በጦርነት የወደመ ቤታቸው ያልተጠገነላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ክረምቱ ፈታኝ ሆኖብናል አሉ

0
972

• በአንድ ወረዳ ብቻ ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች ቤታቸው ፈርሷል

በጦርነት ቀጠና ቆይተው ቤታቸው ያልተጠገነላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የ2014 የክረምት ወቅት ፈታኝ እንደሆነባቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

የክረምት ብርድ እያቆራመደን ነው ሲሉ የሚያማርሩት ነዋሪዎቹ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የሚገኙ ሲሆን፤ በታጣቂዎችና በጦርነት የፈረሰ ቤታቸው ባለመጠገኑ ሕጻናት እና አረጋዊያን ችግሩን መቋቋም አልቻሉም ነው የሚሉት።

ነዋሪዎቹ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ፀሐይ ክረምቱ ከገባ ጀምሮም ዝናብ እየተፈራረቀባቸው መሆኑን አብራርተው ችግራቸውን መንግሥት አውቆ ምላሽ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ በጦርነቱ ወቅት የከባድ መሣሪያ ድብደባ በደረሰባቸው ደብረ ዘቢጥ፤ አግሪት፤ ዳንዴበር፤ አርቢት እና ሌሎች ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የፈረሰ ቤታቸው እንዳልተጠገነ የአካባቢው ነዋሪ ወንድምነው አፈወርቅ ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ከ10 ወራት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከመጠለያ ውጪ ናቸው ተብሏል። አቅም ያላቸው ሰዎች ቤታቸው ቢፈርስም ጠጋግነው ተቀምጠዋል ያለው ወንድምነው፤ ለአብነትም በወረዳው የሚገኘው የመምህራን ቤት በጦርነቱ ወድሞ ነበር። ግን ሙሉ በሙሉ ቆርቆሮውን መቀየራቸውን አንስዋል።

አቅመ ደካሞች ግን መጠገን ስላልቻሉ የዝናብ ሲሳይ ሆነዋል ነው ያሉት። እድለኛ ናቸው የተባሉት በኬንዳ (ሸራ) ቢጠለሉም በርካታ ሰዎች ግን ጣራው በተሸነቋቆረ ቤት ነው የሚኖሩት ሲሉ ወንድምነው የዐይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ነዋሪው ቤታቸው ከፈረሰባቸው ሰዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰው አምና በጦርነቱ የደረሰው ውድመት እልባት ሳያገኝ አሁንም በድንበር አካባቢ ጦርነቱ ተቀስቅሷል ያሉ ሲሆን፤ የከባድ መሣሪያው ድምጽ መቄት ወረዳ ድረስ እንደሚሰማና በዚህም ነዋሪው የአምናውን ወቅት በምልሰት እያስታወሰ መሸበሩንም አልደበቁም።

ሙልዬ አለነ በመቄት ወረዳ የአግሪት ቀበሌ ነዋሪ እንደሆኑና ቤታቸው በጦርነቱ ወቅት በከባድ መሣሪያ ተመትቶ ቢፈርስም እንዳልተጠገነ ተናግረዋል። አቤቱታ አቅራቢው ‹‹ሚስቴም የከባድ መሣሪያ ፍንጣሪ መትቷት በብር እጥረት ምክንያት ሕክምና ባለማግኘት በሕመም እየተሰቃየች ነው›› ይላሉ።

ሙልዬ የቤቴ ጣራ በመፍረሱ ዝናብ ሲዘንብ ቤቴ ደጅ ነው የሚመስለው። ባለቤቴን እንኳ የማስታምምበት ቦታ አጥቻለሁ ሲሉ ያሉበትን ከባድ ኹኔታ ያብራሩ ሲሆን፤ የሚኖሩበትን የተሸነቋቆረ ቤትም በምስል ቀርጸው ለአዲስ ማለዳ ልከዋል።

በወረዳው ከ6 ሺሕ 200 በላይ የግለሰብ ቤቶች በጦርነት ምክንያት መውድማቸውን የመቄት ወረዳ አስተዳደር አሰፋ ይልማ ከዚህ በፊት መግለጻቸው ይታወሳል። ነዋሪዎቹም ወረዳው አቅም እንደሌለው ገልጾልናል ያሉ ሲሆን፤ አስተዳደሩ ያለውን ምላሽ ይበልጥ ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ማሳካት አልተቻለም። ነዋሪዎቹ ቤታችንን እንዳንጠግን በ2013/14 የምርት ወቅት በጦርነቱ ምክንያት አለማምረታችን ዋነኛው ችግር ነውም ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ በኦሮሚያ ክልል ኦነግ ሸኔ ሲያደርሰው በነበረው ሰፊ ጥቃት ከተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ተፈናቅለው አንገር ጉትን ከተማ ከነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ከወራት በፊት ወደ ሊሙ ወረዳ የተመለሱ ሰዎች ቢኖሩም ቤታቸው ግን ፈርሷል።

ሥማችን ባይጠቀስ ያሉት ተመላሾቹ እንደገለጹት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በታጣቂ ቡድኑ ቤታቸው ተቃጥሏል። ታዲያ ‹‹ለይስሙላ›› ወደ ቄያቸው ተመልሰዋል ቢባሉም፣ የሚገቡበት ቤት ግን እንደሌለ ተናግረዋል። የሊሙ ወረዳ አስተዳደር ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ ሲጠየቁ፣ ቆይተህ ደውል ባሉት መሠረት በድጋሚ ሲደወል ‹‹አላውቅም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ደበበ ዘውዴ ምላሽ ለመግኘት ጥራለች። ነገር ግን ‹‹ቆይተህ ደውል›› ብለው በድጋሚ ሲደወል ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት ሳይቻል ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here