ባለትዳር የቤት ዕድለኞች ሥማቸውን በማስቀየር እንዳስቸገሩት ንግድ ባንክ ገለፀ

0
619

በየካቲት 2012 ላይ በወጣው የጋር መኖሪያ ቤቶች እጣ መሰረት ቤቶች ለእድለኞች በመተላለፍ ላይ መሆኑን ተከትሎ 40 በመቶ የቆጠቡት ባለ እድለኞች 60 በመቶውን ያበደረው ንግድ ባንክ ውል በሚፈፀምበት ወቅት በተለይ ባለትዳር የቤት ባለእድለኞች ሥም በማስቀየር እና ፍቺ ጭምር በመፈፀም ሰነድ በማቅረብ መቸገሩን አስታወቀ።

ባንኩ ይዞት የቆየውን ሥም እና የጋብቻ ሁኔታ በፍርድ ቤት በተረጋገጡ ሰነዶች ይዘው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን መጨመሩን ያስታወቁት የባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ያብስራ ከበደ፣ የግል መጠሪያ ሥማቸውን ከማስቀየር ባሻገር የአባት፣ የአያት እንዲሁም የእናት ስማቸውን በፍርድ ቤት በመለውጥ አስወስነው ንግድ ባንኩ መረጃውን እንዲያስተካክልላቸው አቅርበዋል፣ አሁንም በማቅረብም ላይ ያሉ አሉ ሲሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር አማካኝነት 18 ሺሕ 576 የ40/60 የጋራ መኖሪያ ኮንደሚኒየም ቤቶች እጣ መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን ከሰኔ ወር ጀምሮ የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶች ምዝገባን ያከናወነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመሔድ የቤቱን ዋጋ አርባ በመቶ ክፍያ በማጠናቀቅ ቀሪ 60 በመቶ የቤቱን ዋጋ ከባንኩ ጋር የብድር ውል በማድረግ የቤት ርክክብ ሒደቱን ማከናወን ተጀምሯል።

የቤቱን ርክክብ ለመፈጸም እጅግ በርካታ የቤት እድለኛ ግለሰቦች፣ በቀድሞ ሥማቸው የተመዘገበ ቤት ቢኖራቸው በዚያ ሳቢያ ኮንደሚኒየሙን እንዳያጡት በሚል ያደረጉት ነው የሚል ስጋትን በባንኩ ላይ ፈጥሯል።

የነገሩ በከፍተኛ ሁኔታ መደጋገም አሳስቦኛል ያለው ባንኩ፣ ውል እየተዋዋሉ ያሉት ባለእጣዎች ከዚህ በፊት ቤት ይኑራቸው አይኑራቸው ሳላውቅ የሕዝብን ሀብት ፍትኀዊ በሆነ መልኩ የማከፋፈል ኃላፊነቴን አደጋ ውስጥ ከቶታል ብሏል። ይህንንም ችግር መፍታት አስቸጋሪ ቢሆንም ችግሩን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ጋር በጋራ የማጣራት ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን ገልጿል።

ያብስራ እንደሚናገሩት ሥም ማስለወጥ ሕጋዊ የሆነ ተግባር እና ማንኛውም ሰው ሥሙን በፍርድ ቤት አስቀይሮ ከመጣ ንግድ ባንኩ የመቀበል ግዴታ ያለበት መሆኑ፣ ሒደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደዚህ አይነት የማጭበርበር ሁኔታዎችን ለመከላከል ከከተማው ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ጋር በመሆን የተቀየሩ ስሞችን እና የጋብቻ ሁኔታዎችን ባጠቃላይ በመሰብሰብ ለማጥናት እና የማጭበርበር ሥራዎችን ለመለየት እየሠራ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ባንኩ የጋብቻ ሁኔታ ለውጥን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎች እንዲቀየርላቸው የሚጠይቁ ባለእድለኞችን ለማስተናገድ በቅድሚያ ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እንደሚያሳውቅና በዚህም የባለ እድለኞችን የቀድሞና የአሁን መረጃን አያይዞ ቢሮው እንዲያጣራ እንደሚልክለትም ገልጿል።

በትዳር አጋራቸው በኩል የቀበሌ ቤት ወይንም የግል ቤት ያላቸው ግለሰቦችም ተጨማሪ ጥቅም ለማግኘት የቤቶቹ እጣዎች በሚወጡበት ወቀት የፍቺ ወረቀት ከወረዳዎቻቸው ይዘው ይመጣሉ ተብሏል።

በሕገ ወጥ ድርጊቱ ላይ ተሳትፈው መረጃ የተገኛባቸውን ግለሰቦች በሕግ ለማስጠየቅ ግብረ ኃይል በማቋቋም እየሠራን ነው ሲሉ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በ2005 የ20/80 እና የ40/60 የቤት መርሀ ግብር ምዝገባ ሲደረግ ቤት ያላቸው እንዲሁም የትዳር አጋሮችም በአንዴ የኹለት ኮንደሚኒየምም ሆነ የሌላ ቤት ባለቤት መሆን እንደማይችሉ የተደነገገ ሲሆን አሁን ላይ በ40/60 ቤቶች ርክክብ ወቀት የጋብቻ ሁኔታን እና በፍርድ ቤት ሥም በማስለወጥ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኛት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

አዲስ ማለዳ በተጋጋሚ ወደ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት እና አስተዳደር በአካል ብትሔድም በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሚሰጡ ኃላፊዎችን ማግኘት አልቻለችም። ነገር ግን በተቋሙ ውስጥ ካሉ ምንጮቿ መረዳት እንደቻለችው ችግሩ በተመሳሳይ ለኤጀንሲውም ራስ ምታት እንደሆነ እና ችግሩን ለመፍታት የመረጃ ቋት የማዘጋጀት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here