መነሻ ገጽአንደበት“ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያዊ ጋር ሲዋጋ ስለምንተዋወቅ በኹለቱም አቅጣጫ እልቂት ከመፍጠር ያለፈ የሚመጣ ቁምነገር...

“ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያዊ ጋር ሲዋጋ ስለምንተዋወቅ በኹለቱም አቅጣጫ እልቂት ከመፍጠር ያለፈ የሚመጣ ቁምነገር የለም”

ይህችን ዓለም የተቀላቀሉት በ1951 ነው። የትውልድ አካባቢያቸው በወቅቱ ወለጋ ክፍለ አገር ሆሮ ጉድሩ አውራጃ ነው። በልጅነታቸው ከመንፈሳዊ እስከ አስኳላ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ቀስመዋል። ገና በለጋ እድሜያቸው የፈጥኖ ደራሽ ትምህርት ተከታትለው፣ በ1969ኙ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጦርነት በፈጥኖ ደራሽነት ተሰልፈው ለአገራቸው ተዋግተዋል።

በኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ፈጥኖ ደራሽ 11ኛ ሻለቃ ተሰልፈው ለአገራቸው፣ በአንድ ቀን ኹለት ጊዜ ቆስለዋል፤ ሻለቃ ታመነ አባተ። በደርግ ዘመነ መንግሥት በሑርሶ ማሠልጠኛ ማእከል አሠልጣኝ ሆነውም አገልግለዋል። በ1973 በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት በአሁኗ ሩሲያ ለኹለት ዓመት የሴኩሪቲ (ደኅንነት) ትምህርት ተከታትለዋል።

በሕወሓትና በደርግ  ጦርነት ከደርግ ወገን ቆመው የብሔራዊ ውትድርና ደኅንነት ሆነው፣ ከአስመራ እስከ ሱዳን ደርግ እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ አገራቸውን አገልግለዋል። የደርግ ደኅንነትና የኢሰፓ አባሉ ሻለቃ፣ በኢሕአዴግ ስርዓት 10 ዓመት ያለ ፍርድ ታስረዋል። ሻለቃ ታመነ አሁን ላይ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅና የወታደራዊ ደኅንነት ባለሙያ ሲሆኑ፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ስለ ድርድሩ፣ የትጥቅ ትግልና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ በሚመለከት ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ማነው? ዓለማውስ ምንድን ነው?

በየቦታው የወደቁ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ቀና ብለው መሄድ አለባቸው። ከአሁን በኋላ አንገታችንን ደፍተን ቤተሰቦቻችንንና ልጆቻችን ፍጹም ባይተዋር ሳይሆኑ፣ በተዋጋንላት፣ በደማንላት፣ በቆሰልንላት አገርና ሕዝብ ፊት በኩራት መራመድ መቻል አለብን። የደማንላትና የቆሰልናት አገር አላውቃችሁም አላለችንም፣ ሕዝቡ አላውቃችሁም አላለንም። ስንራብ እያበላን፣ ስንጠማ እያጠጣን፤ እኛም ወታደራዊ ዲሲፕሊናችንን ሳናፈርስ ያን የመሰለ መሣሪያ ይዘን ውሃና ምግብ ስንለምን ነበር፤ ከሕዝባችን ላይ። ወደ ዘረፋ አልገባንም።

ስለዚህ ይህን ማኅበር ስናቋቁም ትልቁ ዓላማ ይሄን የወደቀ የቀድሞ ሠራዊት ቀና ብሎ እንዲሄድ ማድረግ ነው። ካቋቋምን በኋላ በሥራ አመራሩ አስተባባሪነት፣ ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ የሠራዊቱ አባላትን እንደ በላይነህ ክንዴ፣ እንደ እነ ሻምበል እድሜዓለም እጅጉ የመሳሰሉ የሠራዊቱ አባላት እርዳታ እያደርጉልን ሠራዊቱን እያደራጀን 298 ያህል ማኅበራትን አደራጅተን ኃይላችን ወደ አንድ ሚሊዮን ደርሷል።

አሁን ሁልጊዜ ሰውን በልመና ማስቸገር ስለማይገባን፣ ሥራ መፍጠር አለብን ብለን ፈጥኖ ደራሽ የጥበቃና የጽዳት አገልግሎት የሚል አቋቁመን በትንሹ ከ40 እስከ 60 የሚሆን የቀድሞው ሠራዊት በዚያ ሥራ ውስጥ ተቀጥሮ በሚከፈለው ደምወዝ ዳቦ እንዲበላ ማድረግ ችለናል።

አሁን ደግሞ ‹እራስ አድማስ› የሚል የፋይናንስ ተቋም መሥርተን፣ በማደራጀት ላይ እንገኛለን። በዚህም ሠራዊቱ ከእነ ቤተሰቡ አባል ሆኖ፣ ሌላውም ኢትዮጵያዊ ድርሻ (ሼር) ገዝቶ ባለድርሻ ሆኖ አንድም የቀድሞ ሠራዊትን መርዳት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ራሱ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ ስለሆነ ኹለተኛውን ምዕራፍ በዚህ ከፍተናል።

ሌሎችም ፕሮጀክቶች አሉን። የተለያዩ አደረጃጀቶችና ማኀበራት ስላሉ፣ እነዚህ ማኅበራትና አደረጃጀቶችም በየፈርጃቸው እየተንቀሳቀሱ ነው የሚገኙት። አሁን የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሞላ ጎደል ቀና እያለ ነው።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ጦርነት ሲገጥማት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ነበር። ማኅበራችሁ አሁን ካለው መንግሥት ጋር ወይም መከላከያ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

እኛ አሁን ከመከላከያ ጋር በጣም ጥሩ ግንኙነት አለን። በሕግ ማስከበሩ ወቅትም ተርፎን ሳይሆን፣ አገራችንን ስለምንወድና ሕዝባችንን ስለምናከብር ወደ 200 ሺሕ ብር አዋጥተን ለመከላከያ ሠራዊት ሰጥተናል። ምክንያቱም፣ የእነሱም ደም የእኛ ደም ነው።

እኛ የአገራችን ጉዳይ ያንገበግበናል፣ ያቃጥለናል። ከአሁን በፊትም የደማነው የቆሰልነው ለአገራችን ነው፣ ዛሬም ነገም እስካለን ድረስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ የምናከብረው ስለሌለ ዳግም መስዋዕትነት ለመክፍል ለመከላከያ አሳውቀን፣ አሠልጣኞችን በመስጠት፣ ሙያተኞችን በመስጠትና በግንባር በመሰለፍ አስፈላጊውን ነገር እያደረግን ነው።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት በድርድር እንዲፈታ መንግሥት ውሳኔ አሳልፏል። አሁን ባለው ሁኔታ የድርድር ጥረቱን እንዴት ይመለከቱታል?

ከጉዳት በስተቀር በኹለቱም አቅጣጫ፣ ከጦርነት የሚገኝ ጥቅም የለም። እንደምታውቀው ውጊያው የኢትዮጵያዊያን የእርስ በእርስ ጦርነት ነው። እኛ እኮ ከጠላት ጋር ቢሆን የምንዋጋው ለደቂቃ ከፊታችን የሚቆም ኃይል እንደሌለ በሶማሊያ ውጊያ ዐይተናል። አሁን ሁልጊዜ የእርስ በእርስ ጦርነት በሚሆንበት ወቅት፣ ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያዊ ጋር ሲዋጋ ስለምንተዋወቅ በኹለቱም አቅጣጫ እልቂት ከመፈጠር ያለፈ የሚመጣ ቁምነገር የለም።

ነገር ግን አንዱ ለመታረቅ ፈቃደኛ ሆኖ፣ አንዱ ፈቃደኛ ካልሆነ፤ ይህ ነገር አሁንም የሰው ሕይወት መስዋዕትነትን ነው የሚጠይቀው። ምንም እንኳን ሕወሓትና ሸኔ በሽብርተኝነት ቢፈረጁም አንዳንድ ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጪም ቢሆን ለሕዝብ ደኅንነትና ለአገር ሉአላዊነት ሲባል ይደረጋል። የአገርን እና የሕዝብን ጥቅም በማይሸራርፍ መልኩ ኢትዮጵያ በምታቀርበው ሐሳብ ሌላው ተቃዋሚ ቡድን የሚስማማና የኢትዮጵያ ጥቅም የማይነካ ከሆነ ሰላምን ማንም አይጠላም። እያንዳንዱ ሰው አገራችን ሰላም ሆና እፎይ ብሎ ቢተኛ፣ ነገ ምዕራባውያኑ የሚፈሩትን የኢትዮጵያን እድገት ማምጣት ያስችላል።

ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉበት ትልቁ ምክንያት ኢትዮጵያ ገና ያልተነካች፣ ምድሯ ያልተነካ ድንግል አገር ስለሆነች ነው። ይሄ ነገር እየወጣ ማኅበረሰቡ የሥራ ፈጠራን እያጎለበት ከመጣ፣ ኢትዮጵያ አፍሪካን በቀላሉ የማስተባበር አቅም ስላላት በየአቅጣጫው እንድንወጋ፣ በመሬታችን ላይ በሚፈስ ውሃ  እንዳንጠቀም የሚያደርጉን ምዕራብያዊያን ኢትዮጵያ እድገት ስለማይፈልጉ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ስለዚህ ሰላሙ የኢትዮጵያን መብት በማይነካ ደረጃ፣ ኢትዮጵያን ከክብሯ የማይሸርፍ የሆነ እንደሆነ፣ ሰላም ለሕዝባችን፣ ሰላም ለአገራችን ስለሚያስፈልግ የሰላም ድርድሩ በእኔ አመለካካለት ክፋት ያለው ነው ብዬ አላምንም።

የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ የሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ድርድሩ አይሳካም የሚል ሐሳቦች እንዲሰሙ ምክንያት ሆኗል። ከፌዴራል መንግሥትና ከአማራ ክልል እንዲሁም ከሕወሓት በኩል የሚነሱ ቅድመ ሁኔታዎች ስለ ድርድሩ ስኬትና ክሽፈት የሚያመላክቱት ነገር አለ ማለት ይቻላል?

አዎ! መንግሥት እንደመንግሥት ይሄን ነገር አያስብም ብዬ አላስብም። ሕወሓት የሚያስበው ተንኮል ሁልጊዜ አንድ እርምጃ ወደፊት ነው። አሁን ለምሳሌ ስለ ድርድሩ ከአሜሪካ የመጡ ልኡኮች መቀሌ ሄደው እያነጋገሩት ባለበት ሁኔታ ወልቃይት ላይ የትንኮሳ ሥራ እየሠራ ነው ያለው። ይሄ ምን ማለት ነው፣ ወልቃይትን ይዞ ለመደራደር ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሱዳን የሚገኝ ሳምሪ የሚባል የሕወሓት ቡድን በኹመራ አካባቢ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ስለዚህ ሕወሓት ሁልጊዜ በጎ ነገር ብቻ ያስባል ብሎ የሚገምት ሰው የዋህ ነው። ስለዚህ ድርድሩ ባይሳካ የሚቀጥለው እርምጃ ምንድን ነው ብሎ ማሰብና ቀድሞ መዘጋጀት ይጠይቃል። ይሄን መንግሥት አያደርግም ብዬ አላምንም፣ መቶ በመቶ ያደርጋል ብዬ ነው የማምነው። እነሱ እንደአመጣጣቸው በሰላማዊ መንገድ ከመጡና የኢትዮጵያን መሬት ከሕግ አግባብ ውጪ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ እነ ወልቃይትና ሑመራን ቆርሰው እንደያዙት፣ አሁንም እነዚህን አካባቢዎች ይዘን ታላቋን ትግራይ እንመሠርታለን የሚለውን ሐሳበቸውን ትተው፣ እነዚህን አካባቢዎች የሚተዉ ከሆነ፣ በኢትዮጵያዊነታቸው አምነው ከኢትዮጵያዊያን ጋር የሚቀጥሉ ከሆነ የሰላሙ ጉዳይ ምንም የሚያጠራጥር አይሆንም።

ነገር ግን ከበስተጀርባ፣ ሌላ ተንኮል ይዘው እንደሚመጡ መንግሥት ጠርጥሮ እንዳመጣጣቸው ለመመለስ ይዘጋጃል ብዬ ነው የማምነው። የመንግሥትን ቅደመ ሁኔታ መቀበል ከቻሉ እሰየው ነው። መቀበል የማይችሉ ከሆነ ግን አሁንም በሰላም ያልተፈታውን ነገር በጦርነት ለመፍታት ትገደዳለች ብዬ ነው የማምነው።

በሰሜኑ ጦርነት ተሳትፎ የነበራት ኤርትራ በድርድሩ ላይ መሳተፍ አለባት፣ አይ የለባትም የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ። እርስዎ እንደ ወታደራዊ ባለሙያ ምን ይመክራሉ?

አሁን እንደምታውቀው ኤርትራ ሌላ አገር ናት፣ ኢትዮጵያ ሌላ አገር ናት። ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ናት። ስለዚህ ደርድር በኹለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል፤ በኢትዮጵያና በትግራይ ሕዝብ መካከል የሚደረግ ነው። እንደ እኔ እምነት ሕወሓት ሙሉ በሙሉ የትግራይን ሕዝብ ይወክላል የሚል እምነት የለኝም። ነገር ግን ወደ ድርድር የሚመጣ ከሆነ፣ በዚህ ድርድር የኤርትራ መሳተፍ  ከምን አንጻር ነው?

ኤርትራ እንደ አገር ድንበሯን ታስከብራለች፣ እነሱም ይተናኮላሉ። በድንገት በተደረገው ወረራ ኤርትራ አግዛ ይሆናል፣ እኔ መቶ በመቶ አግዛለች የሚል እምነት የለኝም። ከሆነም ደግሞ በአገሮች መካከል በሚደረግ የሠራዊት ውል ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ኤርትራ ድርድሩ ውስጥ መግባት አለባት የሚለው ጉዳይ ብዙም አይታየኝም፤ በእኔ አመለካከት።

- ይከተሉን -Social Media

የኤርትራ መገለል የኹለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ቀድሞ ጠላትነት ሊቀይረው ይችላል?

አይቀይረውም። ለምን መሰለህ የማይቀይረው፣ ሕወሓት በመንግሥትነት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በበረሃ ውስጥ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ስምምነት አፍርሷል። ዓላማቸው መጀመሪያ ሕወሓት አሁን የያዘቻቸውና በሕገ መንግሥቱ ያልተፈቀዱለትን የአማራ ክልል መሬቶችን ይዞ፣ ለኤርትራ ደግሞ ባድሜን ለቆ በጋራ በፌዴሬሽን አብሮ ለመኖር ነበር እቅዳቸው።

ሕወሓት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ፣ የሥልጣንን ጣፋጭነትና ምዝበራ ሲያይ፣ የበረሃውን ውል ሰረዘው። ሻዕቢያዎች ሲጠይቁት ያ የበረሃ ውል ነው፣ በበረሃ ውል አልገዛም አለ። ስለዚህ አቅም የለውምና የቀድሞውንም ሠራዊት አስከፍቷል በሚል ነበር ሻዕቢያ ውጊያ የከፈተው። ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የእርስ በእርስ ጸብ ቢኖረውም አገር ሲነካ ኃይለኛ በመሆኑ፣ ከጣሊያን ጊዜ ጀምሮ አሁንም የሻዕቢያን ወጊያ የቀድሞው ሠራዊትም ተሳትፎ እንዴት አድርገው እንደመለሱት ያየነው ነው።

አሁን ግን ከእነ ዶክተር ዐቢይ መንግሥት ጋር ኤርትራን የሚያቃቅር ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም። ለምን ከተባለ፣ በፍርድ ቤት የተወሰነላቸው መሬት አለ፤ ለኤርትራዊያን። ስለዚህ ያንን በፍርድ ቤት የተወሰነውን ነገር መንግሥትን ሊጠይቁ ይችሉ ይሆናል። ያ ከሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚያላትማቸውና ወደ ቀድሞ ጦርነት የሚመልሳቸው አንድም ምክንያት የለም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ እና የትግራይ ሕዝብ ታረቀ ማለት፣ ክልሉ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚመራ ስለሆነ ኤርትራን የሚያሰጋትና የሚተነኩሳት ነገር የለም ማለት ነው።

ድርድሩ በስኬት ካልተቋጨ የሰሜኑ ጦርነት እጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል? ኢትዮጵያስ ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሊገጥሟት ይችላሉ?

እንደሚታወቀው ሕወሓት ሦስት እድሎችን አበላሽቷል። የመጀመሪያው በሕግ ማስከበበሩ፣ ቀጥሎ በሕልውና ማስከበሩ፣ በሦስተኛውም በተመሳሳይ። አሁን በአራተኛው የቀረበለትን የሰላም ሂደት የሚገፈትር ከሆነ፣ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሕወሓት አመራሮች መጥፊያ ነው የሚሆነው። የእነሱ መጥፋት ደግሞ ለትግራይ ሕዝብ ብርሃን ይፈነጥቃል።

ለድርድር ዝግጁ ሆነው ካልተገኙ ወታደራዊ ኃይል አስፈላጊ ነው። ሕዝቡ እርስ በእርስ ጦርነት በቃን እያለ ሕወሓት ድርድሩን የማይቀበል ከሆነ፣ የራሱን ውድቀት አቅጣጫ ማፍጠን ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያ ላይ የሚመጣ ቅንጣት ታክል ችግር የለም።

ድርድሩ በስኬት ተቋጭቶ የሰሜኑ ጦርነት አብቅቶ ሕዝቡ ሰላም እንዲያገኝ ከማን ምን ይጠበቃል?

- ይከተሉን -Social Media

ድርድሩ ግቡን ይመታል፣ ሰላም ይመጣል የምንለው የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የሚያስቀምጡትን ነጥብ ሕወሓት የተቀበለ እንደሆነ ነው። ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የምክክር ኮሚሽን አቋቁማ በየአቅጣጫው ጥረት እያደረገች ነው። እንደዚህ የሰላም እጅ በተዘረጋበት ሁኔታ፣ ሕዝቡም ቢሆን ሰላም ለማምጣት እስከሆነ ድረስ የማይቀበልበት ምክንያት የለም።

የጦርነትን ጉዳት ኖረንበት አየነው። ለምሳሌ እኔን ብትወስድ በጦርነት ተወልጄ በጦርነት አረጀሁ። ከመቁሰል፣ ከመድማት ያለፈ አንድም ያገኘኹት ጥቅም የለም። ቀጣይ የሚመጣው ትውልድ እፎይ እንዲል እና ራሱንና አገሩን እንዲያበልጽግ የሚፈለግ ከሆነ እዚህ አገር ላይ ሰላም መምጣት አለበት። ሰላም ደግሞ መጀመሪያ በሰላማዊ መንገድ ይመከራል። በሰላማዊ መንገድ ተሞክሮ፣ ሕዝቡም ተሳትፎበት ሰላም ከመጣ እሰየው ነው።

ይሄ ሳይሆን ቀርቶ ሰላሙን ያፈረሰው አካል የታወቀ እንደሆነ፣ እንደ ቀደምት አባቶቻችን ኢትዮጵያዊያን ሆ ብለው ተነስተው ሰላምን የረገጠውን ረግጠው የሰላምን ሉዓላዊነት ማሳየት አለባቸው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ከሰላም ጎን መቆም አለበት።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙ አኩራፊ ኃይሎች ተፈጥረዋል። አንዳንዶቹ አኩራፊዎች የትጥቅ ፖለቲካ በመምረጣቸው ኢትዮጵያ እየተፈተነች ነው። አሁን የሚታየውን የትጥቅ ፖለቲካ እንዴት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ አሰላለፍ ማምጣት ይቻላል?

በአገራችን የቀደሙት አባቶቻችን፣ አሁንም ያሉት የእርቅን መንገድ ከምንም፣ ከማንም በላይ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለምሳሌ አባ ገዳዎች፣ አገር ሽማግሌዎች። እነሱ በመጡበት መንገድ መሣሪያ ያነገቱ አካላትን በውጊያ ብቻ ማሸነፍ አይቻልም። በመሆኑም የአገር ሸማግሌዎችን፣ አባገዳዎችንና ነፍጥ ያነሱ ሰዎች ቤተሰቦች ይዞ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ መፈለግና ከሕዝቡ ጋር መምከር ያስፈልጋል።

የሕዝብን ድጋፍ በማሳጣት ያለምንም ውጊያና ቅድመ ሁኔታ፣ ትጥቁን አስቀምጦ ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖር የሚፈለግ ከሆነ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችንና ነፍጥ ያነሱ ቤተሰቦችን ይዞ የሰላም መንገድ መፈለግና ሁልጊዜ ሰላምን መሻት አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ትውልዱ ሁልጊዜ በውጊያ የሚያምን ትውልድ ከሆነ ይህች አገር አታድግም። ነገም የሚመጣው ትውልድ መሣሪያ ነው የሚስበው። ከነገ ወዲያም የሚመጣው ትውልድ መሣሪያ ነው የሚያስበው።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጎን ቆሞ፣ ነፍጥ የያዘውም ለምንድን ነው ነፍጥ የያዝኩት? ብሎ ቆም ብሎ አስቦ፣ ምንድን ነው የምፈልገው? መሣሪያ ይዤ ሕዝብን የማስጨንቅበት ምክንያት ምንድን ነው? ወገኔን የምገድልበት ምክንያት ምንድን ነው? ብሎ እንደሰው ቆም ብሎ ማስብ አለበት። ሁሉም አካል ተረባርቦ ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ በማድረግ ሰላም ማምጣት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ አዳጋች እየሆነ መጥቷል። አሁን ባለው ሁኔታ የሕዝብን ደኅንነት እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል?

እንደምታውቀው እሾህን በእሾህ የሚባል አባባል አለ። በአንድ አካባቢ ያለ ሕዝብ እንደዚህ የሕዝብን ሉዓላዊነት በማያከብሩ አካላት የሚደርስበትን ጥቃት እንዲከላከል በትክክል መንግሥት የሚፈልግ ከሆነ በሚሊሻነት አሠልጥኖና አስታጥቆ ራሳቸውን፣ አካባቢያቸውና ማኅበረሰባቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ይቻላል። መጀመሪያ ግን የሚታጠቁትን ሰዎች ሕዝቡ ራሱ መምረጥ አለበት።

ከማኅበረሰቡ ጋር ደግሞ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ስላሉ፣ አብረው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ወቅት የታጠቀ ኃይል አካባቢውን መጠበቅ ከቻለ አገርን ጠበቀ ማለት ነው። ስለዚህ መከላከያን ወይም ልዩ ኃይሎችን መጠበቅ ያስፈልጋል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት አሁን ባለው የመከላከያ ብዛት መሸፈንና መቆጣጠር አይቻልም።

እርስዎ ማኅበረሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ ማስታጠቅ ብዙዎች እንደ አጭር ጊዜ መፍትሔ የሚመክሩት ቢሆንም፣ የታጠቀ ማኅበረሰብ መፍጠር ሌላ ችግር ያስከትላል የሚሉ ስጋቶች ይነሳሉ። እርስዎ የሚነሳውን ስጋት እንዴት ያዩታል?

አይደለም! ሌላ ችግር እንዳያስከትል እድሉን ለሕዝብ መስጠት ነው። እድሉን ለሕዝብ ሰጥቶ ሰላም ለማስከበር የሚታጠቁ ኃይሎችን ሕዝብ አምኖባቸው እንዲመረጡ ማድረግ ነው። ከመንግሥት የሚጠበቀው፤ ሕዝብ የመረጠውን አሠልጥኖ፣ አስታጥቆ የአካባቢውን ሰላም እንዲያስከብር ማድረግ ነው። አገር ሰላም ከሆነ ደግሞ መንግሥት ያስታጠቀውን መሣሪያ ተቀብሎ ግምጃ ቤት ማስቀመጥ ነው።

ለምሳሌ እስራኤልን ብንወስድ፣ በጣም ትንሽ አገር ነች። እስራኤል ውስጥ ሴተኛ አዳሪ የለ፣ ሊስትሮ የለ፤ ሁሉም ዜጋ ለአገሩ ወታደር ነው። ሠልጥነው በብርጌድ፣ በሻለቃ፣ በመቶ አለቃና በሻምበል ተዋቅረዋል። ተዋቅረው ትጥቅ ተሰጥቷቸው፣ ትጥቃቸውን አስመዝግበው የሚያስቀምጡበት ግምጃ ቤት ተሰጥቷቸዋል።

በሰላም ጊዜ ቀጥታ ግምጃ ቤት ሄደው በሻለቃቸው፣ በብርጌዳቸው፣ በመቶ አለቃቸው አማካይነት ሄደው ያስቀምጣሉ። አገራቸው ችግር ሲገጥማት በየምድባቸው ተሰማርተው ከግምጃ ቤት መሣሪያቸውን አውጥተው አገራቸውን ይከላከላሉ።

ስለዚህ እኛም መፍጠር ያለብን ይሄን ሲስተም ነው። ገና ለገና መሣሪያ ካስታጠቅነው ነገ ተመልሶ ጠላት ይሆናል የምንል ከሆነ፣ ከመተላለቅ የሚያድነን ነገር የለም። ስለዚህ ሕዝቡን ስታስታጥቀው ግንዛቤው ሊኖረው ይገባል። ለምን? ለማን ብሎ እንደታጠቀ ማወቅ አለበት። አሁን አብዛኛዎቹ ሕዝብ የሚፈጁት መሣሪያውን ለምን? ለማን እንደታጠቁት አያውቁም። ለዘረፋ ብቻ ነው የሚጠቀሙበት።

ሰው ገድሎ ንብረት ዘረፋ፣ አገር አበላሽቶ ንብረት ፍለጋ፣ አገር ከሌለች የዘረፈውን ንብረት የት ሆኖ ሊበላው ነው? ሌላ ነገር ነገ ይመጣል ብሎ ማኅበረሰቡን ማስታጠቅ መፍራት ማለት፣ ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም ዓይነት ነው። የሚሆነውንና የሚመቸውን መምረጥ አለብን።፤ ወይ ማኅበረሰቡ የመረጣቸውን ሰዎች አስታጥቆ ሰላም ማስከበር ነው። ወይ እነሱን ከማስታጥቅ ይለቁ ብሎ መተው ነው።

መወሰን ይጠይቃል። አንዳንድ ጊዜ ወታደራዊ ውሳኔ ያስፈልጋል። እነዚህ የሚታጠቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከመከላከያ ውጪ አይደሉም፣ መከላከያ ሊመራቸውና አመራር ሊሰጣቸው ይገባል። ከዚያ በኋላ ሰላም ሲሆን መሣሪያቸውን ወደ ግምጃ ቤት ያስገባሉ። ችግር ሲፈጠር ትጥቃቸውን አውጥተው ራሳቸውን ይከላከላሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
Previous articleመምህርነት
Next articleራስን ማጥፋት
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች