መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብኪን/ጥበብየኢትዮጵያ ፊልም አሁናዊ ቁመና

የኢትዮጵያ ፊልም አሁናዊ ቁመና

ፊልም ሲባል የአንድን ማኅበረሰብ፣ ባህል፣ ስሜትና አመለካከት፣ ታሪክ ወይም ፈጠራ ለማስገንዘብ የሚረዳ የኪነጥበብ አካል እንደሆነ ብያኔ ተሰጥቶታል። አገረሰባዊ ውበትን ወይም መልከዓ ምድራዊ ገጽታን ለማስተዋወቅም ቢሆን ፊልም ተመራጭ መሆኑ አይካድም።

የኢትዮጵያ ሲኒማም እድሜ ጠገብ ነው ባይባልም፣ በቆየባቸው ዘመን ግን ከፊልም ፋይዳ አንጻር በርከት ያለ አስተዋጽኦ እንዳበረከት ይመሰከርለታል።

ይሁን እንጂ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአገራችን የፊልም እድገት እየቀጨጨ ነው፣ በፊልሞቻችን ሊነገር የሚችል ያለን አገራዊ የኪነጥበብ ሀብትና ፊልሞቻችን ለተመልካች ይዘውት የሚቀርቡት ሐሳብ አይቀራረብም። አቀራረቡም የጥበብ ኃይል የሌለው ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

አንድ ሰሞን በየሲኒማ ቤቱ እየዞርኩኝ ፊልም ማየትን ሥራዬ አድርጌ ነበር የሚል ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገ አንድ የፊልም ተመልካች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሐሳብ መደጋገሙና ፈጠራ አልባ የሆነ የፊልም ድርሰት መመልከቱን ስላልወደድኩኝ ሲኒማ ቤት መሄዱን ጨርሶ ትቻለሁ ይላል።

በትንሹም ቢሆን ስለፊልም ጥበብ ሥልጠና ወስጂ፣ የሚሠሩ ፊልሞችን በተማርኩት መሠረት ስመለከት በጣም ብዙ መጣረስ እንዳለ ተመልክቻለሁ ባይ ነው። ‹‹በኢትዮጵያ ፊልሞች አንድ ተወናይ ለብዙ ደቂቃዎች ሲያወራ ልታይ ትችላለህ። በዓለም ዐቀፉ አካሄድ ሲታይ ይህም በጣም አሰልቺና የማይመከር ነው።›› በማለትም አክሏል።

በአዲስ አበባ መንገድ ላይ ከሚጓዙ ሰዎች በድንገት ‹‹አማርኛ ፊልም ታያለህ?›› ብለን ስንጠይቅ የሰጡት መልስ ብዙዎች ማየት እንደማይፈልጉ ነው።

አንዱ አስተያየት ሰጪም፤ ‹‹አባቴ በልጅነቴ ጀምሮ ነው አማርኛ ፊልም እንዳላይ የከለከለኝ። የውጭ ፊልሞች የቋንቋና ሌሎች ክህሎቶችን ስለሚያስገኙ እነሱን እንዳይ ይመክረኝ ነበር። አሁን ግን የአገሬን ፊልም ማየት አለብኝ ብዬ ለማየት ስሞክር ብዙ ፊልሞች ተመሳሳይ ይዘትና ደካማ መልዕክት የያዙ ናቸው።›› ብሏል።

አንድ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ‹‹ለእኔ ፊልም ማለት የወደፊቱን የሚተነብይ ሲሆን ነው። እንዲህ ዓይነት ፊልሞችን የየትም አገር ይሁኑ አሳድጄ አያለሁ። ለምሳሌ፣ አንድ የፊልም ባለሙያ እንዳጫወተኝ፤ ሆሊውድ ባራክ ኦባማ የአሜሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዘዳንት ከመሆናቸው በፊት፣ በፊልም መልኩ አቅርቦት ነበር። አሜሪካዊያን ይህን ፊልም ዐይተው ቢቆጡ ኖሮ ኦባማ የአሜሪካ መሪነት እንደናፈቃቸው ይቀር ነበር። ፊልም በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ይህን ያህል ጉልበት አለው። ምንም ጥያቄ የለውም፤ የእኛ ፊልሞች ከዚህ ረገድ ሥራ እየሠሩ አይደለም።››

አማርኛ ፊልም ማየት ብዙም አይደለንም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ካነሷቸው ሐሳቦች መካከል፣ የአማርኛ ፊልሞች ዐስር ደቂቃ ገደማ እንደታዩ መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል። እንዲሁም ፈጠራ ካዘለ አዳዲስ አቀራረብ ይልቅ በአሉባልታ የተሞሉ ናቸው።

ለወጪ ቅነሳ ሲባልም እውቀትና ክህሎት ባላቸው ባለሙያዎች ሳይሆን በትውውቅና በቤተሰብ ለመሥራት መሞከር፣ ሴቶችን ከብቃትና ክህሎት ይልቅ አካላዊ ውበታቸውን እንደማስያዣ የሚጠቀም ዘርፍ በመሆኑ  ለተመልካች የሚመጥኑ ፊልሞች እየተመረቱ አይደለም ይላሉ።

በተለይ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የአገሪቱ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም ያለው የኑሮ ውድነት ተደራርቦ ዘርፉን ክፉኛ ሳይጎዳው እንዳልቀረ ብዙዎች ይስማማሉ።

ከሰሞኑ ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 1/2014 በዓለም ሲኒማ (አዲስ አበባ) የሚታዩ ፊልሞችን ዝርዝር ለዘርፉ ችግር እንደማጣቀሻ የወሰዱት ነበሩ። በዚህ የሲኒማ የሦስት ቀን መርሃ ግብር አርብ ሐምሌ 29 ከሰባት ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት ኹለት ሰዓት ተኩል ገደማ ድረስ አራት ፊልሞች ለስምንት ጊዜ ይታያሉ። ‹‹የሱፍ አበባ›› የሚለው ፊልም ሦስት ጊዜ የሚታይ ሲሆን፣ ‹‹አንድ ታሪክ››ም ኹለት ጊዜ ለተመልካች ይቀርባል።

እነዚህ ፊልሞች ቅዳሜ ከተመሳሳይ ሰዓት ጀምሮ ተደጋግመው የሚታዩ ሲሆን፣ እሁድ ነሐሴ 1/2014 ደግሞ በተመሳሳይ ሰዓት (ከ7 ሰዓት እስከ ምሽት ኹለት ሰዓት ከኻያ ደቂቃ) ‹‹የሰኔ ግርግር›› የሚለው ፊልም አምስት ጊዜ ለዕይታ ይቀርባል። አርብና ቅዳሜ ሲታዩ የነበሩ ፊልሞችም አብረው ይታያሉ።

ሥማቸው የተጠቀሱት እነዚህ ፊልሞች በቫምዳስ ሲኒማም ተደጋግመው የሚታዩ ሲሆን፣ በዓለም ሲኒማም ቢሆን እስከ ነሐሴ 5/2014 ድረስ ለመታየት ተደጋግመው ከተጻፉ ፊልሞች መካከል ናቸው።

ብዙ የፊልም አፍቃሪዎች ደግሞ ሳምንቱን ሙሉ አዳዲስ ፊልሞችን ማየት እንደሚወዱ ይገልጻሉ። ከኹለትና ሦስት ዓመት በፊት የነበረ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የፊልም ዘርፉ በዓመት ከ80 እስከ 100 ፊልም ያመርታል።

በፖሊሲና በተቋም የተደገፈ ባለመሆኑም የኢትዮጵያ ፊልም ራሱን ችሎ የሚቆም ዘርፍ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት የሚናገር የለም። በተለምዶ ግን የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ተብሎ ይጠራል።

- ይከተሉን -Social Media

የፊልም አሠራር ሂደቱም አገራዊ ማንነትን ከማስተዋወቅ ይልቅ ገንዘብ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ሚዛን የደፋ ነው የሚል ሀሜት የሚነሳበት ነው።

አዘጋጅና ተዋናይ አሰፋ ዘሪሁን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ፣ የኢትዮጵያ ፊልም በኹለት እግሩ አልቆመም ሲል ገልጾ፣ ትልቁ መነሳት ያለበት ጉዳይ ዘርፉ በአገራችን የተሰጠው ትኩረት ምን ያህል ነው የሚለው መሆን አለበት ይላል።

‹‹ሌላ አገር ላይ ፊልም ሲባል፣ ሕዝብና ባለሙያው አይደለም መንግሥት ራሱ ስለዘርፉ በደንብ አድርጎ ይገነዘባል። የፊልም ዘርፍ ትልቅ ገበያ መሆኑን የተረዱ ብዙ አገራትም ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ትምህርት ቤቶችን፣ ስቱዲዮ እንዲሁም እቃዎችን ያለማሉ።›› ነው ያለው።

እኛ አገር ላይ ጉዳዩ የተገላቢጦሽ መሆኑን በማንሳትም፣ ዘርፉን መቶ በመቶ ተሸክመው የሚጓዙት በራሳቸው የሚጥሩ ባለሙያዎች እንደሆኑ ይናገራል። በዚህ መንገድ የተሠራ ፊልምም ውጤቱ ውስንና ደካማ እንደሚሆን ሳይጠቅስ አላለፈም።

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት በኩል ያለው ዕይታ የተስተካከለ ባለመሆኑም፣ የፊልም ዕቃዎች ሲገቡ የሚጣልባቸው ቀረጥ አስደንጋጭ ነው። ለማኅበረሰቡ የኪነጥበብ እድገት የሚያስፈልጉ መሆናቸው አይታሰብም።›› ይላል።

የተዋናዮች ብቃት

የአገራችን ፊልም ዘርፍ ገብተው ከሚሠሩ ተዋናዮች ብዙዎች የሚሞገሱና የሚወደዱ ባለሙያዎች አይጠፉም። እሱ ወይም እሷ ያለችበት ፊልም ከሆነ ያምራል የሚባልላቸው ተዋናዮች ስለመኖራቸው መካድ አይቻልም።

በአንጻሩ ደግሞ በቀላሉ ዕድሉን ስላገኙ ብቻ ወደ ፊልም ሥራው ዘው ብለው የሚገቡ ተዋናይ ነን ባዮችም ሞልተዋል።

- ይከተሉን -Social Media

አዘጋጅና ተዋናይ አሰፋም፣ በራሳቸው ጥረት የድንቅ ክህሎት ባለቤት የሆኑ ተዋናዮች መኖራቸውን ጠቅሶ፣ ነገር ግን እንደሌሎች አገሮች እጅግ ትልቅ በሆነ የፊልም ትምህርት ቤት ተምሮና በተደራጀ ስርዓት ውስጥ ገብቶ የሚሠራ ባለሙያ የለንም ባይ ነው።

በዚህ ወቅት ያለው አብዛኛው ተዋናይ ግን የሚያወራው ከአፉ እየወጣ መሆኑን የማያውቅ ሲሆን፣ ይህም ተዋናዮች ወደ ዘርፉ የሚመጡበት መንገድ ደካማ እና የፊልም ሳይንሱ በሚጠይቀው መንገድ ከመሄድ ይልቅ በባህላዊ መንገድ መሆኑ ነው ብሏል።

ትክክለኛ ፊልም ዘጠኝ ወር ነው የሚፈጀው ሲል ጠቅሶም፣ ሦስት ወር ለቅድመ ዝግጅት፣ ሦስት ወር ለቀረጻና ሦስት ወር ለአርትኦት የሚጠይቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ በምንም ተዓምር እኛ ፊልም ሥራ ላይ ተተግብሮ አያውቅም ሲል ተናግሯል።

አሁን እየተደረገ ያለውም፣ ካፌ ውስጥ ወይም ኮንዶሚንየም ውስጥ አንድ ፊልም ታስቦ ያልቃል። ሲነማ ቤቶች እያሳዩ ያለው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ኹለት ሦስት ቦታዎች የሚያልቅ ፊልም ነው። አንድ ተዋናይ በሆነ ምክንያት ቢያቋርጥ አንዱ ብድግ ብሎ ይቀጥለዋል። ይህ ያስፈራል። በአንድ ሰው ግንዛቤ ልክ የሚሠራ ፊልም ነው የብዙዎች አዕምሮ ግብዓት እየሆነ ያለው በማለት ያብራራል።

የዘርፉ ዕድሎች

ምንም እንኳን የሚጠይቀው ወጪ እና ለቀረጻና ለሌሎች ሥራዎች ቢሮክራሲው የበዛ ቢሆንም፤ በሐይማኖት፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በአመጋገብና በአለባበስ ውስጥ ያለውን አገራዊ የኪነጥበብ ሀብት ወደ ፊልም መቀየር የሚቻልበት ሰፊ እድል እንዳለ ይነገራል።

መንግሥትና ባለሙያዎች በአንድ መስመር አብረው መሮጥ ከቻሉም ዘርፉን፣ የአገርን ገጽታ ለመገንባት፣ የቱሪዝም ገበያውን ለማስተዋወቅ እንዲሁም የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት የተመቸ መሆኑ የብዙዎች ዕይታ ነው።

ባለሙያዎች እንደሚሉትም፣ የአገርን ገጽታ ከፍ አድርገው የሚያሳዩና በዓለም ዐቀፍ የፊልም መድረኮች ላይ ተገኝተው ለዓለም መታየት የሚችሉ የፊልም ጹሑፎች ይመጣሉ። ነገር ግን፣ በተለይ ጽሑፉን ወደ ፊልም ለመቀየር አስቸጋሪ በሆነው የአገራችን ቢሮክራሲና  በወጪው ምክንያት የሚሠራው የታሰበው ሳይሆን የተቻለው ብቻ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ስለሆነም፣ እንደ አገር ያለው ሰፊ የኪነጥበብ ሀብት እንዲሁም የፊልም ዘርፉ የያዘው ትልቅ ገበያ እንደ መልካም እድል ይነሳል።

በዚህ ወቅት

አዘጋጅና ተዋናይ አሰፋ ችግር ሁሌም የትም አለ ይላል። በዚህ ወቅት ኮሮና ቫይረስ (አሁን ላይ ስጋት ባይሆንም)፣ የፀጥታ ችግር እንዲሁም የኑሮ ውድነት እንደችግር ይነሳሉ። ግን ችግር እያለም ሥራ ይሠራል። የሠሪው ቁርጠኝነት እንጂ ችግር በራሱ ጉልበት የለውም ባይ ነው።

‹‹በፊት ፊልም በደንብ ይመረት ነበር። በየሳምንቱ ሰኞ ብሔራዊ ቴአተር ፊልም ይመረቅ ነበር። አሁን ያ ቁጥር የለም። የሌለውም በወቅታዊ ችግሮች ሳይሆን በፊት በዚህ ዘርፍ ላይ ሲሠራ የቆየው አልባሌ ስህተት የሠሪውን ፍላጎት ዘግቷል። በዚህ ወቅት አንድ ፕሮድዩሰር በፍጹም ሌላ ፊልም ደግሞ አይሠራም። ያወጣው ገንዘብ እንዴት እንደተመለሰለት ያውቀዋል። ስለሆነም ለምን ብሎ ሌላ ፊልም ለመሥራት ያስባል?›› ሲል ይጠይቃል።

‹‹በኬንያና ናይጄሪያ ብናይ እንኳን በየሳምንቱ አስደንጋጭ ቁጥር ያለው ፊልም ይወጣል። እነሱ ችለው እኛ ስለማንችል ሳይሆን አዕምሯቸው በዚያው ልክ ስለተለጠጠ ነው›› የሚል ሐሳቡንም ሰንዝሯል። ፊልም ለመሥራት ገንዘብና ቁሳቁስ የግድ አይደለም። ወሳኙ የአዕምሮ እድገት ነው። በሌሎች አገራት የስልክ ፊልም (በስልክ ብቻ የሚሠሩ) ፌስቲቫል አለ ነው የሚለው።

ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ፊልም በዚህ ወቅት እንደበፊቱ አይደለም ሳይሆን የሚባለው፣ ድንቅ ባለሙያዎችንም እያጣ ነው ሲል ይገልጻል።

መፍትሄው

የፊልሙ ዘረፍ ባለቤት አልባ እንደሆነና፣ የሚመራበት ጠንካራ ፖሊሲ እንዲሁም ተቋም እንደሌለው ይነገራል። ባለሙያዎች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ሳይቀር አለመኖሩ ብዙዎች እንደ ትልቅ ችግር ያነሳሉ።

የዚህ ኹሉ ችግር ምንጭ ደግሞ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ሲበዛ የወረደ መሆኑ እንደሆነ አክለው ይገልጻሉ።

ብዙ ባለሙያዎችም እስኪሰለቻቸው ድረስ ዘርፉ ባለቤት እንዲኖረውና በተቋም እንዲመራ መንግሥትን ሲወተውቱ እንደቆዩ ይናገራሉ። አሁን እየሆነ ያለውም መንግሥትና ባለሙያው የግብ ማስቆጠሪያውን ነቅለው ለ90 ደቂቃ እየተጫወቱ ነው ይላል አሰፋ።

‹‹መንግሥትም ባለሙያውም ይጫዎታሉ። ግባቸው ምን እንደሆነ ግን አይታወቅም። ኹሉም ጥጉን ይዞ ይጫወታል፤ ግብ የሚባል ነገር የለም። ስለሆነም የዘርፉን አስፈላጊነት የሚረዱ በመንግሥት ውስጥ ያሉ ሰዎችና ባለሙያው ተገናኝተው መፍትሄ ቢሰጡት ይበጃል።›› ነው የሚለው።

መፍትሄው በመንግሥት እጅ ነው። ጉልበት ስላለውም ከባለሙያዎች ጋር ተዋህዶ ሲሠራ ነው ለውጥ የሚገኘው ሲል አስገንዝቧል።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች