መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናአማራ ክልል የተሻሻለ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና መመሪያን ተግባራዊ አደረገ

አማራ ክልል የተሻሻለ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና መመሪያን ተግባራዊ አደረገ

የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት የተሻሻለ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ።

የመንግሥት ሠራተኞችን አፈጻጸም በተጨባጭ ማስረጃ ላይ በመመሥረት ለመለካት፣ የተሻለ የሠሩትን ለማበረታታት፣ ድጋፍ ለመስጠትና በአፈጻጸም ሂደት የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችል የአፈጻጸም ምዘና ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ፣ የክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት የተሻሻለ መመሪያ ማውጣቱ ነው የተገለጸው።

ይህ መመሪያ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት በጀት በሚተዳደሩ በክልሉ በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተመላክቷል።

የሠራተኞች የሥራ አፈጻጸም እቅድ የሚዘጋጅበት አግባብም በመመሪያው የተካተተ ሲሆን፣ በዚህም ለማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የሚዘጋጅ የስድስት ወር እቅድ በየወሩ ተሸንሽኖ እንዲሰጠው ይደረጋል። የሠራተኛውን እቅድ በቅርብ ኃላፊው በማፅደቅ ከስምምነት መድረስ ካልተቻለ ደግሞ በመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ውሳኔ እንዲያገኝ የሚደረግ መሆኑ ነው የተጠቀሰው።

የስድስት ወር እቅድ በሠራተኛው እና በቅርብ ኃላፊው በጋራ የሚዘጋጅ ሆኖ፣ የአፈጻጸም ስምምነቱ ከሐምሌ አንድ እስከ 15 እና ከጥር አንድ እስከ 15 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በመፈራረም የሚዘጋጅ ነው ተብሏል።

ለሠራተኛው የተሰጡ ተግባራት፣ የአፈጻጸም ስምምነት ጊዜ፣ የሠራተኛው ሙሉ ሥምና የሥራ መደቡ መጠሪያ እንዲሁም የመሥሪያ ቤቱንና የዳይሬክቶሬቱን ሥም በይዘት ያካተተ፣ ሠራተኛው ከቅርብ አለቃው ጋር የሚፈራረመው የዕቅድ አፈጻጸም ስምምነት ሰነድ መኖሩም ተገልጿል።

የሠራተኛው የአፈጻጸም ግምገማና ምዘናም የአፈጻጸም የመረጃ ምንጮችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ተቀምጧል።

በዚህም የተቋምና የቡድን ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የሠራተኛው የየወሩ እና የቅርብ ኃላፊው የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት፣ አስቀድሞ የተያዙ ሪፖርቶች፣ ግብረ መልሶች እና ቃለ ጉባኤዎች፣ የግብ ተኮር ተግባራት እና የባህሪ ብቃት መገለጫዎች አፈጻጸም የምዘና ግብዓቶች ሆነው ተጠቅሰዋል።

የሠራተኞች የስድስት ወራት አፈጻጸም ምዘና ሲካሄድ የግብ ተኮር ተግባራት አፈጻጸም ውጤት 70 በመቶ የሚይዝ ሲሆን፣ ለውጤቱ መገኘት መንስኤ የሚሆኑ የባህሪ ብቃት አፈጻጸም ደግሞ ቀሪ 30 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል።

የባህሪ ብቃት አፈጻጸም ምዘናው የሚካሄደው ተመዛኙ በተገኘበት ሆኖ፣ በሥራ ቡድን አባላትና በቅርብ የሥራ ኃላፊው ሲሆን፣ በቡድን አባላት ለግለሰቡ አፈጻጸም ውጤት የሚሰጥ የነጥብ ክብደት 10 በመቶ ይይዛል። ቀሪ 20 በመቶውን የአፈጻጸም ውጤት በቅርብ የሥራ አለቃው ለግለሰቡ የሚሰጠው ይሆናል።

ኹለት ወር እና ለበለጠ ጊዜ በኮሚቴ ሥራ የሚሳተፍ ሠራተኛ በግብ ተኮር ተግባራት አፈጻጸም ምዘና ከኮሚቴው ሪፖርት በመነሳት 70 በመቶው በቅርብ ኃላፊው ይሞላል።

ይህን ተከትሎም በጣም ከፍተኛ፣ ከፍተኛ፣ መካከለኛ፣ አጥጋቢ እና ዝቅተኛ አፈጻጸም ተለይቶ ለባለቤቱ እውቅና የሚሰጠው መሆኑንና የምዘና ስርዓቱ የግለሰቡን ጥንካሬና ጉድለት በመለየት አፈጻጸሙ በቀጣይ የሚሻሻልበትን ስልት እንዲያሳይ መመሪያው ያትታል።

የሠራተኛው የስድስት ወራት ግብ ተኮር ተግባራት አፈጻጸም ውጤት በየ15 ቀኑ እና በየወሩ በሚካሄድ ግምገማ ላይ ተመሥርቶ በቅርብ የሥራ ኃላፊው የሚሞላም ነው።

በመመሪያው መሠረት የስድስት ወር አፈጻጸም ማጠቃለያ ምዘና ውጤት ላይ በሥራ ቡድኑ አባላትና በቅርብ የሥራ ኃላፊው መካከል ልዩነት ካለ መጀመሪያ በጋራ ውይይት ለመፍታት ሙከራ ተደርጎ፣ በዚህ ካልተቻለ ግን በመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ የሚሰጥ ውሳኔ የመጨረሻ ተደርጎ ይወሰዳል።

የሠራተኛው የስድስት ወራት አጠቃላይ የአፈጻጸም ውጤትም በተቋሙ ማኔጅመንት ኮሚቴ እንዲፀድቅ ይደረጋል።

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የመንግሥት ሠራተኞችን ሥራ አፈጻጸም ለመመዘን የወጣን መመሪያ አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ ካፀደቀበት ሐምሌ 1/2014 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል።


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች