መነሻ ገጽዜናየእለት ዜና"የታሰርኩት በኮንዶሚንየም ቤት ዕጣ አወጣጥ ላይ የትግሬ ሥም በዝቷል ተብሎ በብሔሬ ምክንያት...

“የታሰርኩት በኮንዶሚንየም ቤት ዕጣ አወጣጥ ላይ የትግሬ ሥም በዝቷል ተብሎ በብሔሬ ምክንያት እንጂ ወንጀል ፈጽሜ አደለም” ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ

ሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የታሰርኩት በኮንዶሚንየም ቤት ዕጣ አወጣጥ ላይ የትግሬ ሥም በዝቷል ተብሎ በብሔሬ ምክንያት እንጂ ወንጀል ፈጽሜ አደለም ሲሉ የአ/አ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊው ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ ምሩፅ ለፍርድ ቤት ገለጹ።

ዶ/ር ሙሉቀን በሐምሌ 1 ቀን 2014 ወጥቶ በተሰረዘው የ14 ና ዙር 20/80 እና በ3ኛ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ አወጣጥ ጋር ተያይዞ ሲስተም ውስጥ ያልቆጠቡ ግለሰቦች እንዲካተቱ ተደርጓል ተብሎ በቀረበ ቅሬታ መነሻ ተጠረጠረው ከ14 ቀን በፊት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ ዛሬ ለ2ኛ ጊዜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

የፌደራል ፖሊስ መርማሪ በሐምሌ 11 ቀን በነበረ ቀጠሮ ለተጨማሪ ምርመራ በተሰጠው 14 ቀን ጊዜ ውስጥ የሰራውን የምርመራ ውጤት ለችሎቱ አብራርቷል።

የተጠርጣሪውን የጣት አሻራ ማስነሳቱን እና ተጠርጣሪውን የማነጋገር ሥራ መስራቱን፣ ከንግድ ባንክ የቆጣቢዎችን ዝርዝር ጠይቆ በሲዲ እንደተቀበለ፣ ከኢኖቬሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዝርዝር ኦዲት ተሰርቶ እንዲላክ መጠየቁን፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲስተሙ ሲለማ ድጋፍ አድርገዋል የተባሉ ኹለት ባለሙያዎች ጠርቶ ማነጋገሩን እንዲሁም ዕጣው የወጣበትን ሲስተሙ የተጫነበትን ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ተያያዥ ማስረጃዎችን ከከተማ አስተዳደሩ ወስዶ ለቴክኒክ ምርመራ ለኢንሳ መላኩን ለችሎቱ ገልጿል።

በተጨማሪም እጣው እንዲሰረዝ መነሻ የሆነው ኦዲት ሪፖርት ከከንቲባ ጽ/ቤት ማምጣቱን፣ እንዲሁም ከተጠርጣሪ መኖሪያ ቤት በብርበራ የተገኙ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ለቴክኒክ ምርመራ መላኩን ያስረዳው ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ማስረጃዎችን መሰብሰቡንም ለችሎቱ አብራርቷል።

ቀሪ ያላቸውን ምስክር የመቀበል ሥራ፣ የሶፍትዌር ባለሙያዎችን እና የኦዲተሮችን ቃል መቀበል ሥራ እንደሚቀረው ገልጿል።

እንዲሁም እየተከናወነ ያለ የሀብት ምርመራ ውጤት ተከታትሎ ማምጣትና የመዝገቡ አካል የማድረግ ሥራ እንደሚቀረው የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፤ ያለአግባብ በዕጣው የተካተቱ ግለሰቦችን በማጣራት ከተጠርጣሪው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ዝርዝር ምርመራ የማከናወን ሥራ እንደሚቀረው በመግለጽ እንደ አጠቃላይ የቴክኒክና ተያያዥ ማስረጃዎችን ከሚመለከታቸው ተቋማት የማምጣት ሥራ እንደሚቀረው ለችሎቱ አስረድቷል።

መርማሪ ፖሊስ ወንጀሉ ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር በተደራጀ ሁኔታ የተፈጸመ መሆኑን እና ውስን በሆነ የህዝብ ሀብት ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን የተሰበሰቡ ማስረጃዎች ያሳያሉ ሲል፤ ምርመራው በተገቢው ሁኔታ ማከናወን እንድንችል እና ምርመራውን በሰውና በሰነድ ለማረጋገጥ እንድንችል በወ/መ/ህ/ስ/ቁ 59/2 መሰረት የጠየቅነው ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይፈቀድልን ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው ዶ/ር ሙሉቀን በበኩላቸው ስፍትዌሩ የመልማት ሥራውን ከንቲባዋ ባሉበት ከቤቶች ዳታ መቶ ሙከራ ተደርጎ ከንቲባዋ ጥሩ ነው ሲሉ መግለጻቸውንና ግልፅነትን ፈጥረናል ማለታቸውን አስታውሰዋል።

እንደ አጠቃላይ በዕጣው የትግሬ ሥም በዝቷል ተብሎ ነው በብሔሬ ምክንያት ነው የታሰርኩት እንጂ ምንም ወንጀል ሰርቼ አደለም ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ ሞላልኝ መለሰ በበኩላቸው፤ የፖሊስ የጥርጣሬ መነሻ እና የቀረበው ሪፖርት ተጠርጣሪውን አስሮ ለማቆየት የሚይስችል አሳማኝ ምክንያት አደለም ሲሉ ተከራክረዋል።

ቀሪ ሥራ የተባለውም ቢሆን ከተጠርጣሪው ጋር የሚገናኝ አደለም ሲሉ የተከራከሩት ጠበቃ ሞላልኝ መለሰ በሌሎች የሚከናወን ምርመራ እንጂ በዚህ መዝገብ የሚደረግ ወይም የሚሰበሰብ ማስረጃ አደለም ሲሉ በመከራከሪያ ነጥባቸው ጠቅሰዋል።

የተጠቀሰው ቀሪ የምርመራ ሥራ ተጠርጣሪውን በእስር እንዲቆይ የሚያስችል አደለም ብለዋል።

ምርመራ ሲደረግ ተጠርጣሪን ጥፋተኛ ለማለት ብቻ ሳይሆን የተጠርጣሪንም ነጻነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አጠቃላይ ዶ/ር ሙሉቀን የተጠረጠሩበት ወንጀል በራሱ የዋስትና መብትን እንደማይከለክል የገለጹት ጠበቃው ዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የጊዜ ቀጠሮ መፈቀድ አለበት ወይስ መፈቀድ የለበትም የሚለው ፍርድ ቤቱ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት መቅጠሩን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።

- ይከተሉን -Social Media

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች