መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናወደአረብ አገራት ለሥራ ለሚያቀኑ ዜጎች በዘላቂነት ሥልጠና መስጠት ሊጀመር ነው ተባለ

ወደአረብ አገራት ለሥራ ለሚያቀኑ ዜጎች በዘላቂነት ሥልጠና መስጠት ሊጀመር ነው ተባለ

ወደ አረብ አገራት ለሥራ ለሚያቀኑ ዜጎች በዘላቂነት ሥልጠና መስጠት ሊጀምር መሆኑን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ገዛኸኝ አባተ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ሕጋዊ ሆነው የሚሄዱ ቢሆንም እስከ አሁን ባለው ጊዜ ወደተለያዩ አረብ አገራት ለሥራ የሚያቀኑ ዜጎች በቂ እና ጥሩ በሚባል ደረጃ ተገቢውን ሥልጠና ወስደው እያቀኑ አይደለም።

ከዚህ አንጻር 2014 ሳይጠናቀቅ፣ ከአረብ አገራት ተመልሰው በድጋሜ ለሥራ ማቅናት ለሚፈልጉ እና በአዲስ መልክ ወደ አረብ አገራት ማቅናት ለሚፈልጉ ዜጎች ለሥራ የሚያግዛቸውን መሠረታዊ የሆኑ ሥልጠናዎችን በዘላቂነት እንደሚሰጡ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ሥልጠናው የአጭር ጊዜ ወይም እስከ ኻያ ቀን የሚደርስ እንደሆነ እና በሁሉም ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ድሬድዋ ከተማ አስተዳደሮች በኩል በሚገኙ የሙያ እና ቴክኒክ ተቋማት በኩል ይሰጣል ብለዋል።

እስከ አሁን ባለው ጊዜ ለሥልጠናው የሚረዳ በጀት እንዳልተያዘ እና አሁን በጀት ተመድቦለት ወደ ሥራ በሚገባበት ወቅት የቋንቋ፣ የምግብ ማብሰል፣ የቤት አያያዝ፣ የመስተንግዶ ሕጎች እና ሌሎች ለተሻለ ሥራ የሚረዱ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ተመላክቷል።

በተጨማሪ ቀድሞ ከሚከፈለው ከወር ክፍያ አንጻር የተሻለ ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚረዳ፣ ለሥራ አቅንተው በሚሠሩባቸው አገራት ለመግባባት የሚረዳቸውን ቋንቋ ተረድተው መግባባት እንዲችሉ፣ የሚያቀኑበትን አካባቢ ባህል በአጭር ጊዜ ለመረዳት እንዲያግዛቸው፣ የተሻለ ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚያግዝ እና ከአሠሪዎቻቸው ጋር አለመግባባት በሚፈጠርበት ወቅት ተንቀሳቅሰው ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ ለማቅረብ ሥልጠናው እንደሚረዳቸው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት በ2014 በጀት ዓመት በጀቱን ውጤታማ በሆነ መልኩ ከመጠቀም አኳያ በእቅድ ክፍተት ምክንያት አስፈላጊ ጥሬ ገንዘብ ወደ ሳጥን እንደገባ እና ለዚህም በፀጥታ ችግር ምክንያት ሥልጠና ይሰጣቸዋል ለተባሉ ዜጎች ሥልጠና መስጠት ባለመቻሉ ሳቢያ የተያዘው በጀት ወደ ካዝና እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።

በ2014 በጀት ዓመት በቱሪዝሙ ዘርፉ 1 ሺሕ 500 ዜጎችን በቀንና በማታ መርሐግብር ተቀብሎ ሥልጠና ለመስጠት ታቅዶ 273 ሠልጣኞችን በቀን 442 ሠልጣኞችን በማታ በድምሩ 715 አዲስ ሠልጣኞችን ተቀብሎ ማሠልጠን መቻሉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በሥልጠና ረገድ የዕቅዱን 51 በመቶ ማከናወን የተቻለ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የነበረው የፀጥታ ችግር ለእቅዱ ሙሉ ለሙሉ አለመሳካት በምክንያት ይጠቀሳል ተብሏል።

በፀጥታ ችግሮች ሳቢያ ሠልጣኞች በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ተንቀሳቅሰው መመለስ አለመቻል እና የ12ኛ ክፍል አገር ዐቀፍ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ዘግይቶ መሰጠቱ እና ውጤቱም ዘግይቶ ከመለቀቁ ባሻገር የከፍተኛ ትምህርት የመግቢያ ነጥብ በሚመለከተው አካል ዘግይቶ ይፋ መሆኑ ለአፈጻጸሙ ዝቅ ማለት በምክንያትነት እንደሚጠቀስ ተመላክቷል።

ወደ አረብ ሀገር ሄደው የተመለሱና ወደ አረብ ሀገርና ሌሎች ሀገራት ሄደው ሥራ መሥራት የሚችሉ ዜጎችን የሥልጠና ፍላጎቶችንና የሙያ ዓይነቶችን በመለየት ከስልሳ ሺሕ በላይ ዜጎችን የማሠልጠን ሥራ መሥራት የሚያስችል የዝግጅት ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተቋሙ በላከው ሪፖርት አሳውቆ ነበር። ይህ ቁጥር ሊጨምርም ሊቀንስም እንደሚችል ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

 

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች