የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን በጨረታ ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች መሸጥ እንደሚፈልግ አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው የጨረታ ጥሪ ላይ እንደተመለከተው፣ የአገር ውስጥ እና ዓለም ዐቀፍ ባለሀብቶች በስኳር ፋብሪካዎቹ ግዢ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል። ለሽያጭ የቀረቡት ስኳር ፋብሪካዎችም ኦሞ ኩራዝ 1፣ 2፣ 3 እና 5፣ አርጆ ደዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ ናቸው።
የገንዘብ ሚኒስቴር ጨረታውን ያወጣው በዘርፉ ተወዳዳሪነትን ከፍ ለማድረግ እና የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ለማሟላት በማለም መሆኑን አስታውቋል። ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ፍጆታን ለመሸፈን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስኳር ከውጪ አገራት እንደምታስገባ የተናገረው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ ስምንቱ ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታ መሸጋገራቸው ተወዳዳሪነትን እና ምርትን ይጨምራል ብሏል።
የስኳር ምርት ዘርፍ ማደግ የስኳር ሸንኮራ አገዳ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ላሉ የማኅብረሰብ ክፍሎች ሕይወት እና ገቢ መሻሻል ያስችላልም ተብሏል። የገንዘብ ሚኒስቴር ለጨረታ ያቀረብኳቸው የስኳር ፋብሪካዎች በቅርቡ የተገነቡ እና የሚገኙባቸው ስፍራዎችም ለሸንኮራ አገዳ ምርት ምቹ፣ ከፍተኛ የውሃ ሀብት ያለባቸው፣ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው መሆናቸውን ገልጿል።
የስኳር ፋብሪካዎቹን ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው የአገር ውስጥ፣ ዓለም ዐቀፍ ወይም ጥምር ተቋማት ፍላጎታቸውን የሚገልጽ ሰነድ እንዲያቀርቡ የገንዘብ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።
ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014


