1- የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ODP) ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲው የውስጥ አንድነትን በተመለከተ ውይይት መጀመሩን አስታውቋል። በውይይቱ ወቅት ለአገራዊ ለውጡ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ተለይተው የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚቀመጥላቸው የተገለፀ ሲሆን ማዕከላዊ ኮሚቴው እንደ ፓርቲ ያለውን አፈጻጸምን በመገምገም ጠንካራና ደካማ ጉዳዮችን ለይቶ እንደሚወያይ ታውቋል። (አዲስ ማለዳ)
………………………………………………………………..
2- በአፋር ክልል ከሰሞኑ የተፈጸመው የ17 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው ጥቃት የታቀደና በውጭ ኃይሎች የተደገፈ እንደነበር የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቋል። የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አህመድ ሙሐመድ እንዳስታወቁት፣ ጥቃት አድራሾቹ የተደራጁና የሶማሌ ላንድ የሠሌዳ ቁጥር ያለው ተሽከርካሪ የሚጠቀሙ ነበሩ። ጥቃት የተፈጸመበት መንደር ከጂቡቲ ድንበር 35 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቀት ላይ ይገኛል። የመከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱ ላይ የውጭ ኃይሎች አልተሳተፉም ማለቱ ይታወሳል። (አብመድ)
………………………………………………………………..
3- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመጪው ታኅሣሥ ወር ጀምሮ ‹‹የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ›› የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚያደርግ አስታዉቋል። በዚህ ዓመት የሚደረገው ጭማሪ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ እንዲጨመር በተያዘው አቅጣጫ መሠረት የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል። ነገር ግን የአገልግሎቱ ጭማሪ ምን ያህል እንደሆነ በግልፅ አላሳወቀም። (ኢቢሲ)
………………………………………………………………..
4- የፌዴራል መንግሥት ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት በአራት ዓመታት ስድስት ቢሊዮን ብር ቢደጉምም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገንዘቡን ከባቡር ኮርፖሬሽን በመልቀቅ አኳያ ዳተኝነት እያሳየ መሆኑ ተገለፀ። የፌዴራል መንግሥት በየዓመቱ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር እየደጎመ እንደሆነ ያስታወሱት በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ኃላፊ የኋላሸት ጀመረ፣ የከተማ አስተዳደሩ ድጎማውን እያስፈፀመ አለመሆኑን ተናግረዋል። (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
………………………………………………………………..
5- በድሬደዋ ከተማ አዲስ ተቃዋሚ ፓርቲ የተመሰረተ ሲሆን ፓርቲው ‹ቅንጅት ለዴሞክራሲና ለነጻነት› ይሰኛል። የሶማሌ ሕዝብ ነጻነትና ዴሞክራሲ እንደሚታገል ያስታወቀው አዲሱ ፓርቲ መሥራች ጉባዔ እየተካሔደ ሲሆን፣ እስከ ስኞ ድረስ ይቀጥላል ተብሏል። ፓርቲው ዋና መቀመጫውን በጅግጅጋ እንደሚያደርግና በድሬዳዋና አዲሰ አበባም ቅርንጫፎች እንደሚኖሩት ገልጿል። (ቪኦኤ አማርኛ)
………………………………………………………………..
6- የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወስደው ያለፉ የቤት ሠራተኞች ወደ ዓረብ አገራት ሲሔዱ ያቀረቡት ማስረጃ ሕጉን ያከበረ መሆን አለመሆኑን የሚያረጋግጡ ተቆጣጣሪ ሠራተኞችን በኢትዮጵያ አየር መንገድ መመደቡ ታወቀ። በአየር መንገዱ የተመደቡት ሠራተኞች ቀደም ብሎ በአየርና በየብስ ኬላ በተመደቡ ሠራተኞች እንዝህላልነትና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በመያዝ፣ የተመደቡበትን የመቆጣጠር ኃላፊነት የዘነጉ ሠራተኞችን ኃላፊነት በመውሰድ፣ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ተጓዦች ያቀረቡትን ማስረጃ በተገቢው ሁኔታ ፈትሾ መፍቀድና መከልከል የሚያስችል ሥልጣን ያላቸው መሆኑም ተጠቁሟል። (ሪፖርተር)
………………………………………………………………..
7- የዓለም ፓርላማዎች ሕብረት 141ኛው መደበኛ ጉባኤ ሰርብያ ቤልግሬድ በመካሔድ ላይ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም የተመራ ልዑካን ቡድን የዓለም ፓርላማዎች ህብረት ስብሰባ ላይ ተሳትፏል። በጉባኤዉ ላይ የሕዝብ እንደራሴዎች የዓለማቀፍ ሕጎች ማስከበርና ለአከባቢያዊ ትብብር ማጠናከር የሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚካሄድም ታዉቋል። (ፋና ብሮድካስቲንግ)



