞች ሮልስሮይ አውቶሞቢልን መቼ፣ እንዴትና በምን ምክንያት ለአጼ ኃይለሥላሴ ሊያበረክቱ እንደቻሉ፤ አምባሳደር ተፈራ ኃይለሥላሴ በ1999 ባሳተሙት “ኢትዮጵያና ታላቋ ብሪታኒያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ከ1798 – 1966” መጽሐፍ ውስጥ የሚከተለውን መረጃ አስፍረዋል።

“በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመን ኢትዮጵያን ለመርዳት የመጣችው እንግሊዝ … ‘ታላቋ ሱማሌን’ ለመመሥረት የነበረው ምኞቷን ለማሳካት እና በጣና ሐይቅ ላይ ግድብ ለመሥራት የነበራትን ምኞት እውን ማድረግ እንዲያስችላት ለአጼ ኃይለሥላሴ ካበረከተችው ስጦታ አንዱ መኪና ነበር …በ1936 ውል ኹለቱም መንግሥታት በተለያየ ምክንያቶች ረክተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ነፃነት በማስመለሱና ኦጋዴንና የተጠበቀው ክልል የኢትዮጵያ ግዛቶች መሆናቸው መረጋገጡና ከውሉ ዘመን ፍጻሜ በኋላ የመረከብ መብቱ በመጠበቁ ተደስቷል። የእንግሊዝ መንግሥት ደግሞ ኦጋዴንና የተጠበቀውን ክልል ማስተዳደሩን እንዲቀጥል መደረጉ የሩቅ ጊዜ ዓላማውን ‘ታላቋ ሱማሌ’ን ለመፍጠር የመጀመሪያው እርምጃ እንደሆነ በመቁጠር ረክቷል።

… ወደ ፊት ስለወሰን መካለልና በጣና ሐይቅ ላይ ግድብ ለመሥራት ለሚደረገው ድርድር የንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድና ድጋፍ ለማግኘት እንዲረዳው ድርድር በሚካሔድበት ወቅት አንድ ሮልስሮይ አውቶሞቢል ለማበርከት ቃል ገብቶ ነበር። በቃሉ መሠረት መለያ ቁጥር FLU 500 የሆነ ተሸከርካሪ በአዲስ አበባ የእንግሊዝ መንግሥት ጉዳይ ፈጻሚ አማካይነት እ.ኤ.አ ነሐሴ 12/1946 ለኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ማስረከቡ ተመዝግቧል።”
ብርሃኑ ሰሙ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ላይ በንቃት በመሳተፍ ይታወቃሉ በኢሜል አድራሻቸው
ethmolla2013@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here