የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር በሚቀጥለው ዓመት የማኅበራዊ ጥበቃ ፈንድ እና የማኅበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚያስጸድቅ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ መላኩ ባዩ ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት፣ በ2015 የማኅበራዊ ጥበቃ ፈንድ እና የማኅበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ፓርላማ ጸድቆ ይተገበራል ብለዋል።
አዋጁን በ2014 ጸድቆ በሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት እና በተለያዩ ቦታዎች በተፈጠሩ የጸጥታ መደፍረሶች ሳቢያ ሊስተጓጎል እንደቻለ ቡድን መሪው ጠቁመዋል።
አዋጁ የሴፍትኔት ተጠቃሚ ያልሆኑ አካባቢዎች ከማዳረስ ጎን ለጎን በተለያዩ ምክንያቶች በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሉ በመሆናቸው እነዚህ ለመደገፍ የሚረዳ ነው። እንዲሁም ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ችግር ለመፍታት ከሚያደርገው እገዛ ባሻገር የደኅንነታቸውን ሁኔታ ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ቡድን መሪው ገልጸዋል።
ቡድን መሪው አክለውም፣ ወላጆቻቸውን ያጡ እና የሚደግፋቸው ቤተሰብ የሌላቸውን ሕፃናት እና ሴቶችንም ለመደገፍ እንዲሁም ማኅበራዊ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ አዋጁ የጎላ ሚና አለው ብለዋል።
በስፖንሰርሺፕ፣ በማኅበር ዐቀፍ ልማት እና እንክብካቤ፣ በማኅበራዊ ጥምረት አባላት፣ በአገር ውስጥ በሚገኙ ጉዲፈቻዎች እንዲሁም በሌሎችም ጭምር ድጋፉ እንደሚከናወን ተመላክቷል።
አዋጁ ጸድቆ በሚፈጸምበት ወቅት የአሠራር ሥርዓት እና የአፈጻጸም መመሪያ ከመዘርጋት በተጨማሪ፣ የተጠያቂነት የአሠራር ሂደትን ዘርግቶ ሚኒስቴሩ ክትትል የሚያከናውን ይሆናል ነው የተባለው።
አዋጁ ተተግብሮ ሥራ ላይ በሚውልባቸው ጊዜያት የተሻለ ለውጦች ያስመዘግባል ተብሎ እንደታመነበት ቡድን መሪው ጠቁመዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የሴቶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን እና በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነት እና አካታችነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የሕፃናትን መብት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ በ2014 በጀት ዓመት ጥረት አድርጓል ነው የተባለው።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በ2014 ሪፖርቱ፣ በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ምላሽ ከመስጠት አንጻር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እና በማስተባበር እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።
የቀጣይ በጀት ዓመት እቅዱም በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን እንዲሁም ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመደገፍ እና የማቋቋም ሥራ በማጠናከር አስቀጥላለሁ ብሏል።
በተጨማሪም፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማስተባበር ሕፃናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ማድረግ እና ችግሩን ከምንጩ መቅረፍ ትኩረት ከሚሰጣቸው ውስጥ በቀዳሚነት እንደሚጠቀስም ተጠቁሟል።
ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014



