የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ካፒታል ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ተችሏል ተባለ

0
1267

ባለፈው ዐስር ዓመት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ካፒታልን ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው፣ ባለፉት ዐስር ዓመታት ማኅበሩን ለማጎልበት በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሠሩ ሥራዎች ያሉ ሲሆን፣ በ101 ሺሕ 834 መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ 16 ሚሊዮን 406 ሺሕ 710 ወንድ እና 8 ሚሊዮን 17 ሺሕ 944 ሴቶች በድምሩ 25 ሚሊዮን 507 ሺሕ 304 አባላትን ማፍራት ተችሏልም ተብሏል።

በተጨማሪ 395 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች፣ 20 ሺሕ 373 የዩኒየን አባል የሆኑ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና አምስት የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖችን ማፍራት እንደተቻለም ተጠቁሟል። ከነዚህም በአጠቃላይ 33 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማፍራት ተችሏል ነው የተባለው። ኮሚሽኑ አክሎም፣ ባለፈው ዐስር ዓመት ውስጥ 22 ሺሕ 358 መሠረታዊ የገቢ ቁጠባ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 133 የገቢ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እና ኹለት የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽን መፍጠር እንደተቻለ እና ካፒታሉን ወደ 30 ቢሊዮን 568 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳደግ እንደተቻለ ተነግሯል።

ኮሚሽኑ በተጨማሪ ለገንዘብ ቁጠባ ብድር ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ኢንቨስትመንት 29 ነጥብ 49 ቢሊዮን ብር ብድር ማቅረብ መቻሉን አመላክቷል። አጠቃላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የካፒታል ዕድገት በ2005 ከነበረበት 3 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ተነስቶ በ2006 ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሬ በማስመዝገብ 8 ነጥብ 80 ቢሊዮን ብር ማድረስ ተችሏል። በተጨማሪ በ2007 12 ነጥብ 30 ቢሊዮን ብር
ማሳደግ እንደተቻለ እና ከአንድ ዓመት በኋላ 2 ነጥብ 30 ቢሊዮን ብር ጭማሬ በማሳየት 14 ነጥብ 60 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደተቻለ ተነግሯል።

በ2009 የማኅበሩ ካፒታል 20 ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2010 ወደ 22 ነጥብ 80 ቢሊዮን ማሳደግ እንደተቻለም ተነግሯል። በ2011 እንዲሁ 25 ነጥብ 44 የነበረውን የማኅበሩን ካፒታል ከአንድ ዓመት በኋላ 28 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደተቻለ ተጠቁሟል። በተጨማሪ በ2012 የነበረው የማኅበሩ ካፒታል በ2013 31 ነጥብ 70 ሚሊዮን ብር እንደነበር እና በ2014 ደግሞ ከ33 ነጥብ 70 ቢሊዮን ብር በላይ ማሳደግ እንደተቻለ ተጠቁሟል።

ይህም ማኅበሩ ባለፉት ዐስር ዓመታት በየዓመቱ ከኹለት ቢሊዮን ብር ጀምሮ እስከ አምስት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ካፒታሉን ማሳደግ እንደቻለ ተነግሯል። ኮሚሽኑ አያይዞም መንግሥት ፋይናንስ የሚያደርጋቸውን ቋሚ የምግብ እና የሰብል ግዥ የሚፈፅሙ ተቋማት ሰንሰለት በማብዛት ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here