የጡት ማጥባት ፈተናዎች

የሰው ልጅም ሆነ እንስሳት ወልደው በማጥባት ልጆቻቸውን እንደሚያሳድጉ ይታወቃል። እንቁላል ከሚጥሉት አብዛኞቹ በስተቀር፣ ማንኛውም ወላድ የሆነ ፍጥረት ልጆቹ እንደተወለዱ የሚበላውን ጥሬ ምግብ አይሰጥም። ከወፎች የሌሊት ወፍን ጨምሮ አብዛኛው የምድር አጥቢ ተብሎ የሚገለፅ እንስሳ ተፈጥሮ የለገሰችውን ወተት ከእናቱ ጠብቶ ያድጋል።

ይህ የማጥባት ኃላፊነት በተፈጥሮ የእናት ብቻ ሳይሆን አንዷ እናት የሌላንም ሕፃን የምታጠባበት ሂደት እንዳለ ከሰው ልጆች ታሪክም ሆነ ከእንስሳቱ ዓለም ድርጊት መረዳት ይቻላል። እናቱ የሞተችበት ጨቅላ ሌላ የምታጠባው እናት ካላገኘ እንደሚሞት ስለሚታወቅ፣ የእሱ ዝርያ ብቻ ሳይሆን ሌላዋም አጥብታ ልታሳድገው እንደምትችል ታሪክ ያስረዳናል።

ጫካ ጠፍተው የዱር እንስሳትን ጡት ጠብተው አደጉ እየተባለ በአፈ ታሪክም ቢሆን የሚነገርላቸው የነታርዛንና የኢትዮጵያዊው ጋዝያ ወይም አቢሲና ታሪክ እንደሚያስረዳን፣ የሰው ልጆችም ቢሆኑ ካልወለዷቸው እንስሳት ወተትን ካገኙ መኖር እንደሚቻላቸው ነው።

አሁንም ድረስ በዓለማችን ለልጆች ፍጆታ ተብለው በፋብሪካ ከሚዘጋጁት የሕፃናት ምግቦች ይልቅ በተፈጥሮ ከእንስሳት የሚገኝ ወተት በብዛት ጥቅም ላይ እንደሚውል ይታወቃል። በአብዛኛው አገራት የላም ወተት ቀዳሚውን ስፍራ ቢይዝም፣ የግመል፣ የፍየል እንዲሁም የተለያዩ የጋማ ከብቶች ወተትም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ጥቅም ላይ ይውላል።

በዓለም ላይ በከፍተኛ መጠን ጥቅም ላይ ከሚውል ወተት አብዛኛው የፍየል ወተት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ሲያስረዳ ከላም ከሚገኝ ወተት በመጠን በአራት እጥፍ ያነሰ ቢሆንም በብዛት ይመረታል ያለው ኤጂ ሀየርስ የተባለው ድረገጽ ነው። 650 ሚሊዮን ፍየሎች በዓለም ላይ አሉ የተባለ ሲሆን፣ እንደአየሩ ፀባይ የተለያየ ቦታ መኖር የሚችሉ ናቸው። ከዓለማችን ሕዝቦችም ወተትን በብዛት የሚጠቀሙ የስካንዲቪያ አገር ዜጎች ሲሆኑ፣ አሁን አሁን ከእንስሳት ወተት በተጨማሪም የአኩሪ አተርን የመሳሰሉ ከአዝዕርት የሚገኙ ወተቶችም በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ።

የእናት ጡት ወተት

በአገራችንም፣ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ የተለያየ ዓይነት የወተት ምርት በሕፃናትም ሆነ በትልልቆች የሚዘወተር ሲሆን፣ የእናት ወተትን የማያጠባ ማኅበረሰብ ግን እንደሌለ ይታወቃል። የዓለማችን ኹሉም ማኅበረሰብ ጡት አጥብቶ ልጆቹን የሚያሳድግ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን ከሥልጣኔ ጋር በተገናኘ እንዲሁም ሴቶችም ከቤት ውጪ የሚያሳልፉት ጊዜ ስለጨመረ እንደቀደመው ዘመን ሳይሆን የማጥባት ልምድ እየቀነሰ መምጣቱ ይነገራል።

ወቅቱ የጡት ማጥባት ሳምንት እንደመሆኑ፣ ከ3 ዓመት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ቢያንስ የሕፃኑ እድሜ ስድስት ወር እስኪሆነው ከእናቶች 50 በመቶ የሚሆኑት ጡታቸውን ብቻ እንዲያጠቡ ለማድረግ እሠራለሁ ሲል ይሰማል። እንደተቋሙ መረጃ ከሆነ ሕፃናት እንደተወለዱ ወዲያው ወተት ማግኘት የሚገባቸው ቢሆንም፣ ለአንድ ሰዓት ያህል ጡት የሚያገኙት ሕፃናት ከአምስቱ ኹለቱ ብቻ ናቸው ተብሏል።

ሕፃናት ስድስት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ የእናት ጡት ወተት ብቻ እንዲመገቡ ቢመከርም፣ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን ለማወቅ ተችሏል። የሕፃናቱን በሽታ የመከላከል አቅም ለማሳደግም ሆነ ጤነኛና ጠንካራ እንዲሆኑ በተመሳሳይ ልጅ ከልጅ ሳይለይ እንዲጠባ ይደረግ ቢባልም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ተብሏል።

ሕፃናቱ ኹለት ዓመት እስኪሞላቸውም የእናት ጡት ቢያገኙ መልካም ነው ቢባልም፣ ሲሶ የሚሆኑ ሕፃናት ለእድገታቸው ወሳኝ የሆነው የእናታቸው ጡት ያለወቅቱ ይቋረጥባቸዋል ተብሏል። ይህ ሁኔታ እንደአካባቢው ማኅበረሰብ አኗኗርና ባሕል የሚለያይ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ መሻሻል ያለበት ልምድ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ።

የጡት ማጥባት ሂደት ባለፉት ዐስር ዓመታት በተወሰነ መልኩ መሻሻል አምጥቷል የሚለው የተቋሙ መረጃ፤ ይህ ግን በሁሉም አካባቢ እንዳልሆነ ይጠቁማል። ኢ-ክሊኒካል ሜድሲን ላይ በወጣው ዘገባ መሠረት፣ ሀብታም የሚባሉ አገራት ያሉ እናቶች በተገቢው መጠን ልጆቻቸውን እንዲያጠቡ ማድረጉ የድሃ አገሮችን ያህል ውጤታማ አይደለም። ድሃ የሚባሉ አገሮች ልጆቻቸውን በተሻለ ለማጥባት መሞከራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ ቢባልም፣ በተባበሩት መንግሥታት የተቀመጠውን መስፈርት ግን ከየትኛውም አካባቢ ያሟላ የለም ተብሏል።

እናቶች ቢያንስ ልጃቸው ኹለት ዓመት እስኪሞላው ጡት ቢያጠቡ የሚጠቀሙት የልጃቸውን ጤናማነትና እድገት በማፋጠን ብቻ ሳይሆን፣ ለሌላ ምግብ የሚያወጡትን ወጪ በመቀነስም ኢኮኖሚያቸውን ማሻሻል ይቻላቸዋል ተብሏል።

በአጠቃላይ ሲታይ ከሚወለዱ ሕፃናት 95 በመቶ የሚሆኑት ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ የእናት ጡት ወተትን እያገኙ እንደሚያድጉ ነው። ከአምስት ሕፃናት አንዱ የእናት ጡት ወተትን ማግኘት የማይችልባቸው አካባቢዎች እንዳለ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ከአደጉት አገራት ይልቅ መካካለኛ ገቢ ያላቸው አገራት የሚኖሩ እናቶች የተሻለ ልጆቻቸውን በአግባቡ ያጠባሉ ተብሏል።

የጡት ማጥባት ፈተናዎች

እናቶች ጡት ማጥባታቸው ለልጆቻቸው ጠቃሚ እንደሆነ ቢያውቁም ተግባራዊ ከማያደርጉበት ምክንያቶች መካካል ለጡት ማጥባት ማኅበረሰቡ ያለው አመለካከት አንዱ እንቅፋት ነው። በተለይ በሥራ ምክንያት ልጆቻቸውን ከቤት ውጪ ይዘው የሚወጡ እናቶች በአደባባይ ለማጥባት ሲቸገሩ ይስተዋላል።

በአገራችንም ቢሆን በመጓጓዣም ይሁን በሥራ ገበታቸው ላይ እናቶች ለማጥባት ሲጨነቁ ይስተዋላል። አንዳንዶች ተሸፍነው ለማጥባት ሲሞክሩም ይስተዋላል። ግን ይህን ማድረግ ለብዙዎቹ ምቾት የሚሰጥ አይደለም፡፡

- ይከተሉን -Social Media

በዚህ ዙሪያ የተካሄደና ሠሞኑን ይፋ ተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ እናቶች አማራጭ አጥተው በመንገድም ሆነ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች በሚያጠቡበት ወቅት ከማኅበረሰቡ የሚያገኙት ምላሽ በጎ እንዳልሆነ ነው። ዐይን አፍጦ ከማየት ጀምሮ ምን ነካሽ የሚሉ አስተያየቶች እናቶች እንዲሸማቀቁና ልጆቻቸውን ከማጥባት እንዲቆጠቡ እንደሚያደርግ በጥናቱ መታወቁ ተነግሯል።

እናቶች አማራጭ አጥተው እንደሚያጠቡ የማይረዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ገንቢ አስተያየትም ሆነ ምልከታ ከመስጠትና ከመተባበር ይልቅ፣ ሲነቅፉ መሰማቱ ሂደቱ እንደነውር ማፈሪያ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ተመራማሪዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በተለይ በሀብታም አገራት ያሉ ሴቶች በመደብርም ሆነ በመጓጓዣ ላይ የሚያጠቡት ሌላው ተመልካች ወንድን ለመተናኮስ የሚመስላቸውም አሉ ተብሏል። አብዛኞቹ በጥናቱ የተካተቱ ሰዎች እንደሚሉት፣ በግልፅ ማጥባትን እንደነውር የሚያዩና መብት መሆኑንም የማይረዱ ብዙ ናቸው ሲሉ በተለይ እናቶች የሚገጥማቸውን ችግር አሳውቀዋል።

ከ17 ሺሕ በላይ እናቶችን በመጠየቅ እንዲሁም የተወሰኑ ወንዶችን የመጠይቁ አካል በማድረግ እናቶች በአደባባይ ሲያጠቡ ኅብረተሰቡ ከሚሰጣቸው አስተያየት በመነሳት ምን እንደሚሰማቸው ለመረዳት ሞክረዋል። አብዛኞቹ እናቶች ማኅበረሰቡ እንደሚያሸማቅቃቸው የተናገሩ ሲሆን፣ አተኩሮ ከማየት ጀምሮ በቃላት ጭምር እንድናቆም የሚናገሩ ሰዎች አሉ ይላሉ።

ከሥልጣኔና ከሕግ አንፃር ማኅበረሰቡ እየተሻሻለ መምጣት ሲገባው፣ ይብሱኑ ሴቶች በቤት ውስጥ ብቻ እንዲያጠቡ የሚያደርግ አተያይ በመበራከቱ የእናት ጡት ወተት እንዲዘወተር የሚሠራው ተግባር ላይ እንቅፋት ይሆናል ተብሏል። ማኅበረሰቡ የሚያጠቡ እናቶችን ሲያይ ይቀፈዋል ያሉ ተጠያቂዎች እንዳሉት፣ የኅብረተሰቡ ተቃውሞ ስለሚበዛባቸው አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር ልጆቻቸው እያለቀሱም ቢሆን አለማጥባትን እንዲመርጡ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመዋል።

የስዋንሳና ካርዲፍ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች ባካሔዱት በዚህ ምርምር፣ ልጅ ሲያጠቡ የሚመለከቱ ሌሎች ሰዎች አጥቢዋን እናት ልጇን እንደምትንከባከብ እናት ከመመልከት ይልቅ እነሱን ለማማለል ያደረገችው የሚመስላቸውም እንዳሉ ጠቁመዋል።

ይህ ዓይነት የማኅበረሰብ አመለካከት እናቶች ልጃቸውን ማጥባት ባለባቸው ወቅት እንዲሳቀቁና እንዲጨነቁ ስለሚያደርግ፣ አስተሳሰቡ ካልተቀየረ በስተቀር የሚያጠቡ እናቶችን ቁጥር የተፈለገው መጠን ላይ ለማድረስ የሚሠራውን ተግባር ወደኋላ ይጎትታል ብለዋል።

ይህ ዓይነት የማሸማቀቅ ባሕል አብዛኞቹ እናቶች በተቻላቸው መጠን ከቤት ውጭ እንዳያጠቡ ስለሚያደርግ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታቸውን ያናጋል። ጭራሹኑ ከቤታቸው ውጪ ለማጥባት የማይፈልጉ ሴቶች በርካታ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ ያለው አመለካከት ካልተስተካከለ ሂደቱ እየባሰበት እንደሚመጣ ተመላክቷል።

እናቶች በአደባባይ ማጥባት እንዲችሉ ሕግ አውጥተው ሂደቱ ተፈጥሯዊ መሆኑን ለማመላከት የሞከሩ አገራት ቢኖሩም ያን ያህል መሻሻል አላገኙበትም። በገበያ ቦታም ሆነ በተሽከርካሪ ማቆሚያዎች አልያም በአገልግሎት መስጫ ቦታዎች እንዲህ ዓይነት ሕጎች እንዳሉ እያወቁም የሚከለክሉ መኖራቸው፣ እናቶች እንደልባቸው ሳይሸማቀቁ እንዲያጠቡ አያደርግም ተብሏል።

- ይከተሉን -Social Media

ይህ የመገለልና እንደነውረኛ የመታየት አባዜ በሁሉም የዓለማቸን ክፍል በእኩል የሚተገበር አለመሆኑን ያመለከቱት አጥኚዎቹ፣ በድሃ አገራት በሚገኙ ወጣት ሴቶች ላይ የመፈፀሙ አዝማሚያ ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። ኑሮ አስገድዷቸው ሳይፈሩ እንደልባቸው የሚያጠቡ የመኖራቸውን ያህል ሰው ሳያስቸግራቸውም የሚሸማቀቁ መኖራቸውም ታውቋል። ልጆቻቸው እያለቀሱ አፍረው ለማጥባት የሚግደረደሩን በማኅበረሰቡ ግፊት በአደባባይ እንዲያጠቡ የሚያደረጉ እንዳሉ የተናገሩት ተመራማሪዎቹ፣ በተለይ ወንዶች እናቶችን ከማሸማቀቅ ተላቀው እንደጉድ ከማፍጠጥም ተቆጥበው ተፈጥሯዊ ሂደቱን እንዲተባበሩ መክረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች