ኢትዮ ቴሌኮም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 10 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ

0
997

ኢትዮ ቴሌኮም በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 10 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል።

ዛሬ ጥቅምት 6/2012 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሥራ አፈፃጸም በተመለከተ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኢትዮ ቴሌኮም በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም የእቅዱን 98 በመቶ ማሳካት መቻሉን እና ከባለፈው ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 21 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የገለጹ ሲሆን ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 56 በመቶው ከድምጽ አገልግሎት 29 በመቶው ደግሞ ከሞባይል ዳታ የተገኘ መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 41 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላሩ ከዓለም አቀፍ አገልግሎቶች የተገኘ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 44 ነጥብ 4 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን  የደንበኞች ቁጥርም 10 በመቶ መጨመሩ በመግለጫው ተጠቅሷል ።

ኢትዮ ቴሌኮም ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸዉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል። ከአዲስ አበባ ዉጭ ለሚገኙ ተማሪዎች የ32 ሺሕ ደብተር እገዛ ያደረገ ሲሆን በጤና፣ በግብርና፣ በማህበራዊ አገልግሎቶች፣ ሕጻናትን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አረጋዊያንን በማገዝ እና በአከባቢ ጥበቃ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here