ብሔራዊ “አለመግባባት”

0
332

ቤተልሔም ነጋሽ ሰሞኑን በአንዳንድ ባለሥልጣናትና የመብት አራማጆች የተፈጠሩ እሰጣ ገባዎችንና ንትረኮችን እንዲሁም የተፈጠሩ ኩነቶችን በማንሳት ለእብደት እየዳረጉን ነው ሲሉ ያማርራሉ፤ መፍትሔውም መቆጨት ነው ሲሉም አመላክተዋል።

 

 

የሰሞኑን ዙሪያ መለስ ትርምስና ብዙ ትክክል ያልሆኑ ጉዳዮች ችላ ሲባሉ ላየ፤ ከግራ ቀኝ ከሚያስማማ ይልቀ የሚያራርቅ ንግግር ከመብት አራጅ (አክቲቪስ) ነኝ ባይ የማኅበራዊ ሚዲያ አርበኞች እስከ የክልል ባለሥልጣናት ሲያሰሙ ሲታይ፣ በአንድ ወረዳ 50 ሴቶችን በጅምላ እየደፈረ፣ ባሎቻቸውን ጭምር እያሠረ አካባቢውን ካሸበረ በኋላ ተይዞ በዋስ ሲለቀቅ፣ በየአቅጣጫው ቀናነት ሲጎድል “እውን ይህቺ አገር ተስፋ አላት?” “እንደው መጨረሻችንስ ምን ይሆን? ያስብላል። ይህ ጽሑፍ የሰሞኑ ብሶት የወለደው ሐተታ ነው። ቁም ነገር ብታጡበት፣ የምታውቁት ያያችሁት ቢደገም አትገረሙ።

የመጀመሪያው እብደት እያደገ የመጣው ብሔራዊ “አለመግባባት” አንድ ምሳሌ የሚሆን ግርግር ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ የተከበረው ኢሬቻ (ሆራ ፊንፊኔ) በዓል ያከተለው አላስፈላጊ እንካ ሰላንቲያ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ሲሰነዘሩ ከነበሩ የአዲስ አበባ ነዋሪ “አይኑ ቀላ” ትርክትና “እኛና እነሱ” መከፋፈል ላይ የሰጠሁት መልስ ነው። “ቻሉት እንግዲህ በየዓመቱ እናደርገዋለን ምናለ ደስ ብሉዋችሁ ብታከብሩ” ስንባል ቅሬታ ሲያሰሙ አካላት አንዷ ነበርኩና ወቀሳው ሲበዛ መልስ መስጠት ይገባል ብዬ ያልኩት ኹለት ዋና ዋና ነገር ነበር። አንደኛው በጥቅሉ ቅሬታ አታቅርቡ ማለት የማይቻልበት የመንገድ መዘጋት ጉዳይ ነው። በዓሉ ቅዳሜ እንደሆነ ገምተን ሳለ አርብ ጀምሮ አብዛኛው የአዲስ አበባን ክፍለ የሚሸፍኑት አደባባዮችና ዋና ዋና መንገዶች እንደሚዘጉ የሰማነው ሠራተኞች ሥራ ገብተን ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ሔደው ነው። በየትኛውም ወቅት ከሚደረገው በብዙ እጥፍ የበዛ መጠነ ሰፊ የመንገድ መዘጋት (ያልተዘጋውን ንገሩን እስኪባል) የተነገረበት መንገድ፣ ጊዜው ግድ የለሽ ድርጊት ነው የሚስብል ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ነገር ኹለት ሦስት ጋዜጠኞች ጠርቶ ነገ ሊሆን ማታ ላይ ለሚሠራ ዜና መግለጫ በመስጠት የሚገለጽና የሚሠራ አይደለም። ሲጀመር አብዛኞቹ አደባባዮችና ወደ ከተማዋ የሚስገቡ መንገዶች ከእኩለ ቀን ጀምሮ ሲዘጉ ሠራተኛና ተማሪው፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠረው አዲስ አበቤ ወደ ቤቱ እንዴት ይመለሳል የሚለውን ለማሰብ ሊቅ መሆን አይጠይቅም፣ ሲቀጠል ደግሞ ይህንኑ መረጃ አስቀድሞ ቢያንስ በሞባይል አጭር የጽሑፍ መልዕክት ማስተላለፍ ለምን አልተቻለም።

በዓሉ በተከበረበት ዕለትም ፕሮግራሙ ምን እንደሆነ ዝርዝሩ የሚበቃበት ሰዓት ጭምር አልተገለጸም፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ይህንኑ ለመጠየቅ የሞከሩ ሰዎችም ምን ቆርጧችሁ እናንተ የብሔራችን ጠላቶች ተባሉ። ከክፍለ ሃገር ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ በርካታ አውቶብሶችን ጨምሮ በከተማው ምንም ዓይነት ትራንስፖርት ሳይኖር የአዲስ አበባ ነጋዴዎች “ሕዝቡን አገልግለው መጠቀም ሲችሉ ሱቅ ዘግተው አመፁ” ተባለ። ከዋዜማው ጀምሮ ከተማው የገዳ ቀለሞች ናቸው በተባሉት ባንዲራዎች አሸብርቆ ሲያጌጥ፤ በየቦታው ስለ በዓሉ መግለጫዎች ተጽፈው ሲስቀሉ፤ በበኩሌ ካየኋቸው መካከል የትኞቹም ከኦሮምኛ ቋንቋ ውጪ የተፃፉ አልነበሩም። በበኩሌ እንደ ግለሰብ ባለፉት 15 ዓመታት አዲስ አበባን ቤቴ ብዬ ብኖርም ከየትኛውም የኢትዮጵያ ከተሞች በወሬ ሳይሆን በተጨባጭ ባለ ብዙ ባሕል ኅብረ ብሔራዊ በሆነችው ሐረር ከተማ ሳድግ ድሮ ገና የኦሮሞን ባሕል ባሕሉ አድርጎ “አቴቴ”ን ተቀብሎ የራሱ ያደረገ ማኅበረሰብ አካል ነበርኩ።

የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫና የአገሪቱም ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ የሁሉም እንደመሆኗ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሁሉም ባሕል የሚንፀባረቁባት፣ አገሪቱን የምትመስል ሁሉን ያካተተች ብትሆን ምኞቴ ነው ብቻ ሳይሆን መሆን ያለበትም እንደዚያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩትና በዚህ ጋዜጣም እንደተዘገበው ተጨማሪ የፌደራል የሥራ ቋንቋዎች የሚያስፈልጉንም፣ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለንን ሥራ መጀመር ያለብን ግን ለዚህ ነው። አልያ በሕዝብ ቁጥር ስለምበልጥ የእኔ ነች ቋንቋውም ባሕም የእኔ ይሁን ሌላውን አልይ ማለት ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። እናድርግ ቢባልም በቀላሉ የሚቻልና የሚሆን አይደለም።

ባለፈው ሳምንት ያየነው ነገር እውነቱ እነኝህ ሰፊውን የአዲስ አበባ ሕዝብና ይወክሉታል ያሉትን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለ አዲስ አበቤ እንደሚወነጅሉት ያለ ጥቁረት እና ነጭ እኛ ጥፋት የለብንም ችግሩ የእናንተው ነው ዓይነት ጩኸቴን ቀሙኝ ውንጀላ ቀላልና ቀጥተኛ አይደለም። እነሱ እንደሚሉት ከያለንበት መጥተን አዲስ አበባን ቤታችን ያልን ተጨምረን የአዲስ አበባ ሕዝብ በጭፍን ኦሮሞን የሚጠላ ኢሬቻ አዲስ አበባ በመምጣቱ (የታሪክ ድርሳን ማጣቀሱ ስለማይጠቅም) የተበሳጨ አይደለም። ይልቁንም “ሆራ ፊንፊኔ” የተቀነበበበት ትርክት፣ ፕሮግራምና ድርጊት ጨርሶ ሌሎችን የሚጋብዝ ሳይሆን የሚያርቅና የሚያስከፋ ነበር። ይኸው አባባሌን የሚያስረግጥልኝ ምሳሌ፣ ልተወው ብወድም እሺ የማይለኝ ሁላችንም እንድናየው እንድንሰማው ተተርጉሞ የተነገረን ከፋፋይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ትርክት ነው። “እኛ” እና “እናንተ” አሸናፊና ተሸናፊ ሰባሪና ተሰባሪ ሲዘረዘር፣ ሌላው ተሰሚነት ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ ፖለቲከኛ ምላሽ ሲሰጥ ጭምልቅልቅ ሲል ማየት አሳዛኝ ነበር። ሌላው ጉዳይ በመስቀል ከባበር ወቅት ከፍተኛ ጥብቅ ቁጥጥር ኖሮ ከተፈቀደው የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ውጪ አንድም እንዳይገባ፣ የቤተክርስቲያን ከበሮ የታሰረበት ሳይቀር እየተፈታ (የባንዲራው ቀለም የቤተክርስቲያኗ አርማ መሆኑ ተረስቶ) ወደ አደባባይ እንዳይገባ ሲደረግ በኢሬቻ አከባበር ላይ ግን የኦነግ ባንዲራ በቴሌቪዥን ሲውለበለብ ስናይ አንዱ “ልጅ” ሌላው “እንጀራ ልጅ” ነው ወይ ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። ከዛም ያንን ድርጊት የሚቃወመው ወገን እንደሚለው የ“ተረኝነት” መንፈስ ገባብን ይሆን ያስብላል።

በአወዛጋቢው በኢሬቻ አከባበር ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኋላ መጥተው በአዎንታዊ ቃላትና ምሳሌ የታጀበ ንግግር አድርገው ሕዝቡን ያረጋጉታል ቢባልም ከወደዚያ የወጣ ምንም መረጃ የለም። ይልቁንም ጽሕፈት ቤታቸውን እና ቤተ መንግሥቱን በቢሊዮኖች በማደስና “የአንድነት ፓርክ” በመገንባት ሥራ የተጠመዱ ይመስላል። ለዚህ ነገር የምሰጠው አስተያየት ከዚህ ቀደም ለዜጎች መፈናቀል ተሰጥቶ የነበረውን የዝምታ ምላሽ አስመልክቶ በጻፍኩት ጽሑፍ ያስቀመጥኩትን በመድገም ነው።

“እንደ ሰጎን አንገትን ከአሸዋ ውስጥ ቀብሮ ችግሩ በኖ ይጠፋል ብሎ ተስፋ የማድረግ፣ እስኪያልፍ የመደበቅ ዘመን አልፏል” ይላል በቀውስ ወቅት መደረግ ያለበትን የተግባቦት ሒደትና እና ቶሎ ቶሎ መረጃ የመስጠት አስፈላጊነት የሚያትት አንድ ጽሑፍ። ጽሑፉ በአብዛኛው ተቋማት ችግር ውስጥ በሚገቡ ጊዜ ወቅታዊ መረጃ ባለመስጠታቸው የገቡበትን ጣጣ ሲተነትን ብዙ ዋጋ እንደከፈሉበትም ጭምር በማተት ነው።

ዓመት ባለፈውና የእውነትም ለውጥ እንደነበር እያጠራጠረን በመጣው የለውጥ አየር ወቅት የተግባቦትና መረጃ የመስጠት ሒደት እንደሚቀየር ሰምተን አምነን ነበር። “በግልጽ እንጂ በድብቅ የሚሆን የለም” ከተባልን በኋላ “የምንናገረው፣ መረጃም የምንሰጠው እኛ በፈለግነው አጀንዳ ላይ ነው” ማለት የሚመስል ዝምታ በተደጋጋሚ አይተናል።

ሰው ሠራሽ ቀውስና ግጭት ሊያስከትል የሚችል ነገር ሲከሰት የመረጃ መስጠት፣ የማስተካከል፣ ትክክል ያልሆነውን የመናገር ሥራ ማከናወን አንድ ከሚያደርገው ይልቅ የሚከፋፍለው የበዛበትን ሕዝብ ያረጋጋል።

ቆይ ፀጥ ልበልና ልየው፤ ተደብቄ ላሳልፈው ዓይነት አካሔድ በተለይ ፍትሐዊ ምርጫና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ባሉበት የሚታሰብ አይደለም፤ ነገ በምርጫ ካርድ መወገድን ሊያመጣ ይችላልና። ዛሬ ያለህን ሥልጣንና ተሰሚነት ተጠቅመህ ድጋፍ እንዳገኝ ካላደረክ ያንተ መሪነት ምኔ ነው መባልም አለና።

ሌላው አሁንም ብዙ ጣጣ እንደሚጠብቀን የሚመለክተው የቅማንትና አጎራባቹ የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል ያለው እያደር የሚያገረሽ ግጭት ነው። ከወራት በፊት ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ በብዙ ሺሕዎች መፈናቀል የጀመረው የግጭቱ ሁኔታ ዛሬ እንደገና ተከስቶ ክልሉ በተፈፀመ ድንገተኛ ጥቃት 53 የልዩ ኀይል አባላት መገደላቸውን ገልጿል። የክልሉ መንግሥት ፌደራል መንግሥት ከአቅሜ በላይ ሆኗል አግዙኝ ብሎ ላቀረበው ጥያዌ ምላሽ አልሰጠኝም ብሎ በተደጋጋሚ ከሷል።

ሰሞኑን ፌደራል መንግሥቱን እከሳለሁ እያለም ነበር። አለባብሰው ቢርሱ በአረም ይመለሱ የቀረልን ይመስልም። ለማረም ዝግጁ የሆነ ካል ግን በመንግሥትም በፓርቲም እያየን አይደለም። እዚህ የደረስነው ባጭሩ ሊቀጩ የሚገቡ ማንአለብኝነቶች ስላልተቀጩ፣ መታረም የነበረበባቸው በወቅቱ ባለመታረማቸው ነው።

ስለማረም ሳነሳ ጽሑፌን የምቋጨው ነገሬን የሚስረዳልኝን ዳንኤል ክብረት “እያረምን ወይስ እያበድን እንሒድ” በሚለው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋራው ጽሑፍ ነው። ዓውዱን ለመጠበቅ ከጽሑፉ ቀንጨብ አድርጌ ከነአባባሉ አስቀምጣለሁ።

ገበሬው ለሙግት ወደ ሸንጎ ሔዶ ሲመጣ የገዛ ወዳጆቹ የዘራውን እህል ሳያርሙ፣ ሳይኮተኩቱ ጠበቁት። ማሳውን እያየ ያብዳል። እንዴት እንደዚህ ይደረጋል? ይህን ያደረጉት እነ እንቶኔ ናቸው? ይህን ያደረጉት እኔን ሊጎዱ ነው? ድሮም እነርሱ አይወዱኝም ነበር፤ በቃ የሰው ነገር መጨረሻው እንደዚህ ሆነ ማለት ነው? በቃ የእርሻዬ ነገር አበቃለት ማለት ነው? እያለ ፀጉሩን እየነጨ ያብዳል።

አንድ ሽማግሌ ከሩቅ አይተውት መጡ። እየዛበረ የሚናገረውን ሰሙ። ከዚያም “እባክህ ረጋ በል” አሉት። “ምን ረጋ እላለሁ፤ እንዲህ ሲሆን እያዩት፤ ከዚህ በኋላ ምን ተስፋ አለኝ” እያለ ሲጮኽ ሽማግሌው ሰሙትና “ወዳጄ ይህ ሁሉ ቢሆንም፣ እያረምን እንጂ እያበድን መሔድ አለብን እንዴ” አሉት አሉ።

ኢትዮጵያም እንዲህ ነው እየሆነች ያለችው። አንዱ ስንዴ፣ ሌላው እንክርዳድ ይዘራል፤ አንዱ ያቀናውን ሌላው ሊያጣምመው ይተጋል። በዚህ ሲደፈን በዚያ ይቦተረፋል፤ ራስ ሲነቃ እግር ይጎተታል፤ ብዙዎቻችን እንደዚያ ገበሬ የምናየውና የምንሰማው ለእብደት እየዳረገን ነው። ማበድ ግን አገር አያቀናም። መቆጨት እንጂ መናደድ መፍትሔ አያመጣም። አበቃ፣ አለቀ፣ ደቀቀ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ ሔደ፣ አከተመ፣ ነጠፈ፣ ተሟጠጠ እያሉ ማለቃቀስ ነገሩን አይቀይረውም።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here