የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሠራተኞች ተቋሙ ከፍተኛ በደል እያደረሰብን ነው አሉ

0
1758

የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሠራተኞች ተቋሙ ከፍተኛ በደል እያደረሰብን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ለደህንነታችን ሲባል ሥማችን አይጠቀስ ያሉት ሠራተኞቹ የኑሮ ውድነቱን ያላገናዘበ ዝቅተኛ የሥራ ክፍያን ጨምሮ የሠራተኞችን የተለያዩ ቅሬታዎች ለመፍታት ሙከራ አያደርግም ሲሉ ተናግረዋል።

ከአራት ሺሕ በታች የሚከፈላቸው ሠራተኞችን እንዲያሳውቅ በሲቪል ሰርቪስ ቢጠየቀም፣ ከ4 ሺሕ በታች የሚከፈለው ሠራተኛ የለም በማለት መልሷል። ይሁን እንጂ፣ ከአንድ ሺሕ አንድ መቶ ጀምሮ እስከ አራት ሺሕ ብር ዝቅተኛ ወርሃዊ ደሞዝ የሚከፈላቸው በርካታ ሠራተኞች አሉ ነው ያሉት። ይህንም ገጽታውን ላለማበላሸት ሳያደርገው እንዳልቀረ ጠቁመዋል።

የሰው ኃይል ያልተመደበባቸው በርካታ ክፍት የሥራ መደቦች እንዳሉ ገልጸውም፣ የሠራተኞችን የሥራ አቅምና የኑሮውን ሁኔታ አስጠንቶ ሊያስተካክል አልቻለም የሚል ቅሬታ አቅርበዋል።

እንዲሁም፣ ከአምስት ዓመታት በፊት ለዩንቨርሲቲው ማህበረሰብ መኖሪያ ቤት ለመሥራት አዲስ አበባ ውስጥ ሶስት ሠፋፊ ቦታዎችን የተረከበ ቢሆንም፣ ግንባታው እስካሁን ካለመጀመሩም በላይ ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እንኳን ማሳወቅ አይፈልግም ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ የሠራተኞቹን የቤት ችግር ይፈታል የተባለ ፕሮጀክት፣ በቀድሞው የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት (ዶክተር አድማሱ ፀጋዬ) አስተዳደር ወቅት ባለ 300 ገጽ ጥናት ተደርጎ ወደ ተግባር እንደሚገባ የተገለጸ ቢሆንም፣ አሁን ያለው አስተዳደር ግን ኮሚቴውንም አፍርሶ ሠራተኛውን በኮንደሚኒየም ተደራጁ የሚል ምላሽ እየሰጠ ነው። ስለሆነም ዩንቨርሲቲው በአፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ነው ያሉት።

እንዲሁም የግቢውን ሠራተኞች አቅምና መጠን ያላገናዘበ ኹለት የሠራተኞች መመገቢያ ካፌ ብቻ መኖሩን ጠቅሰው፣ ካሉትም በ45 ብር መመገብ አቅቷቸው፣ ከዩንቨርሲቲው አቅራቢያ ከሚገኘው የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የሠራተኞች ካፌ ሄደው ምሳ የሚመገቡ ሠራተኞች መኖራቸውን ገልጸዋል። ሌሎች ተቋማት ለሠራተኞቻቸው ከዚህ በእጥፍ ባነሰ ዋጋ እንደሚያቀርቡም አክለዋል።

ተቋሙ ራስ ገዝ (autonomous) ልሆን ነው ካለ የቆየ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ወደ ተግባር መምጣት አልቻለም። ከዚህ ባለፈም ጥናቱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና መቼ ተግባራዊ እንደሚደረግ ለሠራተኞች እንኳን ግልጽ አይደለም ነው ያሉት።

በግቢው ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች ተብሎ ከተጀመሩ ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ ሕንጻዎች ቢኖሩም ለብዙ ጊዜ በጣም ተጓተዋል፣ ይህ የሆነበት አሳማኝ ምክንያትም ለሕዝብና ለሠራተኛው ግልጽ አይደረግም ሲሉ ተደምጠዋል።

ተቋሙ ለሠራተኞች የትምህርት ዕድል እንዲሁም ነጻ ሕክምና የሚሰጥ በመሆኑ ይህ ያስመሰግነዋል ያሉት ሠራተኞች፣ ይሁን እንጂ ብዙ መሠራት ያለባቸውን ጉዳዮች ከወሬ በዘለለ ተግባራዊ አያደርግም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ሠራተኛው በብዙ ችግር ውስጥ እያለ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለተቀመጡ አካላት ዘመናዊ የሆኑ የቅንጦት መኪኖችን ይገዛሉ፣ የመንግሥት በጀትም ለታለመለት ዓላማ ሳይውል እየባከነ ነው በማለት ገልጸዋል።

ስለሆነም፣ በዩንቨርሲቲው አስተዳደር ክፉኛ መማረራቸውን አንስተው፣ አስተዳደሩ ሠራተኞችን ሰብስቦ ለማወያየት ሞክሮ እንደማያውቅ፣ ይሁን እንጂ ኹሉም ሠራተኛ በርካታ መናገር የሚፈልገው ነገር አለ፣ ቅሬታ ለማሰባሰብ እንዲሁም ሰብስቦ የሚያናግረንን እየጠበቅን ነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ የተነሳውን ቅሬታ መሰረት በማድረግ ከዩንቨርሲቲው ማብራሪያ ለማግኘት ብትሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here