ሐሙስ ሐምሌ 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአሜሪካ ኦሬገን በተካሄደው 18ኛው አለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛ በመውጣት አመርቂ ውጤት ላስመዘገበው የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን የዕውቅና፣ የምስጋናና የማበረታቻ ሽልማት መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት አከናውኗል።
በመርሃ ግብሩ ላይም የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት፣ የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድኑ አባላት፣ አንጋፉ የአገራችን አትሌቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚህም መሰረት፤ በአሜሪካ ኦሬገን በተካሄደው 18ኛው አለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፈው ለአገራችን፦
* የወርቅ ሜዳሊያ ላስገኙ አራቱ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ60 ሺህ ብር የገንዘብ ስጦታ
* የብር ሜዳሊያ ላስገኙት አራት አትሌቶች (የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችውን ጉዳፍ ፀጋዬን ጨምሮ) ለእያንዳንዳቸው የ40 ሺህ ብር ስጦታ
* የነሀስ ሜዳሊያ ላስገኙት ኹለት አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ30 ሺህ ብር ስጦታ
*እንዲሁም ዲፕሎማ ላገኙ 10 አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር ስጦታና ለተሳተፉ 16 አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ7 ሺህ ብር የገንዘብ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ የፌደሬሽኑ አመራሮች፣ አሠልጣኞች እና የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድኑ መሪዎች በየደረጃቸው የተለያዩ የገንዘብ ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል።
በአሜሪካ ኦሬገን በተካሄደው 18ኛው የአለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 4 ወርቅ፤ 4 ብር እና 2 ነሃስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን መሰብሰቧ ይታወቃል።















