“እልም አለ ባቡሩ . . .!?” የጸጥታ ሥጋት ፍልቅል ቅነቷን ያሳጣት – ድሬዳዋ

0
905

ነፋሻማው የወርሃ ጥቅምት ማለዳ አጥንት ድረስ ዘልቆ በሚገባ ብርድ እያንዘፈዘፈን አዲስ አበባ ለቡ ኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ጣቢያ ተገኝተናል። 310 የኢትዮጵያ ብር የከፈልንበትን የባቡር መሳፈሪያ ትኬታችንን በእጃችን ይዘን የመግቢያው በር እስኪከፈት ከወዲህ ወዲያ እየተንጎራደድን የባቡር ጣቢያውን ኪነ ሕንፃ ስናደንቅ፣ ዓይነ ግቡ የሆነ ገፅታ ስናገኝ ደግሞ በተንቀሳቃሽ ስልካችን ምስል ስናስቀር ጊዜውን እንደምንም ገፋነው። ምንም እንኳን በባቡር ጣቢያው የደረስንበት ጊዜ ከሰዓታችን እጅግ አስቀድመን ባይሆንም ጥቅምት ነውና መጠለያ በሌለበት ብርዱ በግላጭ ስላገኘን መሸሸጊያ በመሻታችን ጊዜውን አርዝሞብናል። አዲስ ማለዳ አራት ቡድን ካለው ከዓለም ዐቀፍና ከአገር ውስጥ የዜና አውታሮች ጋር መነሻዋን አዲስ አበባ ለቡ አድርጋ ጅቡቲ ነጋዳ የባቡር ጣቢያ ድረስ በሚጓዘው ባቡር መድረሻዋን ወደ ሼመንደፈር እናት ድሬዳዋ ለማድረግ ዝግጅቷን ጨርሳለች አብራችሁን ዝለቁ።

አሁን ወደ ባቡር የመሳፈሪያው ሰዓት ደርሷልና መንገደኛ የያዘውን ጓዝ ጠቅልሎ ወደ መፈተሻው ቦታ እየተመምን ነው። የባቡር ጣቢያው አገር ውስጥ ለሚጓዙ እና ድንበር ተሸግረው ጉዞ ለሚያደርጉ የተለየ ቅድመ ሁኔታ አለው። ዓለም ዐቀፍ ነውና ጉዞው ለጅቡቲ መንገደኞች ማሟላት የሚጠበቅባቸው የኢሚግሬሽን ጉዳዮች በጥንቃቄ ይሞላሉ። ለትኬት ተቆጣጣሪዎች ትኬቶቻችንን አሳይተን ወደ ባቡሩ ለመሳፈር ከዐሥር ያነሰ እርምጃዎችን አድርገን ቀይ ሰደርያ በነጭ ሸሚዝ፣ ጥቁር ሱሪ፣ ቀይ ቆብ ያደረጉ የባቡር ሠራተኞች በየባቡሩ ፉርጎዎች ደጅ ላይ በተጠንቀቅ ተሰድርው እንድንገባ በፈገግታ ታጅበው ይጋብዛሉ። ባቡሩ በሰላሳ የተለያዩ ማዕረግ ባላቸው ፉርጎዎች የተዋቀረ፣ ዘመናዊነቱ ገና ወደ ውስጥ ሳይዘልቁ ውጫዊ ገፅታውን አይተው የሚፈርዱለት ዓይነ ግቡ ነው። ባቡር ሲባል በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በፈረንሳይ ኩባንያ የተገነባውን የከሰል ባቡር ወደ አዕምሮው የሚመጣ ሰው ለዚህ ባቡር ባዳ ቢሆን አይገርምም።

ለጅቡቲ መንገደኞች የመግቢያ በር የተጓዦችን ቁጥር ያማካለ ነውና መግቢያው አንድ ብቻ ነው። ለአገር ውስጥ መንገደኞች ግን በርካታ መግቢያዎች ቢኖሩም ፉርጎዎቹ በሞሉ ቁጥር ቀጣይ ፉረርጎዎች እየተከፈቱ ለመንገደኞች ዝግጁ ይሆናሉ። ወደ ውስጠኛው የባቡር ክፍል ገብተናል፤ የተመደብንበት ክፍል በኹለት ረድፍ ሦስት ሦስት የሚይዙ እና ኹለት ኹለት የሚይዙ መቀመጫዎች ይገኛሉ። በግምት በአንድ ፉርጎ ውስጥ ከሠላሳ እስከ አርባ ሰው ይገኛል (እኛ ያለንበትን ማለቴ ነው) ኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተሰበጣጠረ አቀፍ ጉዞ እንጂ እንዲያው ባጋጣሚ የተገናኘን አይመስልም። ሕፃናት ከፍልቅልቅ ድምጸታቸው፣ አረጋውያን ከማይጠገብ የዕድሜ ጨዋታቸው፣ ወጣቱ ወንዶች ለአፍታ ከማያምኑት ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ጋር እንዲሁም ሴቶች ከልብ ሰራቂ ፈገግታቸው ጋር በዚህ ባቡር ውስጥ ይገኛሉ። በሦስተኛ ወገን ለሚታዘብ እንደጋዜጠኛ በርካታ ነገሮች ወደ አዕምሮው ይመጣል፤ ምን አለፋችሁ የባቡሩ ገፅታ እጅግ ቀልብን የሚስብ ነው።

የተጋበዝነው የቻይናው የግንባታ ኩባንያ ሲሲኢሲሲ የገነባኹትን የባቡር መስመር ታዘቡልኝ እግረ መንገዳችሁንም የአገራችሁን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጠውን የባቡር አገልግሎት ጎብኙልን የሚል አንዱ የግብዣ አካል ነው። በዚህም መሰረት ባቡሩ ሲንቀሳቀስ የባቡሩን ቻይናዊ ዋና ካፒቴን ጋር ቃለ ምልልስ ልናደርግለት ቀጠሮ ይዘናልና በስልክ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። አሁን ከጥዋቱ ኹለት ሰዓት ሆኗል፤ ባቡሩም የመጨረሻ የተሳፋሪዎችን ግቡ የሚለውን ጡሩምባውን አሰምቶ ደጆቹን ዘግቶ መንቀሳቀስ ጀምሯል። በሰዓት ቀልድ የለም!

ከደቂቃዎች በኋላ ዋና ካፒቴን ቻይናዊው እና ተግባቢው “ሊ” ወደ አለንበት ማዕረግ በመምጣት ጋዜጠኞች በትክክል እኛ መሆናችንን ካረጋገጠ በኋላ የባቡሩን የተለያዩ ማዕረጎችና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸውን ክፍሎች በማስጎብኘት እግረ መንገድም ቃለ ምልልሱን ለማድረግ መጀመር እንደምንችል ነግሮን አስከትሎን ካለንበት ማዕረግ ይዞን ሔደ። በሊ አማካኝነት በርካታ የመንገደኞች ያሉበትን ፉርጎዎች ወይም ማዕረጎች እያቆራረጥን ወደ መመገቢያው ክፍል አመራን ።

መመገቢያው ክፍል እጅግ ቅንጡ እና ኹሉም የተሟላለት ቢባል ማጋነን አይሆንም፤ እንዲያውም ቅንጡነቱን ላየ አንድ ከተማችን ውስጥ የተከፈተ ዝነኛ ምግብ ቤት እንጂ ባቡር ውስጥ ያለ መመገቢያ አይመስልም። ይሁን እንጂ ወንበሮቹ ከአጠቃቀም ጉድለት ወይም ከንፅሕና ካለመያዝ ጋር በተገናኘ ቆሽሸዋል። የወንበሮቹ ልባሶች ወጥ፣ የምግብ ዘይት እና መሰል የምግብ ነገሮች ተደራርበውበት ሮዝ ቀለም የነበረው ወደ መወየብ ተቃርበዋል። የባቡሩ መመገቢያ አዳራሽ ወይም ፉርጎ ምንም እንኳን ኹሉ በኹሉ ቢሆንም የምግብ አገልግሎት ግን አይሰጥም። መንገደኛው በሰሀን የቋጠረውን ምግብ ከፍቶ እንዲመገብ ከማድረግና የታሸጉ ውሃ እንዲሁም ለስላሳ መጠጦችን ከመሸጥ ውጪ, ከትኩስ ነገር አቅም እንኳን ማግኘት ህልም ነው።

የመጀመሪያው ጥያቄ ለዋና ካፒቴኑ ለምን ይኼ ሆነ ስንል ላቀረብንት ጥያቄ አንዳንዴም በፈገግታ፣ እልፍ ሲል በምልክት እና በመከራ ለመረዳት በሚቻል የእንግሊዘኛ ቋንቋው, ምግብ ለመጀመር እና ትኩስ ነገር ለመሸጥ ተጀምሮ እንደነበርና በባቡሩ ግድግዳዎች ላይ ያሉት ሶኬቶችን አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገው የነበረ ቢሆንም መንገደኞች የራሳቸውን የትኩስ ነገር ማፊያዎችን ይዘው በመምጣት እና በመጠቀም የኤሌክትሪክ አደጋ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነው እንደነበርና በዚህም ምክንያት ማቆማቸውን ገለፀልን እኛም “አጃኢብ፤ የእኛ ሰው ነገር!” ብለን በራሳችን አፈርን።

ቀጥለን ደግሞ የጅቡቲ ተጓዦች ወደ ሚገኙበት የባቡሩ ክፍል ደረስን። ሰዓቱ ገና ለጋ እና እንዲያውም የምናቋርጥበት ጋራ ሸንተረሮች እንኳን በወጉ ባልነቁበት በዛ ጠዋት ጫቱ ተጀምሯል፣ ጨዋታው ደርቷል፣ ኹሉም ቀጥ ብሎ በመቀመጥ ፋንታ እግራቸውን ወንበር ላይ ሰቅለው ትንሽ እንደማጋደል ብለው ተቀምጠዋል። ጨዋታቸውን ላየ እልፍ ዘመናትን የሚተዋወቁ እንጂ በአንድ ማለዳ ባቡር ለመሳፈር የተገናኙ መንገደኞች አይመስሉም። እውነት ነው ወደ ምሥራቅ የሰው ተግባቦት አፍታ ይበቃዋል። ጨዋታቸው ቀልብን ይገዛል፣ ተሰምቶ አይጠገብም፣ ደግነትን ከርህራሄ ጋር አዳብሎ ፈጣሪ ችሯቸዋል። በዛ ፉርጎ ውስጥ ቆይታችን አጭር በመሆኑ “አቦ ይመቻችሁ!” የሚለውን ምርቃቴን እንካችሁ ብዬ አለፍኩኝ።

በርካታ ሰው አልባ ፉርጎዎችን አለፍን መታጠቢያ ቤቶች በያንዳንዱ የፉርጎ መጨረሻ ላይ በንፅሕና እና በምቾት አለ። እንዲያው “አመል ያወጣል ከመሀል” ተብሎ የሲጋራ ሱስ ውል ቢልብዎት ማጨሻ ቦታዎችም ተመቻችተዋል። እንዲያው ምን አለፋችሁ ባቡሩ ይኼ ቀረህ የሚባል አይደለም። አሁን ሦስት ተደራራቢ አልጋዎች ያሉት አንደኛ ማዕረግ ክፍል ደርሰናል። ቢያሻዎት መጽሐፍ እያነበቡ፣ ቢመችዎት ደግሞ ተኝተው፣ እንዲያው ቢቀናዎት ደግሞ እየጻፉ ጉዞዎን የሚገፉበት ግሩም ክፍል ነው። ይሁን እንጂ ይህም ክፍል ለተሳፋሪዎች ከሦሰት ሳምንት በፊት ክልክል ሆኗል። ለምን አትሉም? ጉዳዩ ከምግብ ቤቱ ጋር ተመሳሳይ ነው።

መንገደኛው በአግባቡ አይጠቀምባቸውም የሚል ነው። አልጋ ላይ በልተው እዛው ላይ እጃቸውን ማፅዳት፣ በጫማ መተኛውን መርገጥ እና የመሳሰሉት ለእገዳው ትልቁ ምክንያት ነው። እውነትም አዲስ ማለዳም እንደታዘበችው የአልጋዎቹ ጠርዞች እንደ መመገቢያ አዳራሹ ወንበሮች ባይሆኑም ቀለማቸውን እየቀየሩ ነው። ጉብኝታችን ወደ መገባደደቡ ነው ዋና ካፒቴኑም ከአጥጋቢ ፈገግታ እና ልብን ከሚነካ ትህትና ጋር ተሰናብቶን ጥቁር እንግዳ በመሆናችን የመጀመሪያ ማዕረጉን (አልጋ ያለበትን) ፉርጎ ውስጥ ሆነን እንድንጓዝ ቀጭን ትዕዛዝ ለአስተናባሪዎች በማስተላለፍ ተሰናብቶን ኼደ።

የጉዞው ነገር በተለይ የባቡሩ ፍጥነት የኤሊ ጉዞ ነው ሰዓታትን አሳልፈን አሁንም እዛው ነን። የአሸዋ ላይ ሩጫ በሉት። ከአዲስ አበባ ለቡ ባቡር ጣቢያ ከተነሳን ከኹለት ሰዓታት በኋላ ነበር አዳማ የገባነው። ምንድነው ጉዱ? በቃ በዚህ ፍጥነት ነው የሚዘልቀው የሚሉ ጥያቄዎች ከሁላችንም እየተስተጋባ ነው። ብቻ ግን ጋዜጠኛ ወሬ አያልቅበትምና አንዱን ስናነሳ አንዱን ስንጥል፣ በድካም ስንኮራረፍ፣ ዘለግ ላሉ ሰዓታት ስንተኛ ጉዞውን እያጋመስን ነው።

እንቅልፍ የማታውቀው አዲስ ማለዳ ዞር ዞር እያለች የባቡሩን ሠራተኞች ከጉዞ ላይ ጨዋታዎች ባለፈ ስለ ባቡሩ አንዳንድ መረጃዎችን ትሰበስብ ነበር። አስደማሚ ታሪኮች፣ አስደንጋጭ ክስተቶችን፣ ሳቅ የሚያጭሩ ሁኔታዎችንም ከሠራተኞች ማድመጥ ችላለች። በባቡሩ የጥገና እና ጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኛው ጌታነህ አለሜ ስለ ባቡሩ ፍጥነት እንዲህ ይናገራል “ፍጥነቱ እንደዚህ አልነበረም በጣም ፈጣን ነበር ቢያንስ 80 ኪሎሜትሮችን በሰዓት ይጓዝ ነበር። ነገር ግን በርካታ አደጋዎች በአካባቢው ሰዎችና እንስሳት ላይ እያደረሰ እና ይህንም ተከትሎ ለበርካታ ጊዜያት እገታ እንደተፈፀመበትና ይህንም ተከትሎ መንግሥት አቅጣጫ በማስቀመጥ አሁን 40 ኪሎ ሜትር እንዲያው ከፍ አለ ከተባለም 50 ኪሎ ሜትሮችን ብቻ በሰዓት እንዲጓዝ ተደረገ” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አጫውተዋል። በዚህ ጊዜ ግን የሁላችንም ሐሞት ፈሰሰ፤ “እንዴት ነው ታዲያ በዚህ አካሔድ ድሬዳዋ ድረስ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ የሚገፋው?” ብለን መልስ ያላገኘንለትን ጥያቄ አንስተናል።

በማኅበረሰብ ጤና ብትመረቅም በሙያዋ ሥራ ባለማግኘቷ በባቡሩ ውስጥ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ በመሆን የምታገለግለው የድሬዳዋ ወጣት ትዕግስት ስለሺም እንዲህ ስትል የማትረሳውን ገጠመኝ ለአዲስ ማለዳ ተናገረች። “እንደተቀጠርኩ ሳምንት ሳይሞላኝ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ጉዞ ስናደርግ አንዲት ነብሰ ጡር ምጥ ያዛት፤ ኹላችን ተደናገጥን በተለይ ደግሞ እኔ አዲስ ስለነበርኩ እጅግ ደነገጥኩ። ወዲያው የሬዲዮ ግንኙነት በማድረግ ወደ ቀጣዩ ጣቢያ ፍጥነት በመጨመር ተጉዘን አምቡላንስ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ በማድረግ ወደ ጤና ተቋም በመድረሷ በሰላም ተገላግላለች” ስትል አጋጣሚውን ትተርካለች። በእርግጥ ባቡሩ ውስጥ ምንም ዓይነት የሕክምና እና የመጀመሪያ እርዳታ መስጫ ማዕከል አለመኖሩ ትንሽ ቅር የሚያሰኝ ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ባቡር ሐዲዱ በርካታ ምሥራቃዊውን የኢትዮጵያ ክፍል ቢያቋርጥም ነገር ግን እንደ ቀደመው የባቡር መስመር በኅብረተሰቡ ዘንድ የእኔነት ስሜት ተቀባይነት አላገኘም። ለዚህም ይመስላል በ19 ወራት የአገልግሎት ዕድሜው በርካታ እገታዎች፣ የባቡር ሐዲድ ማያያዣ ብሎኖች በሕገ ወጥ መንገድ ተፈተው መወሰድ፣ ባቡሩ በሚያልፍበት ወቅት ድንጋይ በመወርወር መስኮት መስበር እና መሰል ጉዳቶች የደረሰበት። አዲስ ማለዳ በባቡሩ ውስጥ ቅኝት ባደረገችበት ወቅትም በቀኝ እና በግራ ኹለት መስኮቶች በድንጋይ ጥቃት ደርሶባቸው መሰበራቸውን አስተውላለች።

እጅግ ከተራዘመው፤ ምናልባትም ከተንዛዛው የጉዞ ሰዓት የተነሳ ያለ አስጎብኝም ቢሆን ባቡሩን መቃኘት አዲስ ማለዳ ችላ ነበር። በዚህ ጊዜ ታዲያ አንድ በመንገደኞች ወደ ተሞላ ፉርጎ ደርሳ አንዲት በዕድሜ ገፋ ያሉ እናት ባቡር ውስጥ ጫት ሲሸጡ ለመታዘብ ችላለች። ለአፍታ ባቡር ውስጥ መሆኔን እስክዘነጋ ድረስ ገበያው የደራ ነበር። ትዕይንቱ እውነት ለመናገር ከአስገራሚነቱ ባሻገር ፈገግታን የሚያጭር ነገር ነበር።

እነሆ በማለዳ ኹለት ሰዓት የጀመረው ጉዞ ሞጆ፣ አዳማ፣ መኤሶ እያለ ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲል ድሬዳዋ ገባን። ድሬዳዋ ያለ መሰሰት ለሁሉም የምታካፍለው የፀሐይ ንዳድ የነገ ሰው ይበለን ብላ ወደ ማደሪያዋ ብትጠልቅም ከለብታ ከፍ ባለ ሙቅ አየር ነበር የተቀበለችን።

እስካሁን ለነበረን ቆይታ እና ስንጠይቃቸው ያለመሰልቸት ሲተባበሩን የነበሩትን የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ሠራተኞችን በየተራ ተሰናበትናቸው። የእኛ ጉዞ ድሬዳዋ ላይ ቢቋጭም እነሱ ግን ጅቡቲ ሳይደርሱ ጉዟቸው አይጠናቀቅም። እንደነሱ ግምት እኩለ ሌሊት ላይ ጅቡቲ ነጋዳ ባቡር ጣቢያ ይደርሳሉ። መልካም ጉዞ ተመኝተን የድሬዳዋን አየር ተነፈስን።

ቻይናዊያን የኪነ ሕንፃ ጥበባቸውን ያፈሰሱበት የድሬዳዋ ባቡር ጣቢያ ልብን የሚሰልብ ውበት አለው። ቻይናዊያን እጃችሁ ይባረክ የሚያስብል እጅግ አስደማሚ የኪነ ሕንፃ ውጤት ነው። የባቡር ጣቢያው እንዲያው ሥያሜው ድሬዳዋ ይባል እንጂ ከከተማዋ ራቅ ያለ ነው። ለዚህ ደግሞ ወደ ከተማዋ ለመድረስ በሕዝብ መጓጓዣ ለአንድ ሰው 50 ብር መጠየቁ አንዱ ማሳያ ነው።

ድሬዳዋ ገብተናል። “ድሬ አቦ ሐዘን ውጣ፤ ወለበል ጭንቀት” ቢሆንም ዘፈኗ፤ ከቅርብ ወዲህ ግን ሳንካዎቿ ተደራርበውባታል። ብሔር ተኮር ከሆነ ግጭት እስከ ችጉንጉኒያ ወረርሽን ልጆቿን ከጉያዋ ነጥቀዋታል። በተለይ ደግሞ አዲስ ማለዳ በድሬደዋ በተገኘችበት ቀን ሦስት ቀናትን አስቀድሞ ብሔር እና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን አስተናግዳ በትንሹም ቢሆን የአለመረጋጋት ዓውድማ ሆና ሰንብታ ነበር። ለዚህም ይመስላል የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ኀይል፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የከተማዋ የፖሊስ ኀይል በንቃትና በተጠንቀቅ የነዋሪውን እንቅስቃሴ የሚቃኙት።

ከወራት እና ከዓመታት በፊት ድሬዳዋን የሚያውቃት, አዲስ ማለዳ ድሬዳዋ በነበረችበት ወቅት ቢደርስ “ምነው ድሬ ፊቷን አጥቁራ እና ቆዝማ ተቀበለችኝ” ሳይል አይቀርም። በርካታ ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዞ ለሚያውቃት ድሬዳዋ እኮ የሞተችው የቀድሞው ኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር (ሼመንደፈር) ሥራ ያቆመ ጊዜ ነው” ሊል ይችላል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነውና ተረቱ ድሬዳዋ ቀን ስትሮጥ ውላ ማታም የማታርፈው ከተማ ከሰሞኑ ግን ሦሰት እና አራት ሰዓት ምሽት ካለፈ የህያዋን ማግኘት ጭንቅ ነው። ፍራቻ አሁንም ነዋሪዎቿ ላይ ይነበባል፣ አለመረጋጋት የዕለት ተዕለት ሥጋቶቿ ናቸው።

ለከተማዋ አዲስ ባንሆንም ከስፍራ ስፍራ ለመንቀሳቀስ የከተማዋን ዋነኛ የመጓጓዣ ዓይነት የሆኑትን ባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪዎችን (ባጃጅ) መጠቀም ግዴታችን ነበር። አገልግሎት የሚሰጡት አሽርካሪዎች ታዲያ ኹሉም ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰላም እየራቃት እንደመጣ እና ሌሊቱን ሙሉ ሰርተው ይገቡ የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን አምሽተው ሠሩ ከተባለ አራት ሰዓት ምሽት ድረስ እንደሚሠሩ እና ይህም ገቢያቸውን በመቀነስ ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደተዳረጉ አውግተውናል።

በእርግጥም ድሬዳዋን በምሽት ተመለከትናታል። የምሽት ቤቶች ከልብስ መሸጫዎች እኩል ነው የሚዘጉት ማለት ይቻላል። እንዲያው አልተዘጉም የተባሉ የምሽት ቤቶች እንኳን ከአስተናጋጆች ውጪ በቤቱ የሚዝናናም ሆነ የሚንቀሳቀስ ሰው ማግኘት በእርግጥ አስቸጋሪ ነው። ድሬዳዋ ታማለች ቢባል ማጋነን አይሆንም። የሰላም እጦት ኹሉንም የንግድ ዘርፍ ጎድቶታል።

ድሬዳዋ ንፅሕናን እና አረንጓዴነትን መርህ አድርጋ የምትንቀሳቀስ ውብ ከተማ ናት። ጎዳናዎቿ ፅዱ፤ የመንገድ ዳርቻዎቿ ደግሞ ልምላሜን ይዘምራሉ። ዝነኛው የፍቅረኞች መንገድ ከዚራ ስንቱን እልፍ ጥንድ አጋብቶ ለወግ ማረግ ቢያበቃም, ዛሬም ደከመኝ የሚል አይመስልም ከነ ሙሉ ግርማ ሞገሱ አዲስ ተተኪ ፍቅረኞች ላይ የፍቅር አየሩን እየረጨ “አይለያችሁ” የሚል ምርቃትን ያዘንባል። የድሬዳዋ ነዋሪ ትብብሩ ከመሐል አገር ለሔደ ሰው ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። አቅጣጫ ጠፍቷችሁ በአጠገብዎ የሚያልፍን አንድን ሰው መጠየቅ ብቻ በቂ ነው፤ ሥራቸውን ትተው ያሰቡት ቦታ ሳያደርስዎት አይመለሱም። ድሬ ከተዘመረላት፣ ከተፃፈላት፣ ከተነገረላት በላይ እጅግ ቀልብን የምትገዛ ከተማ ናት።

ሌላው በድሬዳዋ ከተማ ቀልብን የሚስበው ነገር፤ ኑሯቸውም እንደ ግልፅነታቸው ነው። “እንዴት ነው እዚህ ከተማ, የጓዳ ሕይወት የለም እንዴ?” ያስብላል። መንገድ ዳር ይቦካል፤ መንገድ ዳር ይጋገራል፤ መንገድ ዳር ይበላል። ጫት ከተቃመም በስውር አይደረግም። ነገር ኹሉ ከግልፅነትም ያልፋል። ድሬዎች ከዛፍና ለአረንጓዴያማነት ጋር ያላቸውን መስተጋብር ጠንካራ ምክንያት የሚገባዎት ቀትር ላይ ነው። “አሞራ እንኳን በአንድ ክንፉ እየበረረ, በሌላኛው ከፀሐይ ይከለላል” ይላሉ ጨዋታ አዋቂ ድሬዎች ስለ ድሬዳዋ ሙቀት ሲናገሩ።

አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በተመለከተችባቸው አካባቢዎች ሥራቸውን ገና በማለዳ አጠናቀው ቀትር ሰዓት ላይ ኹሉም ጥላ ሥር እረፍት ያደርጋል እግረ መንገድም የደንቡን ያደርጋል። ጫት ይቃማል፤ ቡና ይፈላል፤ ጨዋታው ይደራል።

በድሬዳዋ ታሪክ ከዐሥርት ዓመታት በፊት አንድ አሳዛኝ አሻራ ጥሎ ያለፈ ክስተት ነበር፤ የጎርፍ አደጋ። በዚህ ጎርፍ አደጋ ድሬዳዋ ልጆቿን ተነጥቃ መሪር ሃዘን ውስጥ ነበረች። ያኔ በዋናነት ጉዳት ያደረሰው የደቻቱ ወንዝ አሸዋውን ብቻ ታቅፎ ክረምት ያገናኘን በሚል ቀጠሮ የአሞራዎች መዋያ እና የተጣሉ የውሃ ኮዳዎችን የሚለቅሙ ታዳጊዎች መነኻሪያ ሆኗል።

አሳዛኙ ነገር ደግሞ ድሬዳዋ የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ብትሆንም ባለሀብቶች ከኪሳራ ጋር በተገናኘ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን ያፈሰሱበትን ሀብት ጥለው የወጡባት ከተማም ናት። ይህ ብቻ ሳይሆን ነዋሪዎቿ በበቂ የሕክምና አገልግሎት እጦት ቢሰቃዩም ከዓመታት በፊት በመቶ ሚሊዮኖች ወጪ የተገነባው የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል ግን ግንባታው ተጠናቆ አሁንም የሰው ያለህ እያለ ነው። እንደነዋሪዎች ገለጻ የተገነባው ሕንፃ በየዓመቱ የተወሰኑ ሴንቲ ሜትሮች ወደ ውስጥ ስለሚሰምጥ ከአገልግሎት ውጪ እንደሆነ ያስረዳሉ። ሳይወለድ ያረጀ ሆስፒታል ነው።

የድሬዳዋ ቆይታችንን ልናጠናቅቅ ነው። ከዛ በፊት ግን በተንጣለለው የድሬዳዋ ከተማ ልዩ ሥሙ መልካ በሚባል ቦታ የተገነባውን ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሳናነሳ አናልፍም። ኢንዱስትሪ ፓርኩ እንደ ሆስፒታሉ ሁሉ ምርቃቱ ሳይታወጅ አሁንም እባካችሁ ትኩረት አትንፈጉኝ በሚል ተማጽኖ አለሁ እያለ ይገኛል። በኢንዱስትሪ ፓርኩ በባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተገኝተው ይመርቁታል ተብሎ ቢጠበቅም ከምርቃት ሥነ ስርዓቱ ከቀናት በፊት በርካታ መሣሪያዎች እና ለሽብር ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦች በመያዛቸው ምርቃቱም ቀረ፤ የፓርኩም ሕልውና የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

ድሬዳዋን ልንሰናበታት ነው። ነዋሪዎቿን በመንፈስም ቢሆን መልካሙን ተመኘንላቸው። ዳግመኛ ስንመጣ በቀደመው ፍቅሯ እና በሞቀው እቅፏ እንድትቀበለን ከልባችን ተመኘን። የመልስ ጉዟችን በሰማዩ ጋሪ ነውና የደቂቃዎች ጉዞ አዲስ አበባ ያደርሰናል። ድሬን ግን በልባችን ተሸክመን አዲስ አበባ ድረስ ምናልባትም ቤታችን ድረስ ይዘናታል ያዘነችው፣ የደነገጠችው፣ ስጋት የተንሰራፋባት፣ ግን ደግሞ ሩህሩህነትን የማትነፍገውን ውብ ከተማ እንዲህ ስንል ተለየናት “አቦ ቸር ይግጠመን!”

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here