132 ደንብ አስከባሪዎች እርምጃ ሊወሰድባቸው ነው

0
1721
  • ደንብ አስከባሪዎቹ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ የተያዙ ናቸው

በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ደንብን የሚጥሱ ሰዎችን እንዲቆጣጠሩና እርምጃ እንዲወስዱ ኃላፊነት የተሰጣቸው 132 ደንብ አስከባሪዎች ራሳቸው የደንብ ማስከበር መመሪያን በመጣስ ሕገ ወጥ ድርጊት ሲያከናወኑ ተገኝተው እርምጃ ሊወሰድባቸው መሆኑ ተገለጸ። በከተማዋ ከተሰማሩ ደንብ አስከባሪዎች መካከል መመሪያን በመጣስ ሕገ ወጥ ሥራ የሚያከናውኑ በርካታ ሠራተኞች እንደተገኙና እርምጃ ሊወሰድባቸው መሆኑን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ሕጉን የተላለፉ ደንብ አስከባሪዎች በጠቅላላው ምን ያህል እንደሆኑ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆንም፤ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ቡድን መሪ ንጹህ አስታጥቄ ግን 132 መመሪያ የተላለፉ ደንቦች በክፍለ ከተማቸው ብቻ መገኘታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በደንብ ማስከበር ሥራ የተሰማሩ በርካታ ‹ኦፊሰሮች› ከዚህ በፊትም ሕገ ወጥ ሥራ ሲያከናውኑ መገኘታቸውን ያስታወሱት ንጹህ፤ በ2014 በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ 132 ሰዎች መመሪያ መጣሳቸውን ተናግረዋል። የደንብ ማስከበር መመሪያን በመጣስ ሕገ ወጥ ተግባራትን ያከናውናሉ የተባሉት ደንብ አስከባሪዎች በዋነኝነት በሕገ ወጥ የመሬት ማስፋፋት፤ ሕንጻ ግንባታ፤ የጎዳና ላይ ንግድ እንዲሁም ሌሎች መሰል ድርጊቶችን ከሚያደርጉ ሰዎች ጉቦ የተቀበሉ እና ዘርፈው ለራሳቸው የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል።

በሕገ ወጥ የመሬት ዝውውር ላይ በደንብ መመሪያው መሠረት እርምጃ መውሰድ ሲገባቸው ኃላፊነታቸውን አጉድፈው የተገኙ አራት ደንብ አስከባሪዎች ጉዳያቸው ሰሞኑን እየታየ መሆኑንና እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ንጹህ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በከተማዋ የተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩና ደንቦች የሚያሳድዷቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ንብረታቸውን እንደሚዘረፉና ደንብ አስከባሪዎችም ‹ደንብ ጥሳችኋል› በሚል ሰበብ ንብረታቸውን እየቀሙ ለግላቸው ጥቅም እንደሚያውሉት መናገራቸው አይዘነጋም።

ለአብነትም በሊስትሮ ሥራ፤ በመንገድ ላይ ንግድ ተሰማርተው እንዲሁም አጣና ሸጠው በሚያገኙት ገቢ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ሠራተኞች ደንቦች በሰበብ አስባቡ ንብረታቸውን እንደሚቀሟቸውና ለግላቸው ጥቅም እንደሚያውሉት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ደንብ አስከባሪዎቹ ይህንኑ ተግባር እንደሚያከናውኑ የመሰከሩት ንጹሕ፤ መመሪያውን በመተላለፍ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡት ሠራተኞች ላይ ከቅጣት እስከ ሥራ ማሰናበት ድረስ እርምጃ ለመውሰድ ጥፋታቸውን በመፈተሽ ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በከተማዋ የተለያዩ ሥፍራዎች ሕገ ወጥ የእንስሳት እርድና ዝውውር በሚያደርጉ፣ ሕገ ወጥ ማስታወቂያ በሚለጥፉ፣ ሕገ ወጥ ሕንጻ በሚገነቡ፣ ሕገ ወጥ የመሬት ማስፋፋት ሥራ በሚያከናውኑ፣ አዋኪ ድርጊቶችን በሚያስፋፉ (ሺሻና ጫት ቤቶች)፣ በመንገድ ላይ ሕገ ወጥ ንግድ በሚያስፋፉ ሰዎች ላይ የቅጣት እርምጃ መወሰዱን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ መተላለፍ ቁጥጥር እና እርምጃ አወሳሰድ ሥራዎች አስተባባሪ ማሙየ ወንድአፈረው ተናግረዋል።

ማሙየ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተያዘው ዓመት በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱት የደንብ ጥሰት ላይ በተሰማሩ ሰዎች ከተገኘ የብር ቅጣት እና ከጨረታ ከ3 ሚሊዮን 580 ሺሕ ብር በላይ ገቢ እንደተሰባሰበ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ደንብን ከጣሱ ሰዎች ከ2 ሚሊዮን 148 ሺሕ ብር በላይ እንዲሁም ከጨረታ 1 ሚሊዮን 587 ሺሕ ብር በላይ መሰብሰቡን ማሙየ በዝርዝር ተናግረዋል። በሕገ ወጥ መንገድ ማለትም ቆሻሻ እና ፍሳሽን ከውሃ ቱቦ ጋር ባገናኙ፤ በመንገድ ላይ በሕገ ወጥ ንግድ በተሰማሩ፤ ሕገ ወጥ ሕንጻ በገነቡ፤ ሺሻና ጫት በሚያስጠቅሙ እና በሌሎች መሰል ተግባራት ላይ በተገኙ ከ3 ሺሕ 572 በላይ ሰዎች እርምጃ እንደተወሰደም ነው የተገለጸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here