የጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ

0
2291

በመርህ ደረጃ እንደሚታመነው ከሆነ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችም ጭምር የክልልነት ጥያቄ መጠየቃቸው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነው። ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ የራሱን ክልል መመሥረት እንደሚችል ይደነግጋል።

ለዚህ ደግሞ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 47 መሠረት ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ በማንኛውም ጊዜ የክልልነት ጥያቄ በሚያነሳበት ወቅት ምላሽ የሚያገኝበት ሂደት እንዳለ የሕግ ባለሙያዎች ሲያነሱ ይደመጣሉ።

ሕገ መንግሥቱ ይሄን የሚደነግግ ከሆነ ማንኛውም ማኅበረሰብ የክልልነት ጥያቄ ማንሳቱ ምንም ዓይነት ጥፋት አይደለም የሚሉም አልጠፉም።

በሕጉ መሠረት የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የማያገኙበት እና ተፈፃሚነት የሚታጣበት ሂደት የሚፈጠር ከሆነ፤ ጥፋቱ የሚሆነው በኢሕአዴግ ጊዜ የወጣውን ሕገ መንግሥት ሳያሻሽል ያስቀጠለው አዲሱ መንግሥት ነው ሲሉ የሚደመጡም አሉ።

የክልልነት፣ የዞን እና የወረዳ እንሁን ጥያቄ በተለያዩ ብሔር ብሔረሶቦች እየተነሱ ሲሆን፣ መንግሥትም በክላስተር በማደራጀት ምላሽ ለመስጠት እየሞከረ ይገኛል።

በደቡብ ክልል ያሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለኹለት ተከፍለው በኹለት አዲስ ክልሎች ለመደራጀት በየምክር ቤቶቻቸው ወስነው ውሳኔውን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረባቸው እሙን ነው።

በጋራ በአዲስ ክልል እንደራጃለን ብለው በምክር ቤት ውሳኔ አሳልፈው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄውን ካቀረቡት መካከል ግን የጉራጌ ዞን እንደሌለበት ይታወቃል።

ዞኑ ከአጎራባቾቹ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ሀዲያ፣ ሀላባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ጋር ነበር በአንድ ክልል ይደራጃል ብሎ መንግሥት አቅጣጫ ያስቀመጠው።

ነገር ግን የዞኑ ምክር ቤት እስከ ዛሬ ድረስ በጉዳዩ ላይ አልተወያየም። አዲሱን አደረጃጀትም አላፀደቀም። ከዚህ በፊት ዞኑ እንደገለፀው የክልልነት ጥያቄን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ ነው።

መንግሥት በአሁን ወቅት ዞኑን በክልል ለማደራጀት እንደሚቸገር በመግለፅ ከአጎራባች ዞኖች እና ልዩ ወረዳ ጋር ተቀናጅቶ ክልል እንዲሆን ነው ሐሳብ እያቀረበ ያለው።

የዞኑ ሕዝብ ግን በክልል የመደራጀት ጥያቄው ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ መሆኑን እና ለጠየቀው ሕጋዊ የሆነ ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጠው፤ ብሎም ጉራጌ ክልል አደረጃጀትም ተግባራዊ እንዲሆንለት በተለያየ መንገድ እየጠየቀ ይገኛል።

ከዚህ አንጻር አዲስ ማለዳ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የፖለቲካ ምሁራንን እና የሕግ ባለሙያዎችን በጉዳዩ ዙሪያ አናግራለች።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት ማሙሸት አማረ እንደሚሉት፣ የጉራጌ ማኅበረሰብ ያነሳው ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከሆነ ተገቢ ነው። ይህ ጥያቄ ደግሞ የሲዳማና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጠይቀው ምላሽ ያገኙበት ሂደት እንዳለ ማንሳት በቂ ነው ይላሉ።

ከዚህ አኳያ የጉራጌ ብሔረሰብ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝበት ሂደት እንዲፈጠር ፓርቲያቸው እንደሚጠይቅም አውስተዋል።

በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን እጣ ፈንታ ወዴት እያመራ እንደሚገኝ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው የሚሉት ኘሬዝዳንቱ፣ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የክልልነት ጥያቄ ጠይቀው ምላሽ በሚያገኙበት ወቅት ኢትዮጵያዊነት እየተሸረሸረ ይመጣል የሚል ስጋት አለን ብለዋል።

አክለውም፣ መንግሥት በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ማሻሻል ካልቻለ በቀጣይም ሌሎች አከባቢዎች ጥያቄ ከማንሳት እንደማይቆጠቡ እና የጉራጌ ማኅበረሰብ የጠየቀውንም ጥያቄ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።

በተጨማሪ፣ የጉራጌ ማኅበረሰብ የክልል ጥያቄ ከመጠየቅ እና ምላሽ ከመሰጠቱ በፊት ሌሎች የክልልነት ጥያቄ ጠይቀው ምላሽ ያገኙ ምን ጥቅም እንዳገኙ በመረጃ ተደግፎ ማጥናት ያስፈልጋል ይላሉ።

ከዚህ ባለፈ ግን የጉራጌ ማኅበረሰብ ጥያቄውን በሕጋዊ መንገድ ማለትም የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ፣ ንብረት ላይ ጉዳት ሳይደርስ ጥያቄውን ማስቀጠል እንደሚችሉ እና የክልልነት ጥያቄያቸውም ምላሽ የሚያገኝበት እድል እንዳለ ተናግረዋል።

በተጨማሪ መንግሥት ሕጋዊ ለሆኑ ጥያቄዎች መፍትሄ በማስቀመጥ ያለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የፖለቲካ ምሁር የሆኑት አሰፋ አዳነ (ረ/ኘ) እንዳሉት፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ እንደሰፈረው ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ ራሱን ማስተዳደር እንደሚችሉ እና ክልል መመሥረት እንደሚችል ሰፍሮ ይገኛል።

ከዚህ አንጻር የጉራጌ ማኅበረሰብ የክልል እንሁን ጥያቄ ማንሳቱ ስህተት አይደለም ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ ከኹለት ዓመት በፊት የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሲፈቅድ፣ በቀጣይ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም ጥያቄ የሚያነሱበት ሁኔታ እንደሚኖር የተለያዩ የፖለቲካ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ቀድመው ሲያነሱት የነበረ ጉዳይ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተጨማሪ መንግሥት የተለያዩ ምሁራን፣ የፖለቲካ አባላት፣ ተመራማሪዎችን ያቀፈ በመሆኑ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ሁኔታን አስመልክቶ በየወቅቱ ምክክር እንደሚያደርጉ ይታወቃል ይላሉ።

የጉራጌ ብሔር ብሔረሰብ ሰፊ ማኅበረሰብ፣ በርካታ ምሁራን እና ሰፊ ሀብት ያለው በመሆኑ የክልልነት ጥያቄው ተገቢነት እንዳለውም ተናግረዋል።

የጉራጌ ማኅበረሰብ ያነሳው ጥያቄም ሕገ መንግሥቱ ላይ በሰፈረው ሕግ መሠረት ተገቢ ከመሆኑም ባሻገር፣ ችግርም ሆነ ተቃርኖ የሚያስነሳ ምንም ዓይነት ምክንያት አለመኖሩንም ገልፀዋል።

ከመንግሥት አኳያ የክልልነት ጥያቄ የሚያነሱ ማኅበረሰቦችን በክላስተር በማደራጀት ክልል እንዲሆኑ እየፈቀደ ነው።

ነገር ግን፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት አንድ ማኅበረሰብ የሚያነሳውን ተገቢ ጥያቄ ወደ ጎን በመተው የክላስተር አደረጃጀትን መፍጠር ተገቢ እንዳልሆነ እና ሕጉም እንደማይፈቅድ አውስተዋል።

ይህ እንዳለ ሁኖ፣ መንግሥት እያደራጀበት ያለውን የክላስተር አደረጃጀት የጉራጌ ማኅበረሰብ የማይቀበል ከሆነ በክላስተር ተደራጁ ብሎ ማስገደድም ሆነ ሕጋዊ ጥያቄውን አለመመለስ ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

አክለውም፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ አገሪቷን እያስተዳደረ ባለው መንግሥት ላይ ሰፊ ድርሻ እንደመኖሩ መጠን ማንኛውም ማኅበረሰብ ራሱን እንዲያስተዳድር የሚፈቅደውን አንቀጽ ማሻሻል ወይም ክልል የመሆን ጥያቄ እንደማያስተናግድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት ተገቢ ነው።

ይህን ማድረግ ካልቻለ የጉራጌ ሕዝብ የክልልነት እጣ ፈንታ እንዳለው ተናግረዋል። መንግሥት አሁን ያሉበትን የተለያዩ ምክንያቶች ከግምት ውስጥ አስገብቶ ከጉራጌም ሆነ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ እና አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስረድቶ እንዲሁም የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች ለተወሰኑ ጊዜ የማይነሱበትን ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል ብለዋል።

መንግሥት ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይቶችን መፍጠር ካልቻለ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን መልስ መስጠት እንደሚያስፈልግ እና ጊዜ ካልወሰደ በስተቀር ማኅበረሰቡ ምላሽ የሚያገኝበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል።

የጉራጌ ዞን ለዓመታት ሲያቀርበው የቆየውን የክልልነት ጥያቄ በተመለከተ፣ የብልጽግና መንግሥት በክላስተር እንዲደራጅ በቅርቡ ያወረደውን ትእዛዝ ተቃውሞ እስከ ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት የሚያቀና መሆኑ ለአዲስ ማለዳ ተገልጿል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሐምሌ 28/2014 ባደረገው ጉባኤ በክላስተርነት ከተደራጁት ሌሎች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር በነበረው ጉባኤ፣ የጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ያልተካተተው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን እየጣሰ ስለሆነ ነው ተብሏል።

በአንጻሩ መንግሥት ያወረደውን የክላስተር አደረጃጀት የጉራጌ ዞን እንዳልተቀበለ አቋሙን በመግለጽ፣ መብቱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲከበርለት ይህ ካልሆነም እስከ ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት ሊያቀና መሆኑን የሕግ አማካሪና ጠበቃ ጀምብር አብዶ ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ኅዳር 7/2011 በምክር ቤቱ ተሰብስቦ በክልልነት መደራጀት እንደሚፈልግ ያለምንም ተቃውሞ መወሰኑንና ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ሕዝበ ውሳኔው እንዲፈጸም ለክልል ምክር ቤት ከደጋፊ ሰነዶች ጋር መላኩን ያስታወሱት ጀምበር፤ የክልልም ሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምላሽ በመስጠት ፈንታ ዝምታን መርጧል ነው ያሉት።

በመሆኑም፣ የጉራጌ ዞን በ2011 የወሰንኩት የክልልነት ጥያቄ ይፈጸምልኝ። በክላስተርነት ግን አልደራጅም የሚል ሕጋዊ አቋሙን ሊቀለብስ አይችልም ተብሏል።

የሕግ አማካሪ እና ጠበቃው በሕገ መንግሥቱ  ክላስተሪንግ የሚል የሕግ መሠረትም ሆነ ጽንሰ ሐሳብ ስለሌለ፤ የጉራጌ ዞን ትዕዛዙን ሊቀበል አይችልም። የክልልነት ጥያቄው ግን ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ክላስተሪንግ ‹‹ብልጽግና ከኋላ ኪሱ በመምዘዝ ያመጣው ነው›› ያሉት ጀምበር፤ የሕግ አካል እና ባለሙያ እንደመሆናችን መጠን እስካሁን አናውቀውም ብለዋል።

ጀምበር ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ ስምንት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ስለመሆናቸው፣እንዲሁም ንዑስ አንቀጽ ኹለት ደግሞ ይህን ሥልጣናቸውን የሚተገብሩት በተወካዮቻቸው አማካኝነት መሆኑን እንደሚደነግግ ጠቅሰዋል።

አያይዘውም የጉራጌ ክልል የሕገ መንግሥት መብቱን ተጠቅሞ የክልልነት ጥያቄው እንዲመለስለት በመጠበቅ ላይ ነው ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ይህንኑ መሠረት በማድረግ በተወካዮቹ በኩል ሙሉ ድምጽ አድርጎ በውሳኔው ላይ ሕዝበ ውሳኔ ይደረግልኝ የሚል አቋም እንዳለው ጀምብር ተናግረዋል።

በመሆኑም ጉራጌ ክላስተር አልቀበልም ማለቱ፣ ጉዳዩ የሕግ መሠረት ስለሌለውና ምክር ቤቱ ተወያይቶ ሕዝቡ ክላስትር እሆናለሁ ብሎ ስላልወሰነ ነው ያሉት የሕግ አማካሪው፣ መንግሥት ክላስተር ተቀበሉ የሚለው በግድ ለመጫን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ምንም ዓይነት ችግር ሳይፈጠር በወልቂጤ ከተማ የመከላከያ ኃይል ከበባና ወከባ መፈጠሩ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ሰሞኑን በከተማው ላይ በወጣው ኮማንድ ፖስት ጭራሽ ጉራጌ ክልል ነው የሚል ቲሸርት መልበስ፤ ክላስተር አልፈልግም የሚል ወረቀት መያዝ እንደማይቻል መመሪያ እየተላለፈ ነው።

በወለጋ፤ በአማሮ ልዩ ወረዳ እና በጉጂ አዋሳኞች እንዲሁም በሌሎች የጥቃት ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች የመከላከያ ኃይል በአሁኑ ወቅት ሊሰለፍባቸው ሲገባ ወደ ወልቄጤ ማምጣቱ በራሱ ከሕግ አንጻር አግባብነት የለውምም ተብሏል። “ሥልጣን ላይ ያለው የብልፅግና መንግሥት ሕገ መንግሥቱን አስገድዶ እየደፈረ ነው” ሲሉ ነው የሕግ ባለሙያው እና ጠበቃው ያስረዱት።

ጉራጌ ከዚህ በኋላ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሄደ ለሦስተኛ ጊዜ ቅሬታውን ለማቅረብ ነው ያሉት ጀምበር፤ መብታቸው በሕገ መንግሥቱ መሰረት ካልተከበረላቸው እስከ ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚያቀኑ ነው የተናገሩት።

ገዢው መንግሥት ሕገ ወጥ አሠራር እየተከተለ ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ የሕዝብን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይገባዋል ሲሉ ጉዳዩን ከሕግ አንጻር አብራርተዋል።

ምንም ቢፈጠር የጉራጌ ዞን የያዘው አቋም ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ የክልልነት ጥያቄው ፍትሃዊ ምላሽ ተችሮት ክልል እስካልሆነ ድረስ ትግላችንን እንቀጥላለንም ብለዋል።

የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የተለያዩ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የክልልነት ጥያቄ እየጠየቁ የመጡበት ሁኔታ መኖሩን ተከትሎ መንግሥት የተለያዩ አከባቢዎችን በማቀናጀት እና በክላስተር አደራጅቶ የክልልነት ጥያቄው ምላሽ ለመስጠት እየሠራ ይገኛል።

‹‹ከሕግ አንጻር የተመለከትን ከሆነ ማንኛውም ዞን፣ ልዩ ወረዳ የክልልነት ጥያቄ መጠየቃቸው ሕጉ እንደሚፈቅድ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 47 ይጠቅሳል›› ብለዋል።

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄም ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንፃር ትክክል እንደሆነ እና ጥያቄውም ተገቢ እንደሆነ መንግሥት እንደሚያምን የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል።

ነገር ግን፣ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን መንግሥት ምላሽ የሚሰጥበት ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ ሌሎች አከባቢዎችም የሚያነሱት ጥያቄ እንደመኖሩ መጠን አገር መከፋፈል ነው የሚል የመፍረስ አደጋ በመንግሥት በኩል ስጋት እንደሚኖር አስረድተዋል።

በተጨማሪም፣ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝ ከሆነ እንደ አንድ ክልል በርካታ ሥራዎች ማለትም ሰፊ መሠረተ ልማት መሠራት እና ሌሎች ፖለቲካ ጥያቄዎችም ምላሽ የሚያገኙበት ሂደት በመኖሩ፣ ለፌዴራል መንግሥት ከበጀት እና ከሌሎች ተደራራቢ ጥያቄዎች ጋር ተዳምረው ራስ ምታት ይፈጥራል ባይ ናቸው።

የሕግ ባለሙያው አክለውም፣ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ሕጋዊ እንደመሆኑ መጠን መንግሥት መከልከል እንደማይችል ያነሱ ሲሆን፣ ክልል መመሥረት ጥቅም እንደሌለው እና የዜጎችን ክፍፍል እንደሚያጠናክር ውይይት አድርጎ ለማኅበረሰቡ ማስረዳት ጥሩ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ እንዲሁ ሕገ መንግሥቱን በቅርቡ እንደሚያሻሽል ማሳወቅ እና የጉራጌ ማኅበረሰብ እንደ አማራጭ አሁን ባስቀመጠው የክላስተር አደረጃጀት እንዲደራጅ ማግባባት ካልቻለ፣ ጥያቄውን በኃይል ማስቆም እንደማይችል እና የጉራጌ የክልልነት ጥያቄው ምላሽ አያገኝም ለማለት እንደማይቻል የሕግ ባለሙያው ጠቁመዋል።

ከክልልነት ጥያቄው ጋር በተገናኘ በጉራጌ ዞን ከተማ በሆነችው ወልቂጤ ከተማ የሥራ ማቆም አድማ መደረጉ ይታወሳል። በሌሎች የጉራጌ ከተሞችም ጎዳና ላይ በመውጣት የመንግሥትን በክላስተር ተደራጁ የሚል ሐሳብ በመቃወምና የክልልነት ጥያቄውን በመደገፍ ትዕይንተ ሕዝብ ተካሂዶ ነበር።

የክልልነት ጥያቄው ጋር በተገናኘ የዞኑ የብልፅግና አባላትና የኢዜማ ተወካዮች ለየፓርቲያቸው መልቀቂያ ማስገባታቸውም ሲናፈስ የነበረ ጉዳይ ነው። ወቅታዊውን የዞኑን ጥያቄ መፍትሔ ለመስጠት የዞኑ አመራር ሐሙስ ነሐሴ 5/2014 ቀን የምክር ቤቱን አባላት አጀንዳውን ሳይነግሩ ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ነበር።

በእለቱ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፤ ከሌሎች የአስተዳደር መዋቅሮች ጋር በክላስተር ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በአብላጫ ድምጽ ውድቅ አድርጓል፡፡

ምክር ቤቱ  ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤው የጉራጌ ዞንን በደቡብ ክልል ሥር ከሚገኙ ሌሎች አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር በማዳመር የጋራ ክልል ለመመሥረት የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በ52 የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞ እና በ 40 ድጋፍ ውድቅ ማድረጉም ታውቋል።

ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት ወስኖት የነበረውን የጉራጌ በክልልነት የመደራጀት ውሳኔን አጽንቷል:: የምክር ቤቱን ውሳኔ ተከትሎም በወልቂጤ ከተማ ሕዝቡ ወደ አደባባይ ወጥቶ ደስታውን ገልጿል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here