እውነት ኢትዮያዊ መልኩን አልቀየረም?

1
987

ብዙዎች ይሟገቱበታል። ‹‹አሁን እየታየ ያለውን የእርስ በእርስ ግጭትና ጭካኔ የተሞሉ ድርጊቶችን እያየን ‹ኢትዮጵያዊ ደግ ነው› ማለት መታበይ ነው›› የሚሉ ብዙዎች ናቸው። በአንጻሩ ‹‹የለም! ክፋት በየዘመኑ አለ። እንጂ አሁንም ኢትዮጵያዊያን መልካችን አልጠፋም።›› የሚሉ አሉ። በምግባርም ሆነ በስብእና በኩል በፍጽምና ሰናይም ሆነ እኩይ የለም የሚሉቱ፣ አማካዩ ነው መልካችን ሲሉ ይደመጣል። ይህ ሁሉ ዕይታ ከምን መጣ? እውነት እንደሚባለው ኢትዮጵያዊ መልኩን አልቀየረም? መልኩስ ምን ነበር? ቀይሮስ ከሆነ ምን ይደረግ? እነዚህ ጥያቄዎች ተነስተዋል። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ የተለያዩ ጥናቶችን በማጣቀስና በተለያየ ዘርፍ ያሉ ባለሞያዎችን በማነጋገር የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

ለመግቢያ

መልክ መታወቂያ መገለጫ ነው። ይህም በአካል የሚታይ ውጪአዊ ገጽታ ማለት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ከስብእና (Personality) ጋርም የተገናኘ ነው። ታድያ በርካታ ምኁራን እንደሚስማሙት፤ አገራት የየራሳቸው የተለያየ መልክ አላቸው። መልካቸው የዜጎቻቸው የቆዳ ቀለም ወይም በሚኖሩበት አካባቢ ያለው የአየር ጠባይ አይደለም። ዋናው መልካቸው በሥነምግባር ውስጥ የሚገለጸው ‹ስብእናቸው› ነው።

ኢትዮጵያዊያን/ኢትዮጵያዊያት ስለራሳቸው ‹እንዲህ ነን› ብለው እንደሚናገሩ ሁሉ፣ የቀሪው ዓለም አገራት ሕዝቦችም በአብዛኛው እንደ አገር ወይም እንደ ሕዝብ የሚጋሯቸው ምግባራት እንዳሉ ይገልጻሉ። ያንንም መገለጫ መልካቸው ወይም ስብእናቸው አድርገው ይጠቅሱታል። በአብዛኛውም ነን የሚሉት በጎውን እንጂ እኩይ የሆነውን እንዳልሆነ ልብ ይሏል!

በአንጻሩ ‹የዚህ አገር ሕዝቦች እንዲህ ናቸው› ብሎ መናገር መፈረጅ ነው ብለው የሚያምኑ ጥቂት አይደሉም። ግን እንደዛም ሆኖ የተለያዩ አገራት የየራሳቸው የሆነ ‹ስብእና› ያላቸው መሆኑ አይካድም። ‹‹ለግለሰብስ ይሁን፣ እንዴት ነው እንደ አገር የሕዝብ ‹ስብእና› ማለት የሚቻለው?›› የሚል ጥያቄ ይነሳል። ለዚህ መልስ በመስጠት እንዝለቅ።

ክርስቲያን ጃሬት የተባለ የሥነልቦና ባለሞያ እና ደራሲ ይህንኑ ጥያቄ በአንድ ጽሑፉ ላይ አንስቷል። ‹የተለያዩ አገራት በእርግጥ የተለያየ ስብእና አላቸው/Different nationalities really have different personalities/ የሚል ርዕስ በሰጠው በዚህ ጽሑፉ ላይ፣ የተደረጉ ዓለም ዐቀፍ ጥናቶችን አውስቷል። ጥናቶቹ የሥነልቦና ጉዳይ አጥኚዎች ከተለያዩ አገራት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ያደረጉት የስብእና ምዘና (personality test) ነው። የዚህ ጥናት ውጤትም ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር የተለያየ ሆኖ ሲገኝ፤ በአንድ አገር ውስጥ ግን በአማካይ ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል አሳውቋል።

እንደ ክርስቲያን ገለጻ፣ እነዚህ በጥናት የተገኙ የስብእና ልዩነትና አንድነቶች በተለያየ መነሻ ምክንያት ከምንሰጠው ‹ፍረጃ› ጋር ተመሳሳይ አይደለም፤ ወይም ላይሆን ይችላል።

በዚህ መሠረት ታድያ ለማሳያ ብሎ ኹለት ጥናቶችን ጠቅሷል። አንደኛው በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2005 ይፋ የተደረገና 12 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ከ51 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ ሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት ነው። በዚህ ጥናት በተገኘ ውጤት መሠረት ለምሳሌ ‹አዳዲስ ነገሮችን መለማመድ› ላይ ጀርመኖች ከፍተኛ ነጥብ ሲያገኙ፣ ቻይናዊያን እና አይሪሾች ግን ዝቅተኛ ነጥብ አግኝተዋል።

‹‹ይህ አማካይ ነው። መዘንጋት የሌለብን ቻይናዊያን የሆኑና ከጀርመናዊያን በላይ አዳዲስ ነገሮችን ለመልመድ የሚፈጥኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለውን ነው።›› ሲል ክርስቲያን በጽሑፉ ያስረዳል። በዚህ የተነሳም እንደ አገር የሕዝብ ስብእና ምዘና ማድረግና ውጤቱንም ለመተንተን አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችልና፣ ‹የእዚህ አገር ዜጎች በአብዛኛው እንዲህ ያለ ጠባይ አላቸው› ሲባል አማካይ መሆኑን ልብ ማለት እንደሚያስፈልግ ነው ያስረዳው።

ኹለተኛው ጥናት ደግሞ በ2007 የተሠራና ከ17 ሺሕ በላይ ከ56 አገራት የተውጣጡ ሰዎችን ያሳተፈ ነበር። በዚህም ከቀድሞው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ውጤት ነው የተገኘው። ማለትም በአገራት መካከል የተለያየ ስብእና የታየ ሲሆን፣ በየአገሩ ግን በአማካይ ተመሳሳይ ስብእና እንዳለ ለማየት ተችሏል።

በእነዚህ ጥናቶች መሠረት የዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜጎች በቶሎ ተግባቢዎች ሲሆኑ፣ ጃፓናዊያን እምብዛም ተግባቢ ያልሆኑ ናቸው ተብሏል። አፍሪካዊያን በአሳቢነት ከምሥራቅ እስያዊያን የተሻሉ እንደሆኑም ተጠቅሷል። ጥናቱ ይህን ያስቀመጠው ለእያንዳንዳቸው ነጥብ በመስጠትና ከፍተኛና ዝቅተኛ ነጥብ ያገኙትን በመለየት ነው።

ይህ አንድነትና ልዩነት ታድያ ከየት ይመነጫል የተባለ እንደሆነ፣ በተወሰነ መጠን ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ሳይሆን እንዳልቀረ ክርስቲያን ይጠቅሳል። እንዲሁ በዘርም ሰዎች የራሳቸው የሆነ ጠባይ ወይም ስብእና ይኖራቸዋል። ከዛም ባለፈ ባህል፣ እምነት፣ ስርዓት ብሎም አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተጽእኖም ማኅበረሰብና አገር አንዳች መልክ እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል ብሏል።

በጥቅሉ ግን እንዲህ ያለው አካሄድ አገራዊ መልክን ያሳያል። ክርስቲያን በጽሑፉ እንደጠቀሰውም፣ እነዚህ በአገራት መካከል ስብእናን መሠረት ያደረጉ ልዩነቶች የየአገራቱን የወደፊት አካሄድ ከቀደመው ይልቅ ለመገመት ያስችላሉ።

ወደተነሳንበት ነገር እንመለስ። ኢትዮጵያዊያን በምን ይታወቃሉ?

ኢትዮጵያዊ መልክ?

ዓለማየሁ ተክለማርያም (ፒኤችዲ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ፍላጎት እና አካትቶ ትምህርት ተባባሪ ፕሮፌሰርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ናቸው። እንደ አገር ሕዝብ በጋራ የሚታወቅበት ወይም ራሱን ነኝ ብሎ የሚገልጽበት ስብእና መነሻው ማኅበረሰብ የገነባው ባህል እና እሴት እንደሆነ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት አጠር ያለ ቆይታ ጠቅሰዋል።

በዛም የሚታይና የማይታይ ጠባይ ወይም ‹ባህሪ› አለ ያሉ ሲሆን፤ ‹‹የማይታየው ሐሳባችን፣ አመለካከታችን፣ ርዕያችን፣ እምነታችን እና ስሜታችን ነው። የሚታየው ደግሞ ያሰብነውን የምንገልጽበት መንገድ ነው።›› ብለዋል። የአንድ ማኅበረሰብ እሴትም ከሐሳብ እንደሚጀምር ጠቅሰው፣ የዚያ መሠረት ደግሞ በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት እና በእምነት ተቋማት እንደሆነ ነው ያስረዱት።

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰው አክባሪ፣ እንግዳ ተቀባይ የሆነ፣ አስተዋይና ጥበብን የሚያደንቅ፣ ነገ-በእኔ ማለትን የሚያውቅና በሰው ክፉ የማያደርግ፣ የጎረቤቱን ልጅ ጭምር የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለበት የሚሰማው ሕዝብ ነው ሲሉ ነው ኢትዮጵያዊ መልክን የገለጹት።

‹‹የትኛውም አገር ሕዝብ ስለራሱ መጥፎ ነገር እንደማይናገር የታወቀ ነው።›› ያለችው ደግሞ ሥሟ እንዲጠቀስ ያልፈቀደችውና በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በስፋት የምትሳተፍ ወጣት ናት። ወጣቷም ዓለማየሁ በሰጡት ‹ኢትዮጵያዊ መልክ› ተብሎ በሚገለጸው ነጥብ ትስማማለች።

‹‹የሥነ ልቦና እና ሥነ አእምሮ ባለሞያዎች ሲናገሩ እንደምሰማው፤ ራሳችንን ስንገልጽ በጎውን ማጉላትና በጎውን መናገር ተገቢ ነው። ጀግና ነን፣ ደግ ሕዝብ ነን። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ብዙ ታሪኮችን መጥቀስ ይችላል። ግን ፍጹም ነን ማለት አይደለም። ክፋትና ጥፋት ሊገኝብን ይችላል። ቢሆንም ግን በበኩሌ በበጎው መጠራትን ነው የምመርጠው። እናም የኢትዮጵያ መልክ ሲባል አሸናፊነት፣ ጀግንነት፣ ታማኝነት፣ ደግነትና እንግዳ ተቀባይነት ነው ወደ ሐሳቤ የሚመጣው።›› ብላለች።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማራች እንደመሆኑ ብዙ በጎ አድራጊዎችን እና ቀና ሰዎችን እንደምታገኝ የምትናገረው ወጣቷ፣ በዛም የተነሳ የኢትዮጰያዊያንን በጎነት እንዳየች ትገልጻለች። እናም የኢትዮጵያዊያን መገለጫም ይኸው በጎነትና ከተጎዱ አጠገብ መቆም መሆኑን በጽኑ አምናለሁ ብላለች።

ቅድስት አሰልፍ የዓለም ዐቀፍ እርቅና ሰላም ግብረ ሰናይ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ እና የኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባል ናቸው። በበኩላቸው ይህንን ሐሳብ የሚጋሩ ናቸው። ኢትዮጵያዊ ትልልቅ በሆኑ የሃይማኖት መጻሕፍት የተመሰከረለት፣ መልካምነቱ የሚበዛ፣ ለተቸገረ ሳይሰስት ካለው አካፍሎ የሚሰጥ ሕዝብ ነው ብለዋል። በእርሳቸው መረዳት ኢትዮጵያዊ መልክ ማለትም ይኸው ነው።

እርግጥ ነው፤ ምንም እንኳ ብዙ እንከኖችና እኩይ ነገሮች ያሉና የማይጠፉ ናቸው። ደግሞም ከላይ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ በተነሳው መንገድ በጥናት የታወቀ አይሁን እንጂ፣ አገር የራሷ መገለጫ የሆነ ‹ስብእና› አላት በሚለው መሠረት የኢትዮጵያዊ መልክ ብዙውን ጊዜ የሚገለጸው አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ነው። በእርግጥ ከውጪ በሚመለከት ዐይን ውስጥስ ኢትዮጵያዊ መልክ ምን ይመስላል? ይህ ሌላ ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያዊ መልኩን ቀይሯልን?

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ አስተያየት ሰጪዎችን ጨምሮ ብዙዎች የሚስማሙበትና ኢትዮጵያዊ መልክ እንደሆነ የሚታመነው አብዛኛው እሴት ተቀይሯል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ‹‹አሁን ክፋት በዝቷል። ስግብግብ፣ ራስ ወዳድና አስመሳይ ሆነናል›› የሚሉም ጥቂት አይደሉም። እሴትና ባህል እየጠፋ፣ እንደ አገር ያለን ስብእና እኩይ እየሆነና መልካችን እየተቀየረ ነው ብለው የሚያዝኑም አሉ።

ዓለማየሁ አንዱ ናቸው። ኢትዮጵያዊ መልክ እየጠፋና እየተሸረሸረ ነው ብለው ያምናሉ። ይህም በአንድ ጀንበር የሆነ ወይም ከሦስትና አራት ዓመት በፊት የጀመረ አይደለም ባይ ናቸው። ይልቁንም ወደኋላ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ወዲህ ጀምሮ የሆነ ነው ይላሉ።

በተለይም ደርግ አስቀድሞ ከነበረው ስርዓት በአንጻር ሆኖ የራሱን ርዕዮተ ዓለም ባወጀ ጊዜ እሴቶች መናድ እንደጀመሩ ያስረዳሉ። ‹‹ይህም የተጀመረው ፈጣሪን ከመካድ ነው። ያኔ የሞራልና የሥነምግባር እሴቶች ተናዱ። ያ ሲሆን ደግሞ ሰው ባዶውን ይቀራል።›› ብለዋል።

‹‹ወላጆችም ተሸነፉ›› ያሉት ዓለማየሁ፣ የፖለቲካው ርዕዮተ ዓለም ሁሉን እንደጠቀለለው ያስረዳሉ። ይህም እንደ ውሃ እያሳሳቀ የሚወስድ አካሄድ፣ በትንሹ ‹ትልቅ ሰው ሲመጣ ከወንበር መነሳት ምን ይጠቅማል?› ከሚል ተነስቶ እንዳደገ ነው የሚያስረዱት። ያም ሰውን በሰውነቱ ብቻ የማክበርን እሴት የሚያሳጣ ሆነ። ወላጆችም ይህን መልክ መመለስ ሳይችሉ ቀሩ።

በኋላም የመጣው ኢሕአዴግ አስቀድሞ በተናደው እሴት ላይ ‹የጎሳና ብሔር ማንነት› በመክተት መከፋፈልና አለመተማመንን አስርጿል ይላሉ፤ ዓለማየሁ። ‹‹እኛ ራሱ ሳናውቀው ‹ይህ ሰው አገሩ የት ነው?› ብለን መጠየቅ ለምዶብናል›› ሲሉም የሆነውን ይገልጻሉ።

ቅድስት በበኩላቸው በዚህ ሐሳብ በተወሰነ መልኩ የሚስማሙ ቢሆንም፣ መልካሙን እሴትና ኢትዮጵያዊ መልካችንን ጨርሶ አጥተናል ብለው አያምኑም። ‹‹ችግሩ እሴትን ጠብቆ የመጓዝ ነገር መጥፋት ነው። የሉላዊነት ተጽእኖ እኛነታችንን ማስጣሉ፣ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር ጥሰትና የመሳሰለው ሰዉን ከሥነምግባር አውጥቶ እኩይ ምግባር ታየ እንጂ ብዙ ነገራችን አሁንም ጥሩ ነው። ማኅበረሰባችን አሁንም መልካምነቱ ያመዝናል ብዬ ነው የማምነው።›› ሲሉ ኢትዮጵያዊ መልኩ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቀየረና ፈተና ግን እንደገጠመው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

ለአዲስ ማለዳ ሐሳቧን ያጋራቸው በበጎ አድራጎት ተሳታፊ የሆነችው ወጣት ግን ከኹለቱም ሐሳብ በተለየ እንደውም አሁን ነው መልካችን የታየው ትላለች። ‹‹በእኛው ችግር የተነሳ እርስ በእርስ መጥፎ ነገር ውስጥ ገብተን ይሆናል፤ ገብተናልም። እንደ ገጠመን ችግርና እንደፈተናው ቢሆን ኖሮ አንድ ጀንበር እንኳ እንደ ሕዝብ በአንድ ላይ ባልተገኘን ነበር። ነገር ግን በዛ መካከል ቀናነት፣ ደግነትና ትዕግስት ያሉ በመሆኑ ነው አሁንም ያለነው።›› ብላለች።

በተለይ ማኅበራዊ ሚድያው በዚህ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደረ የምትናገረው ወጣቷ፣ የዜና ሽፋን የሚያገኙትና በብዛት የሚጎሉት የጥፋት ጉዳዮች መሆናቸው ነው መልካችን ተቀይሮ ይሆን ብለን እንድንጠራጠር ያደረገን ባይ ናት።

‹‹ውሎዬ ከደጋግ እና መልካም ኢትዮጵያዊ ሰዎች ጋር ነው። በጥቂት እኩይ ምግባር ባላቸው ሰዎች ኢትዮጵያዊነት መልኩን ቀየረ ብዬ አልናገርም። ከከተማ በሥራ ምክንያት ብዙ ተንቀሳቅሻለሁ። ያየሁት መልክ የተቀየረ አይደለም። በስግብግቡ ነጋዴ፣ በዘረኛውና ጎሰኛው አይደለም ኢትዮጵያዊነት እንዲገለጽ የምፈልገው። ነገር ግን እንዳልኩት ችግሮች አሉ። ለወደፊቱ በሥነምግባርና እሴት ላይ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብንም አምናለሁ።›› ስትል ዕይታዋን ገልጻለች።

ማን ይጠየቅ?

የኢትዮጵያ መልክ ናቸው የተባሉ በጎ እሴቶች ወይም አገራዊ ስብእና ‹ጨርሶ ጠፍተዋል፣ ጎድለዋል ወይም ትኩረት ስላገኙ ነው እንጂ መልካሙ ያመዝናል› በሚሉ ዕይታዎች ውስጥ አግኝተናቸዋል። አስቀድሞስ ነገር ይህን ጉዳይ ለማንሳት ምን ምክንያት ተፈጠረ? ማንስ ነው ለዚህ ጉድለትና ጥርጣሬ መፈጠር ማን ይጠየቅ?

ዓለማየሁ ተክለማርያም ተጠያቂ የሚያደርጉት የመንግሥት ስርዓትን ነው። ‹‹ትውልዱ አይወቀስም፤ ማኅበረሰብም አይወቀስም። መንግሥት ነው የሚወቀሰው። በፖሊሲና ርዕዮተ ዓለም ሕዝብን የሚያስተዳድረው መንግሥት ነው። መንግሥት ርዕዮተ ዓለሙን ለማስረጽ ሲል ብዙ አደጋዎችን ያስከትላል።›› ሲሉ ዕይታቸውን ገልጸዋል።

‹‹የሕዝብ ጠላት መጥፎ ገዢዎችና መጥፎ መሪዎች ናቸው።›› የሚሉት ዓለማየሁ፣ ‹‹እነዚህ ገዢዎች ለአገዛዝ እንዲመቻቸው ሲሉ የማኅረሰቡን እሴት ከፋፈሉት። እሴትን ናዱ። የሰው ልጅ ክብር የሌለው ሆነ። የሆነ ብሔር እየተሰጠ ሆነ ሰው የሚመዘነው።›› ብለዋል።

ይህንን ተከትሎም እኩይ የሚባሉ የመገዳደል፣ የዝርፊያና የስርቆት፣ የሙስና እንዲሁም መሰሉ ሁሉ ተከትለዋል። በሥልጣኔ ቁንጮ የተባሉ አገራት አብዛኞቹ ሥነምግባራቸውን ጠብቀዋል ሲሉ ጃፓንን እንደምሳሌ ጠቅሰዋል። እናም ትውልድንም ሆነ አገርን መልክ የሚሠራውና የሚያፈርሰው ስርዓት መሆኑ ይሰመርበት ሲሉ አሳስበዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃይማኖተኛ ሕዝብ በብዛት ባላቸው አገራት፣ ከትምህርት ተቋማት በተጓዳኝ በእሴትና የአገር መልክ ግንባታ ላይ ሃይማኖት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል። ቅድስት በበኩላቸው በተለይ የሃይማኖት ተቋማት የነበራቸውን ድርሻ አውስተው፣ ባለፉት 30 በላይ የሚሆኑ ዓመታት አመራሮች ተቀባይነት ለማግኘትና ዙሪያ ገባውን ለመቆጣጠር የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ፖለቲካን አስገብተዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።

‹‹ከሥነምግባር የወጡና ፖለቲከኛ የሆኑ ሰዎች ወደ እምነት ተቋማት ገብተዋል። በጣም ነው የሚያሳዝነው።›› ብለዋል። ትክክለኞቹ ሳይታዩ ነገር ግን በፖለቲካ ዓላማ የገቡ ጥቅመኞችና ዘረኞች እንደበዙም ጠቅሰዋል። እናም በተቻለ መጠን ትክክለኛው ሰው ትክክለኛ ቦታ የመቀመጥ እድል ቢያገኝ፤ ሁሉም የየራሱን ሥራ ለመሥራት ይችል እንደነበር እንደሚያምኑም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ የትምህርት ስርዓት ራሱ እሴቶችን ንዷል ብለው ያምናሉ፤ ዓለማየሁ። በቀደሙ ዘመናት ከምዕራቡ በኋላም ከምሥራቁ ዓለም የመጡ የትምህርት ስርዓቶች አገር በቀል እውቀትን ቸል ያሉ መሆናቸው ዋጋ አስከፍሎናል ባይ ናቸው። በደርግ ዘመነ መንግሥትም ይህን የተቃወሙ ሰዎች ዕጣቸው ሞት ይሆን እንደነበር አውስተዋል። ይህም ኢትዮጵያዊ የሆኑ ከስብእና ባሻገርም ያሉ ግዙፍ እሴቶችና መልኮች እንዲጋረዱ ማድረጉን ነው የጠቀሱት።

‹‹በኢሕአዴግ ደግሞ ትምህርት አለ/ነበር እንዴ?›› ብለው የሚጠይቁት ዓለማየሁ፣ ‹‹ሕዝብ ተምሮ እንዲያድግ እና ወደ አንድነት እንዲመጣ አይፈለግም። ያ ስርዓት መምህርን በፕላዝማ ተክቷል።›› ሲሉ ይወቅሳሉ።

ስርዓት ከላይ ከተበላሸ ሁሉም ይበላሻል ብለው በጽኑ የሚያምኑት ዓለማየሁ፣ የሃይማኖት ተቋማትም በተመሳሳይ የፖለቲከኞች ሰንሰለት ሰለባ ሆነው ብዙዎቹ ቀዳሚውን ሥራቸውን እንዲተዉ መደረጉን ያነሳሉ። ‹‹በተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት የሕዝብ ገንዘብ ሲዘረፍ ይታያል። ያሳፍራል። ይህ የእሴት መሞት ነው።›› ብለዋል።

ምን ይደረግ?

ዓለማየሁ አሁን ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ስርዓት ተስፋ ያደርጋሉ። ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩን ብንተባበር፣ ብንሠራና ብናግዝ ጥሩ ነው። ጊዜ ብንሰጠው ውጤታማ መሆን የሚችል ሰው ነው። እኛ ሠርቶ ካሳየን እጥፍ ብንሠራ ጥሩ ለውጥ እናመጣ ነበር። ይህን የምለው እንደ አንድ ግለሰብ ነው፤ እንደ ፖለቲከኛ ወይም ሌላ አይደለም።›› ብለዋል።

ቅድስት በበኩላቸው፣ ‹‹መልካችን አይጠፋም። የተሰጠን ነው።›› በማለት ይጀምራሉ። ‹‹ተባብረን መሥራት ነው ያለብን። መናበብና መፈላለግ ብሎም ልጆችን ማስተማር ያስፈልጋል። ድሮ ግብረገብ ትምህርት ነበር። ያንን ትምህርትም መመለስ ያሻል። አስተዳደርም ቢስተካከል ጥሩ ነገር ይመጣል። ኢትዮጵያዊ መልክ ግን የማይለወጥ ነው ብዬ አምናለሁ።›› ብለዋል።

ወጣቷና ሥሟ እንዳይጠቀስ ያሳሰበችው በጎ ፈቃድ ላይ የምትሠራው ወጣት በበኩሏ፣ ችግሩ ክፉውን ከሚያገንነው ነው ብላለች። ‹‹ኢትዮጵያዊ መልክ አይደለም አገሪቷ ራሱ ፈረሰች እያሉ በየቀኑ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ግን ኢትዮጵያ ምን ፈተናዋ ቢከብድ እንዳሉት አይሆንም። እናም ተስፋን ከመናገርና በጎውን መልክ ከማጉላት ይልቅ ክፉውን የሚያገነው ነው ተጠያቂው። አንድ ሰው ዋጋ አለውና እያንዳንዳችን በጎውን በማጉላት መልካችንን ማድመቅ እንችላለን።›› ስትልም ዕይታዋን በጥልቅ ስሜት ሆና አካፍላለች።

ለመውጫ ይህን እንበል። አስቀድሞ የአገር ስብእናን በጠቅላላ አንስተን ግለሰቦች የዛ አካል የመሆናቸውን ነገር ስናነሳ ነበር። ወዲህ ለመቋጫ ደግሞ የአገር መልክ የግለሰቦች ስብእና ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው የተነገረውን እናንሳ።

‹የጀግና ልጅ ነህ› የተባለና የቀደሙት ወገኖቹ መልክ የጀግንነት መሆኑ እየተነገረው ያደገ ትውልድ፣ የጀግንነትን ሥነልቦና ያዳብራል። ደግ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ትዕግስተኛና ጥበብ ወዳድ ማኅበረሰብ ውስጥ ያደገ አዲስ ትውልድም ያንን መልክ ይዞ ይወጣል። ይህም ማለት የአገር መልክ የዜጎች የየአንዳንዳቸው መልክ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል ማለት ነው። ተከትሎም የግለሰቦችን ማንነት ይሠራል፤ ለአገር የሚኖራቸውን ድርሻም ይቀርጻል። እናም ኢትዮጵያዊ መልኩን ቀይሮም ከሆነ ወደተሻለው መልካም መልክ ለመመለስ፣ ያልጠፋም ከሆነ ይዞ ለመቆየት፤ የግል ስብእናን በአገር የአገርን በግል መነጽር ውስጥ እያዩ በስፋትና በጥልቀት ማስተዋል እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ አሳስበዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

አስተያየት

  1. በእውነቱ የኛን መልክ የሚያደበዝዘው የለም። ዘወትእ ፀዳሉ ያበራል። አንዳንዶች ግን ከሻማው ብርሃን ይልቅ ጨለማውን ስለሚመለከቱ ነው። እንደውም አንዳንዶቹ ኩራዙን አጥፍተው ጨለማ እንዲወርሰን የሚፈልጉ አሉ። ለእነሱ በልባቸው የቅንነት ፀሐይ እንዲወጣ ከመፀለይ በስተቀር ሌላ መላ የለውም። እኛ ገጽ ን ምንግዜም መልካሙን ብቻ እናስተውል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here