መነሻ ገጽዜናትንታኔሰሞነኛው የአልሸባብ ትንኮሳ

ሰሞነኛው የአልሸባብ ትንኮሳ

በፖለቲካም ይሁን በኢኮኖሚ ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት የሚያገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና፣ የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ታጣቂ ቡድኖች ሰንሰለታቸውን የዘረጉበት ቦታ ስለመሆኑ ይነገራል። ከ40 ዓመታት በፊት በሩስያ-አፍጋኒስታን ጦርነት ወቅት የተመሠረተው እስላሚዊ ቡድን አልቃይዳ፣ በ1980ዎቹ ራሱን ያደራጀው በዚሁ ቀጠና በምትገኘዋ ሱዳን ነበር።

ይልቁንም በምሥራቅ አፍሪካ የብዙዎች ሰዎች መልዐከ ሞት ሆኖ የሚታወቀው አልሸባብ የተሰኘው ታጣቂ ኃይል፣ በመሠረታዊነት ራሱን የእስልምና እምነት ጠላት የሆኑ አካላት ላይ ጅሃድ የሚፈጽም ቅዱስ ዘብ አድርጎ ይጠራል። አልሸባብ የጅሃዲስት ወጣቶች ንቅናቄ (Mujahideen Youth Movement) መሆኑንም ነው የሚገለጸው። እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ በተጨማሪም እስልምናን አያስከብርም የሚለውን የሶማሊያ መንግሥት እንዲሁም በአገሪቱ ወታደራዊ ግዳጅ እየከወነ ያለውን የአፍሪካ ኅብረት አቋምም እታገላለሁ ይላል።

ከሶማሊያው አምባገነን መሪ ዚያድ ባሬ ስርዓት ውድቀት የተመዘዘ መሆኑ የሚነገርለትና መሠረቱን በሶማሊያ አድርጎ የተቋቋመው ይህ ቡድን፣ ከታዋቂ አሸባሪ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለውም ይነገራል። በዚህም በፀረ ጽዮናዊነት የሚደረገውን የጅሃድ ዘመቻ በመቀላቀል የአልቃይዳ አባልና የምሥራቅ አፍሪካ ክንፍ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን፣ በምዕራብ አፍሪካ በስፋት ከሚንቀሳቀሰው ‹‹ቦኮ ሃራም›› የተሰኘ ታጣቂ ኃይል ጋርም ከፍ ያለ ትስስር እንዳለው እና ለዓለም ዐቀፉ የሽብር ቡድን አይኤስም ታዛዥ እንደሆነ ነው የሚገለጸው።

የሰሞኑ ጥቃት በሶማሊያዊያን ላይ መጠነ ሰፊ የሽብር ጥቃትና ትርምስ በመፍጠር ጎልቶ የሚታወቀው አልሸባብ፣ በኢትዮጵያም ጥቃት ለመሰንዘር የቆየ ፍላጎት እንደነበረው ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ እስከ ዘንድሮው 2014 ድረስ ድንበር ጥሶ በመግባት ግልጽ የሆነ ጥቃት ሲያደርስ አልታየም፣ ይህም የመጀመሪያው ነው።

በዚህ ወር በተለይም ከባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ ግን በሶማሌ ክልል፣ አፍዴር ዞን ድንበር ጥሶ በመግባት ወጊያ ከፍቷል። በዚህም በርካታ የቡድኑ አባላት መገደላቸውና በክልሉ ነዋሪዎች ላይም የሕይወትና የንብረት ጉዳት መድረሱን ክልሉ አሳውቋል። በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ፓርቲ ባወጣው መግለጫ፣ በሽብር ቡድኑ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጾ፣ የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን እንዲሁም የክልሉ መንግሥት በአልሸባብ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በአስቸኳይ እንዲወሰድ ጥሪውን አሰምቷል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ አልሸባብ በዚህ ወቅት ጥቃት የመሰንዘሩ ምክንያት፣ ቡድኑ በኅቡዕ የሚንቀሳቀስ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቋም ወደ ኢትዮጵያ ያስገባው አንድ አዛዥ በቅርቡ በመገደሉ ነው።

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላትም በድንበር አቅራቢያ ባደረጉት አሰሳ በርካታ የጦር መሣሪያ ተቀብሮ በማግኘታቸውና ይህን ተከትሎም የአልሸባብ አባላት ናቸው በሚል ጥርጣሬ ፖሊስ በርካቶችን በቁጥጥር ስር በማዋሉ ነው ቡድኑ ጥቃት የከፈተው የሚል መላምትም ይነገራል። ኢትዮጵያ በዋነኛው የአፍሪካ መግቢያ በር እንደመገኘቷና ካለችበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ያላት ውስጣዊ ደኅንነት በቀጠናው ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።

ምሥራቅ አፍሪካን የሽብር ቀጠና አድርጎ የቆየው አልሸባብ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ጥቃት መሰንዘሩም፣ በተለይ በገደል አፋፍ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት ገደል እንዳይከተው የሚሉ ስጋቶች በዝተዋል። በሽብርተኝነት የተፈረጁት ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ በሰሜን በኩል እንዲሁም በመሀል አገር የአገሪቱን ውስጣዊ ሰላም ችግር ውስጥ የከተቱ ሲሆን፣ በቅርቡም በምዕራብ በኩል የሱዳን ትንኮሳ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህ ወቅት በአራቱም አቅጣጫ የታጠቁ ኃይሎች በየጊዜው ጥቃት በሚያደርሱባትና አስተማማኝ ሰላም ባልሰፈነባት ኢትዮጵያ፣ ለውጭ ሽብርተኛ ኃይል ጥቃት መጋለጧ ነገሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል።

በአገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ታጣቂ ኃይሎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ የውጭ ሽብርተኛ አካላት መግቢያ በር እንዲያገኙ የሚረዳ መሆኑ በብዙዎች ይነሳል። ስለሆነም፣ እነዚህ ታጣቂ ኃይሎች በደርግና ኢሕአዴግ ዘመን እንኳን ሊተገብሩት ሊያስቡት የማይችሉትን የሽብር ተግባር በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ ሲፈጽሙ ይስተዋላል።

አል ሸባብም ከማሰብ አልፎ በኢትዮጵያ የጥቃት ተግባር መሰንዘሩ፣ በውስጥ ለሚንቀሳቀሱና ሰፊ በደል እየፈጸሙ ለሚገኙ ታጣቂዎች የልብ ልብ የሰጠውን የላላ የመንግሥት እርምጃ አወሳሰድ ተጠያቂ የሚያደርጉ አልጠፉም። ከዚህ ባለፈም አል ሸባብ ኢትዮጵያ ላይ የሰነዘረው ጥቃት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ተከትሎ፣ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በማገናኘት ከበስተጀርባ እነማን አሉ የሚለውን ጥያቄ የሚያነሱ አሉ። ይህም የግብጽ ምሥራቅ አፍሪካን የማተራመስ አንድ አካል ነው የሚሉ ሲኖሩ፣ በዚህ ወቅትም ቢሆን ከምዕራባዊያን ድጋፍ የሚያገኝ ኃይል ነው ብለው ምልከታቸውን የሚገልጹ ምሁራኖች ይደመጣሉ።

ከሰሞኑ ወደ ግብጽ ያቀኑትን የሶማሊያው አዲሱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ጉዳይን በማንሳትም፣ ግብጽ የሶማሊያን ወታደሮች በአገሯ ለማሠልጥን እና የቀይ ባህርን ደኅንነት በጋራ ለመቆጣጠር ኹለቱ አገራት መስማማታቸውን ተከትሎ፣ አል ሸባብ ካደረሰው ጥቃት በስተጀርባ በግልጽ ግብጽ አድፍጣለች ነው የሚባለው። በኢትዮጵያ በኩል ቡድኑ ተደምስሷል እየተባለ የሚነገረውም ቀጥሎ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በውል ባልታወቀበት ሁኔታ ነው ብለው ትችት የሚሰነዝሩ አልጠፉም።

እንዲሁም አል ሸባብን ማጥቃት ቢቻል እንኳን ከኢትዮጵያ ድንበር እንዲወጣ ማድረግ ብቻ ነው ወይስ እንደከዚህ ቀደሙ ሶማሊያ ድረስ ዘልቆ በመግባት ኢትዮጵያ ቡድኑ ላይ ጥቃት ትሰነዝራለች የሚል ጥያቄ ይነሳል። ይህ ከሆነ ደግሞ በግብጽ ግፊትም ይሁን በራሷ ተነሳሽነት ሶማሊያ ኢትዮጵያ ጥቃት እየፈጸመችብኝ ነው ስትል ክስ ልታቀርብ ትችላለች የሚል ስጋት አለ።

ስለሆነም፣ ሰሞነኛው የአል ሸባብ ጥቃት ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ የተረዱ አካላት ከበስተጀርባ ያሉበት ውስብስብ ሴራዎችን ያዘለና ያልታሰበ አደጋ ያነገበ ስለሚሆን፣ ከመንግሥት በኩልም ሆነ የኢትዮጵያና ሶማሊያን የታሪክና በድንበር አካባቢ ያለውን ሰፊ የሕዝብ ትስስር በመጠቀም፣ በሕዝብ ዲፕሎማሲው ጠንካራ ሥራ የሚጠይቅ እንጂ፣ ድንበር ጥሶ የገባው አል ሸባብን ደምስሰነዋል ተብሎ በቀላሉ የሚገለጽ እንዳልሆነ ነው የዘርፉ ምሁራን የሚያስገነዝቡት።

በሶማሌ ክልል የድንበር አካባቢዎች ሰፍሮ የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ ልዩ ኃይል ተተክቶ የቆየ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ግን ሠራዊቱ ወደ ቀድሞ ቦታው መመለሱ ተሰምቷል። በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ታደሰ አክሎግ (ፒኤችዲ) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ለኢትዮጵያ ስጋትም እድልም መሆኑን በማንሳት በአግባቡ ካልተያዘ ግን ጉዳቱ ያመዝናል ነው ያሉት።

ከሰሞኑ የተፈጠረውን የአል ሸባብ ጥቃት አስመልክቶም፣ ሶማሊያ መፈረካከስ ከገጠማት ከ1980ዎቹ ጀምሮ አገሪቱ የተለያዩ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ማንፀባረቂያ ሆና እንደቆየች በማውሳት አሸባሪው ቡድንም በእነዚህ አካላት እንደሚዘየር ሳይጠቅሱ አላለፉም። ስለሆነም፣ ቡድኑ ለምን በዚህ ወቅት ጥቃት መሰንዘር አስፈለገው ለሚለው፣ የአይኤስን በምሥራቅ አፍሪካ መስፋፋት እንዲሁም የኢትዮጵያን ውስጣዊ መዳከም እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ጥቃት መሰንዘሩ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም ከአንዱ ምስቅልቅል ወደ ሌላው ምስቅልቅል እየተሻገረች ነው፣ እንደ ግብጽ ላሉ አገራትም ይህ የአገራችን መዳከም ሲበዛ መልካም አጋጣሚ ነው የሚል እምነታቸውን አጋርተዋል። ‹‹ሰሞነኛው የአል ሸባብ ጥቃትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፣ እንደ ሽብርተኛ ሰርጎ ሳይሆን ተደራጅቶ በተሽከርካሪ ነው የገባው። ለምንስ ድንበር ጥሶ እስኪገባ ድረስ እድል ተሰጠው?›› ካሉ በኋላ፣ አገራችን ለጎረቤቶቿና ለአፍሪካ አለኝታ መሆን ሲገባት በተቃራኒው ራሷን መከላከል የሚያቅታት ደካማ አገር ስትሆን እያየን ነው ይላሉ።

- ይከተሉን -Social Media

በዚህም በምሥራቅ አል ሸባብ፣ በምዕራብ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች እንዲሁም የሱዳን ኃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ስጋት ውስጥ መክተታቸውን አስገንዝበዋል። በአገራት መካከል ቋሚ ጠላትና ወዳጅ የሚባል ባይኖርም፣ ኢትዮጵያ ግን በአባይ ተፋሰስ ጉዳይ ቋሚ ጠላት አፍርታለች ያሉት መምህሩ፣ እነዚህ ቋሚ ጠላቶች ደግሞ በተዳከምን ጊዜ ነው ጥቃት የሚያደርሱት ሲሉ ይገልፃሉ።

ከዚህ የአል ሸባብ ጥቃት ጀርባ ግብጽ እንደምትኖር ምንም ጥርጥር የለውም ሲሉ አክለውም፣ እንደማሳመኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ትንሽ የሐይማኖት ግጭት ሲነሳ ነገሩ በፍጥነት ግብጽ ደርሶ በመገናኛ ብዙኀን ሲሰራጭ እናያለን። ይህ ደግሞ ጉዳዩን እንደሚከታተሉት፣ እንደሚደግፉትና እንደሚያቀነባብሩት ይመሰክራል። አሁንም ግብጽ ኢትዮጵያን ለማዳከም አል ሸባብን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አጋጣሚዎችን ሁሉ ትጠቀማለች ይላሉ። የግብጽ ተንኮል በኢትዮጵያ ብቻ ያልተገደበ መሆኑን በማንሳትም፣ በዩጋንዳ፣ ሩዋንዳና ብሩንዲ ሳይቀር ሴራ እንደምትሸርብ ጠቅሰው፣ እንዲሁም የአባይ ተፋሰስ አገራትን በኢትዮጵያ ላይ እንዲነሳሱ ማድረግ ቋሚ ፖሊሲዋ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ለደቡብ ሱዳን ነፃነት ማግኘት ትልቁን ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያ ሆና ሳለ፣ ግብጽ በምትሠራው ፖለቲካ በመርፌ ቀዳዳ ሾልካ በመግባት የአገራችን ጠል የሆኑ ኃይሎችን ፈጥራለች ነው ያሉት። ስለሆነም፣ ግብጽ ኢትዮጵያን ይጎዳል ባለችው ነገር ላይ ኹሉ ወደ ኋላ ብላ አታውቅም። አገራችንም ሉዓላዊነቷን ማስከበርና ጥቅሟን ማስጠበቅ እየተሳናት ነው። ይህም የሆነው ግብጽ ስለበረታች ሳይሆን እኛ ኃላፊነታችንን ሳላልተወጣን ነው የሚል እምነት አላቸው። መምህሩ አክለውም፣ ‹‹የሚገርመው እንደ ግብጽ ያሉ አገራት የኢትዮጵያ ተፃራሪ ሆነው መቆማቸው አይደለም፣ የሚገርመው እኛ በዚህ ልክ ማንቀላፋታችን ነው›› ይላሉ።

እንደ አገር ትልቅ አደጋ ውስጥ ገብተን እያለ በተለይ ኃላፊነት የተጣለባቸው ፖለቲከኞች አገርን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚወስደውን ትልቁን መርከብ ከመንዳት ይልቅ፣ ተራ የግል ጥቅምና የጎሳ ፖለቲካ በሞላባቸው ትናንሽ መርከቦች ተሳፍረዋል ነው ያሉት። ኢትዮጵያም ለብሔራዊ ጥቅማቸው ከሚተጉ እንደነ ግብጽ ካሉ አገራት በተቃራኒ በአንድነት መቆም ተስኗቸው ብሔራዊ ጥቅማቸውን እያጡ ያሉ የሚፍረከረኩ መሪዎች የሞሉባት አገር ነች ብለዋታል። አይደለም በአረቡ ጎራና በመላው ዓለም ተደማጭነት ያላት ቋሚ ጠላት የሆነችዋ ግብጽ፣ ትናንሽ የሆኑ እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኤርትራ ያሉ አገራት ሳይቀር በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱት የሉዓላዊነት ስጋት ቀላል እንዳልሆነ ነው ያስገነዘቡት።

ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የሉዓላዊነት ስጋት የሕዝብና የመገናኛ ብዙኀን መወያያ አጀንዳ በመሆን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ስለመሆኑ አንፅንኦት ሰጥተዋል። ቡድኑ ተደምስሷል የሚባለው ምን ያህል እውነት ነው? ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ጥሶ የገባው የአል ሸባብ ቡድን ከተገደሉበት ከ200 በላይ አባላት በተጨማሪ ብዙዎች እንደተማረኩ እና በርካታ የጦር መሣሪያ ቁሳቁሶችን ማስረከቡም በተለይ በሶማሌ ክልል በኩል ተገልጿል። ይሁን እንጂ፣ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አሸባሪዎች ሰንሰለታቸው ሰፊና ውስብስብ ነው።

ደመሰስን የሚባለውም ግልፅ በሆነ ድንበር የኹለት አገራት ሠራዊት ሲዋጋ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። አክለውም ‹‹አል ሸባብም በየትኛው ግንባር እንደሚመጣም ሆነ በስውር ስላደራጃቸው ወጣቶች አናውቅም። ማኅበረሰቡን መስሎም ይቀመጣል። ስለዚህም ደምስሰነዋል ማለት አይቻልም›› ነው የሚሉት። ‹‹ደምስሰነዋል ብሎ መናገር ማሞኘት ነው። ከአሁን ቀደምም ኦነግ ሸኔን ደምስሰነዋል እየተባለ ዜጎች ከመሞት አልዳኑም›› ሲሉ ገልጸዋል። የአሸባሪ ቡድኑን የአደረጃጀት ስርዓት፣ የፋይናንስ ምንጭ በተጨማሪም የማሠልጠኛ ጣቢያዎቹን በማምከን ጠራርጎ ማጥፋት እስካልተቻለ ድረስም ደምስሰነዋል ማለት እንደማይቻል ነው የገለፁት።

የሽብር ቡድኑ ዓላማ ምንድን ነው? የሶማሌ ብሔራዊ ክልል የቡድኑን ጥቃት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የአል ሸባብ ዓላማ ‹‹በክልሉ በኤልከሬ ወረዳ በኩል አልፎ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት ከሸኔ ሽብርተኛ ቡድን ጋር ለመገናኘት አልሞ ነበር›› ሲል አመላክቷል። በመንግሥት በኩል ይህ ዓላማውም እንዲከሽፍ ተደርጓል ነው እየተባለ ያለው። ‹‹የአል ሸባብ ዓላማና ጥቃት በቀላሉ አክሽፈናል የሚባል አይደለም›› የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ግን፣ ቡድኑ ከማተራመስ ያለፈ ዓላማ ነው ያለው ሲሉ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ የኃይል የበላይነትን ማረጋገጥ ለሚፈልጉ ኃይሎች ምቹ ነው ይላሉ።

አክለውም፣ በአገራችን ሐይማኖታዊ የሚመስል አደረጃጀት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በመኖራቸውም፣ የሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ ሆኗቸው ጥምረት በመፍጠር የሚፈልጉትን የፖለቲካ ቅርፅ በመያዝ የማይጓዙበት ሁኔታ የለም ነው ያሉት። ከዚህ ቡድን ጋር የኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎች እንዳሉ መስማታችንም ጉዳዩ ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም ሲሉ አብራርተዋል። አል ሸባብ የሶማሊያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ኃይል ነው ከተባለ እንኳን፣ የቀድሞው ተስፋፊ የአገሪቱ መንግሥት አጀንዳ አራማጅ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ስለዚህም፣ ኦጋዴንን መንጠቅ በትንሹ ሊያደርገው የሚችለው ነው። ይህ ትንሹ ሙከራው ይሁን እንጂ የሚመክተው ኃይል ካላገኘ የተከፋፈለውን ማኅበረሰብ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን የማጥለቅለቅና ከፍተኛ ቀውስ የመፍጠር እድል ይኖረዋል ባይ ናቸው። በኢራቅና ሶሪያ መሠረቱን ያደረገው አይኤስ (Islamic State of Iraq and Syria) የሽብር ቡድንም ቢሆን፣ የሽብር አድማሱን አስፍቶ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይም ጥቃት የመሰንዘር ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ይነሳል።

ከአሁን ቀደምም በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግሥት ከአል ሸባብ አባላት በተጨማሪ የዓለም ዐቀፉ የሽብር ቡድን አይኤስ አባላት በዋናነት አዲስ አበባ ውስጥ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ያዝኳቸው ማለቱ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም አል ሸባብን ለማጥፋት ባደረገችው እንቅስቃሴ በርካታ ወታደሮቿን የገበረች ሲሆን፣ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዝብ ከካዝናዋ አጉድላለች። አሁንም ቢሆን በአገሪቱ በርካታ አፍራሽ የሆኑ የተደራጁ ታጣቂዎች መኖራቸውን ተከትሎ፣ ለቡድኑ እኩይ ዓላማ መሳካት ይህ ትልቅ እድል እንደሚሆን በማሰብ አል ሸባብ ዋና የኢትዮጵያ ስጋት እንደሚሆን የብዙዎች ግምት ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች