የቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከነሐሴ 16/2014 ጀምሮ የመክፈል አቅም ለሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ከ13 ዓይነት በላይ ለሆኑ በሽታዎች ነፃ የጤና ምርመራ ሊሰጥ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሸናፊ አምብሬ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ሆስፒታሉ ከሚቀጥለው ሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 21/2014 ባሉት ተከታታይ ስድስት ቀናት የመክፈል አቅም የለንም ለሚሉ ነፃ የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
የመክፈል አቅም ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተባሉት በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች የመክፈል አቅም የሌላቸው፣ አቅመ ደካማ እና ጎዳና ተዳዳሪዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከላይ በተጠቀሱት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የጎዳና አከባቢዎች ላይ የድንኳን ሸራ ወጥሮ እና በሞንታርቦ መልእክቶችን በማስተላለፍ ከ13 በላይ ለሆኑ በሽታዎች ሕክምና እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
ከላይ በተቀመጡት ቀናት ውስጥ በተጠናከረ የጤና አጠባበቅ ትምህርት መሠረት ተላላፊ እና ተላላፊ ባልሆኑ እንደ ኮሌራ እና ሌሎች ውሃ ወለድ ማለትም የተቅማጥ በሽታዎች፣ ወባ፣ ኤችአይቪ፣ ቲቢ፣ ኮቪድ-19፣ የካንሰር ሕመም እና ሌሎች በሽታዎችም ላይ ትኩረት በማድረግ ለተገልጋዮች ሕክምና እንደሚሰጥ ኃላፊው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የደም ግፊት ምርመራ፣ የደም ብዛት፣ የደም ማነስ፣ የስኳር መጠን ምርመራ፣ ከአንገት በላይ ምርመራ፣ የዐይን ምርመራ፣ የቆዳ ምርመራ፣ የሥነ ምግብ ምርመራ፣ የአዕምሮ ጤና ምርመራም ይሰጣል ተብሏል።
የቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እነዚህ በሽታዎች በበጎ ፍቃደኝነት የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ከ200 ሺሕ ብር በላይ በጀት ወጪ እንዳደረገም ኃላፊው አስረድተዋል።
ኃላፊው አክለውም፣ በየቀኑ ሕክምናውን ለማግኘት የሚመጡ ሰዎችን ሰልፍ በማሰለፍ በተራ ለማስተናገድ እቅድ እንደተያዘ እና በእቅዱ መሠረት በአንድ ቀን ውስጥ ከጧት 2 ሰዓት ከ30 ጀምሮ እስከ ምሽቱ 11 ሰዓት ከ30 ድረስ ከ60 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሕክምናው የሚሰጥበት እድል አለ ብለዋል።
ሆስፒታሉ በአዲስ አበባ ከተማ በሽሮሜዳ ታክሲና አዉቶብስ ተራ አካባቢ፣ ቀጨኔ መድኃኔዓለም አካባቢ፣ በእንጦጦ ማርያም የጸበል ቦታ አካባቢ፣ በአፍንጮ በር መስጊድ መግቢያ በር አካባቢ፤ የወደቁትን አንሱ የአረጋውያን የአእምሮ ሕሙማን ማገገሚያ ተቋም፣ በጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል እንዲሁም በታላቁ ቤተመንግሥት የአንድነት ፓርክ እና የወዳጅነት አደባባይ በሚገኙ የሆስፒታሉ የድንገተኛ ክሊኒኮች የሕክምና አገልግሎቱ የሚሰጥባቸው ቦታዎች መሆናቸው ተጠቁሟል።
የቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያስቀመጣቸውን ሕጎች ለማይተገብሩ፣ ከሰልፍ ውጭ ለሚሆኑ፣ ሥነ ምግባር ለሚጥሱ እና ከሰዓት እላፊ ውጪ ለሚገኙ አገልግሎቱን እንደማይሰጥም ተጠቁሟል።
የቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአገር ዐቅፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2014 በጀት ዓመት የተጀመረውን የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተከትሎ “በጎነት ለጤናችን” በሚል መሪ ቃል የሚሰጥ እና የሚቆይ የነጻ የጤና አገልግሎት ነው ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014



