ሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነት ለሰላም የተከፈለውንም ዋጋ መረዳት እና ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንደሚገባው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዎት የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ጀነራል ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ አሳሰቡ።
የአገር መከላከያ ሠራዊት የውጭ ግንኙነት ክፍል በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በኢትዮጵያ ላሉ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተወካዮችና የሰላምና ፀጥታ ኃላፊዎች እንዲሁም ለአገራት ወታደራዊ አመራሮች ማብራሪያ እየሰጠ ነው።
በማብራሪያውም ላይ የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ጀነራል ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ ማናቸውም አይነት የጥፋት ሙከራዎችን በአስተማማኝ መልኩ መቀልበስ እና መመከት የሚያስችለው ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የህወሓት የሽብር ቡድን የሰላም አማራጮችን በመግፋት የኢትዮጵያ ጦር ላይ ዳግም ጥቃት መክፈቱን ይህም የሽብር ቡድኑ ለሰላም ፍላጎት እንደሌለው የሚያሳይ እንደሆነ ሜጀር ጀነራል ተሾመ ለወታደራዊ አመራሮቹ አብራርተዋል።
ህወሓት የጀመረው ጦርነት በቴክኖሎጂ መረጋገጥ የሚችል እንደሆነ የሽብር ቡድኑ በወትወት ራማ ቢሶበር እና ዞብል እንዲሁም በአፋር ድንበር ጦርነት መክፈቱን ገልፀዋል።
መከላከያ ሠራዊት የአገሩን ዳር ድንበር የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት ያነሱት ሜጀር ጀነራል ተሾመ፤ መከላከያ እንደ አንድ ቁልፍ የብሄራዊ ማስፈፀምያ አቅም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በተለይም የህልውና ጥቅም የማስከበር ተቋማዊ ግዴታ አለበት ብለዋል።
ስለሆነም፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነት ለሰላም የተከፈለውንም ዋጋ መረዳት እና ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆም እንደሚገባው አብራርተዋል።
በሽብር ቡድኑ በሚፈበረኩ የተዛቡ መረጃዎችም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊሳሳት እንደማይገባው ጥቃቱ እንዴት እንደተጀመረ በቀላሉ መለየት እንደሚቻልም ማንሳታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
ሜጀር ጀነራል ተሾመ የኢትዮጵያ ሠራዊትም በሽብር ቡድኑ የተቃጣበትን ጥቃት በአግባቡ እየመከተ እንደሆነና ለዚህ ደግሞ የማንም ፍቃድ እንደማያስፈልገው ማስገንዘባቸውም ተገልጿል።



