ኻያ ሺሕ አባወራዎች ከባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ለቀው ለመውጣት ተስማሙ

0
611

በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል መሃል ተካሎ ከሚገኘው ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ውስጥ ከሚኖሩ ከ40 ሺሕ አባወራዎች ውስጥ 20 ሺሕ የሚሆኑት በ2012 ውስጥ ፓርኩን ለቀው ለመውጣት መስማማታቸውን እና ይህንንም ለማስፈፀም የሶማሌ ክልል ውሳኔ እየተጠበቀ እንደሆነ ታወቀ።

በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ የሚገኙትን “ሎክሶዳንታ አፍሪካና ኦርሊያንሲ” የተባሉትን ንዑስ የዝሆን ዝርያ ለማልማትና ለመጠበቅ በ1962 የተቋቋመው የዝሆኖቹ መጠለያ በሕገወጥ እርሻና ሰፈራ መስፋፋት እና በሕገ ወጥ አደን ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት በመምጣቱ በፓርኩ የሰፈረውን ነዋሪ ከፓርኩ ለማስለቀቅ ግድ ማለቱን የፓርኩ ኀላፊዎች ይናገራሉ። በዚህም መሰረት በመጠለያው ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር የምክክር መድረክ ተካሒዶ መስማማት ላይ መደረሱን የመጠለያው ኀላፊ አደም ሞሐመድ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በአካባቢው ነዋሪዎችና በዝሆኖቹ መካከል ያለው ግጭት እየጨመረ ከመምጣቱም ባለፈ በዝሆኖቹ ህልውና ላይ ከባድ አደጋ በመደቀኑ የክልሉን መንግሥት ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ የሶማሌ ክልል ባህልና ቱሪዝም የቱሪዝም ልማት ኃላፊ አደም ሁሴን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በመጠለያው በተደጋጋሚ በሰዎች እና በዝሆኖች መካከል በሚነሱ የጥቃት ልውውጦች የሚደርሱ አደጋዎች ከመስፋፋት አልፈው የሰዎችን እንዲሁም የዝሆኖችን ሕይወት እስከመቅጠፍ ደርሰዋል። በተገባደደው 2011 ብቻ የተቆጡ ዝሆኖች 14 ሰዎችን አጥቅተው አስሩን ለህልፈተ ሕይወት ሲዳርጉ አራት ግለሰቦች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ ማድረሳቸው የሚታወስ ነው። በተመሳሳይ ዓመትም የአስር ዝሆኖች ሕይወት ሲያልፍ ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ግልገሎች መሆናቸውን የመጠለያው ኃላፊ አደም ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ነበር።

አደም ሁሴን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት የዝሆን መኖሪያ በሆኑ አካባቢዎች ላይ እየተስፋፋ የመጣው የእርሻ ሥራ ዝሆኖቹ መኖሪያቸውን ለመከላከል ሲሉ ጥቃት እንዲጀምሩ አድርጓል። በዚህም በአካባቢው ነዋሪዎችና በዝሆኖቹ መካከል የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እንዲበረቱ አድርጎታል።

በመጠለያው ያለውን ሕገ ወጥ ሰፈራ፣ እርሻና አደን ለመቆጣጠር ጥረት ቢደረግም ከ30 ዓመት በላይ በመጠለያው የኖሩ ግለሰቦችን በቂ ዝግጅት እና ተለዋጭ ቦታ ሳይዘጋጅ ማንሳት ተገቢ ባለመሆኑ የሚሰፍሩበትን መተኪያ ቦታ ለማዘጋጀት ጊዜ ፈጅቷል ሲሉ የፓርኩ ኃላፊ ተናግረዋል።

የመጠለያው ኃላፊ አደም በበኩላቸው፣ በመጠለያው ውስጥ የሚኖረው ሰው ከመቶ ሺሕ በላይ በመሆኑ ያንን በአንድ ጊዜ ማስነሳት ከባድ ሆኖ መቆየቱን ይናገራሉ።

ከሶማሌ ክልል በኩል የሚገቡ ሕገ ወጥ አዳኞችም ነዋሪውን መስለው በመግባት ጥቃት እንደሚያደርሱ አውስተው ይህም ለዝሆኖቹ መመናመን የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን ገልጸዋል።

‹‹በ30 ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዝሆኖች ውስጥ 90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሞተዋል፣ ወደ ጎረቤት አገር ተሰድደዋል፣ የደረሱበት አይታወቅም›› ሲሉ የመጠለያው ኃላፊ አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ናቃቸው ብርሌው፣ ባለሥልጣኑ ወደ መጠለያው ባለሞያዎችን ለመላክ በማድረግ ላይ ያሉት ጥረት ከዝሆኖቹ ባሻገር ሌሎች ብርቅዬ እንስሳትንም ለመታደግ የተወሰነ ውጤት እያሳየ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ መጠለያው ከ30 በላይ ጡት አጥቢ የዱር እንስሳት፣ ከ250 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች፣ 3 መቶ ያህል የዕፅዋት ዝርያዎች የሚገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከምድረ ገፅ የመጥፋት አደጋ ላይ ያለው ”የሳልቫዶሪ ዘረ-መል” (Serinus xantholaema) ወፍ እና ባለጥቁር ጎፈር አንበሳ በዚህ መጠለያ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።

ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 550 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው መጠለያው 6982 ካሬ-ሜትር የቆዳ ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከጠቅላላ ስፋቱም ውስጥ 72 ከመቶ ያህሉ በሱማሌ ክልል ስር ሲካለል፤ ቀሪው 23 ከመቶ ያህሉ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ስር ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here