የኹለት ሰልፎች ወግ!

0
1083

በለንደን ከተማ በነበራቸው ቆይታ የተመለከቱትን ሰልፍ በማንሳት የሚጀምሩት በፍቃዱ ኃይሉ፥ ሰልፉን በተመሳሳይ ሰሞን ጥቅምት 2 ቀን 2012 በአዲስ አበባ ይካሔዳል ተብሎ ሲጠበቅ አንድ ቀን በማይሞላ የሰዓት ልዩነት እንደማይደረግ ከተገለጸው ሰልፍ ጋር አነጻጽረው ያሳያሉ። በኹለቱ ሰልፎች መካከል በሰልፉ ጠሪዎች እንዲሁም በመንግሥትና በፖሊስ በኩል ያሉ የአካሔድ ልዩነቶችንም ጭምር ታዝበው እንደሚከተለው አቅርበዋል።

ባጋጣሚ ለንደን ከተማ በተገኘሁበት ባለፈው ሳምንት ‘ኤክስቲንክሽን ሪቤሊዬን’ የተባለ (‘ኤክስአር’ በሚል አጭር መጠሪያ የሚታወቅ) ለአካባቢ ደኅንነት እና ለብዝኀ ሕይወት ጥበቃ ተሟጋች ድርጅት የጠራው ሰልፍ እየተካሔደ ነበር። ሰልፉ ለኹለት ሳምንታት በተከታታይ የሚካሔድ ነበር። እኔ ባላስተውለውም፣ የለንደን ነዋሪዎች የሆኑት ወዳጆቼ “ፖሊስ መንገድ ላይ የበዛው በሰልፉ ምክንያት ነው” ብለውኛል። በተጨማሪም ሰልፉ በሚደረግበት ቦታ ተገኝቼ ለደቂቃዎች የመመልከት ዕድል አግኝቼ ነበር። ሰልፈኞቹ አንድ አደባባይ ላይ ተከማችተው መንገድ ዘግተዋል። የኤክስአር አርማ ያለበት ባንዲራ ያውለበልባሉ። የተለያዩ መፈክሮችን ይዘዋል። ድንኳኖችን ጥለዋል። የሙዚቃ ባንዶች አሉ። የለበሷቸው ልብሶች ላይ የተለያዩ መልዕክቶች ተጽፈዋል። በጥቅሉ ሲታይ ፌስቲቫል ይመስላል። ነገር ግን የተቃውሞ ሰልፍ ነበር።

ሰልፉን ፌስቲቫል ያስመሰለው መንግሥትን ሳያስጨንቀው ቀርቶ አይደለም። የሰልፍ አዘጋጆቹ ጭንቀትም ‘ፖሊስ እንዲህ ያደርገናል፤ ወይም መንግሥት እንዲህ ያደርገናል’ የሚል አልነበረም። እንዴት በርካታ ሰልፈኞች እዚህ ማንቀሳቀስ እንችላለን የሚለው ብቻ ነው። ሰልፈኞቹን ከብበው ቀጥ ብለው የቆሙ በርካታ ፖሊሶች አሉ። የከተማዋ ባተሌ መንገድ በዚህ ሰልፍ ምክንያት ተዘግቷል። አደባባዩ በተለምዶ ‘ነምበር ቴን’ የሚባለው ቦታ የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እና መኖሪያ ፊት ለፊት ያለውን መንገድ እንዲዘጋ አስገድዷል። ሰልፉ የሚካሔደው ደግሞ ለአንድ ቀን አልነበረም። ለኹለት ሳምንታት (ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 10) የሚዘልቅ ነበር። የሰልፈኞቹ ዓላማ መሐል ከተማውን ሥራ በማስፈታት መንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር እና ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ማግኘት ነው።

የኤክስአር ሰልፍ ሦስት የአካባቢ እና ብዝኀ-ሕይወት ጥበቃን የሚመለከቱ ጥያቄዎች አሉት። እነዚህን ጥያቄዎች ለማስመለስ የሰላማዊ ትግል መርሖዎችን አሟጦ እንደሚጠቀም በድረገጹ ላይ ተጠቅሷል። መንግሥት የአካባቢ አደጋ ጊዜ (environment emergency) እንዲያውጅ እስከማስገደድ ድረስ ዒላማ ይዘዋል። ዩጎቭ የሚባል የምርምር ድርጅት እንደሚለው፣ የኤክስአር የትግል ስልት ከ18-24 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ወጣቶች ከፍተኛ ድጋፍ አለው። ከዚህም በላይ ታዋቂ የጥበብ ሰዎች እና ባለሀብቶች ከበስተጀርባ ይደግፏቸዋል። ሰልፉን ሲያዘጋጁም በቅጡ ተሰናድተውበት እና ከሥራቸው ሳይቀር አስቀድመው ፈቃድ ጠይቀው በመውጣት ነው። ይሁንና በተለይ ሹፌሮች እና ሌሎችም መንገድ በመዝጋታቸው ይማረሩባቸዋል።

የአዲስ አበባው ሰልፍ
የአዲስ አበባው ሰልፍ በባልደራሱ ቡድን የተጠራ ነበር። የባልደራሱ ቡድን በዋነኝነት በሕገ መንግሥቱ የሰፈረውን “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም” በመቃወም፣ ብሎም “የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥቅም” ለማስከበር የተመሠረተ እና በእስክንድር ነጋ የሚመራ ንቅናቄ ነው። ንቅናቄው ጥቅምት 2 ቀን 2012 የተቃውሞ ሰልፍ ጠርቶ ነበር። ስለሰልፉ መጀመሪያ የተነገረው በንቅናቄው መሪ የትዊተር ገጽ ሲሆን፥ ስለ ሰልፉ ይዘት ምንነት የተገለጸው በጣም ከዘገየ በኋላ መስከረም 30/2012 ነበር። የሰልፉ ዓላማ ባልደራሱ የታሰሩበት አባላቱ እንዲፈቱ ያዘጋጀው ይሆናል ብዬ ጠርጥሬ ነበር፤ ሆኖም ከዚህ ውጪ በርካታ ጥያቄዎችን ያዘለ ነበር።

ለመዘርዘር ያክልም የዴሞክራሲና የፍትሕ ጥያቄዎች በገዢው ፓርቲ መጠለፋቸውን ለመቃወም፣ የገዢው ፓርቲን የሲቪል መብቶች አፈና ለመቃወም፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የታሰሩ የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱ ለመጠየቅ፣ ዓርማ የሌለበት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይውለበለብ የሚያግደው ሕግ እንዲሻር፣ ፅንፈኞች በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ፣ ለኑሮ ውድነት መንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው ለመጠየቅ እና “ልዩ ጥቅምን” ለመቃወም የተዘጋጀ ነው ተብሏል። በመግለጫው ላይም ሰልፈኞች ሰላማዊነትን የሙጥኝ እንዲሉ ጥብቅ ምክር ተላልፏል።

የሰልፉ አስተናጋጆች በተለያዩ አካባቢዎች (ፈረንሳይ፣ አራት ኪሎ፣ መርካቶ…) በመንቀሳቀስ “አዲስ አበባ ቤቴ፣ ማንነቴ” የሚል ጽሑፍ የታተመበት ቲሸርት ለብሰው እና ሰብሰብ ብለው ፎቶ በመነሳት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ፎቶ በመልቀቅ ሲቀሰቅሱ ከርመዋል። ቅስቀሳውን በሚያደርጉበት ወቅት በተለይ በመርካቶ ፖሊስ ለተወሰነ ሰዓት አደናቅፏቸው ነበር። በተለይም ደግሞ የኋላ ኋላ ፖሊስ ስለሰልፉ አላውቅም ብሎ ያወጣው መግለጫ የሰልፉ መካሔድ ጉዳይ ላይ ጥላ ያጠላ ጉዳይ ነበር። ከዚህ ውጪ ባልደራሱ በበርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሚደገፍ ቢገመትም በቂ ጥናት ስላልተደረገ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። ታዋቂ የጥበብ ሰዎች እና ሌሎችም ግን ደግፈውት ንቅናቄውን ሲያራምዱ ወይም ሲቀላቀሉ አይታዩም። በሌላ በኩል ከኦሮሞ ብሔርተኞች ግን ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ሰንብቷል።

ተቃውሞው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚበረታ ቢሆንም፥ የባልደራሱን ሰልፍ የሚቀላቀሉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሳይሆኑ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ናቸው ተብሎ በመወራቱ ምክንያት የኦሮሚያ ወጣቶች እና አልፎ አልፎ የታዩት ምሥሎች እንደሚያስረዱት የክልሉ ፖሊሶችም ጭምር ከአማራ ወደ ኦሮሚያ፣ ከኦሮሚያ ወደ አዲስ አበባ መተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት ሰልፉን ለማደናቀፍ በሚል በርካታ መንገደኞችን ሲያጉላሉ ከርመዋል።

የሰልፎቹ መጨናገፍ
የኤክስአር ሰልፈኞች መንገድ በዘጉ ልክ በሳምንታቸው ሰኞ ፖሊስ ሰልፈኞቹ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት በኋላ እንዳይቀጥሉ፣ ከትራፋልጋር አደባባይ እንዳይርቁ እና ዌስትሚኒስትር ያለው ፓርላመንት ጋር እንዳይደርሱ እንዲሁም ሌሎችንም እገዳዎች ጥሎባቸዋል። የሜትሮፖሊታን ፖሊስ በአደባባይ እንዲህ ዓይነት ኹነት ለሚያዘጋጁ በድረገጹ ላይ ያስቀመጠው መመሪያ ላይ “እንዲህ ዓይነት ኹነቶችን የማዘጋጀት እና የሰልፎች ነጻነት ጠቃሚ ቢሆንም፣ የሌሎች የተለመደ ዕለታዊ ኑሮ እና ሥራ የመሥራት ነጻነት መስተጓጎልም የለበትም” የሚል ምክር ቢጤ አለው።

ይህ መመሪያ የአደባባይ ኹነት አስተባባሪዎች ከፖሊስ ጋር በትብብር የሚሠሩበትን መንገድ ሳይቀር ይዘረዝራል። ዞሮ ዞሮ በዚህ እና ቀድሞ በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት ይህንን ተላልፈዋል በሚል የጠረጠራቸውን 1400 በላይ ሰዎችን አሥሯል። የኋላ ኋላ ቀሪዎቹ ተለቅቀው “ሕዝባዊ አገልግሎት በማስተጓጎል” እና በመሳሰሉት ክስ መሥርቼባቸዋለሁ ያላቸውን 96 ሰዎች ሥም ዝርዝር በድረገጹ አትሟል።

ፖሊስ ሰልፎቹን ሊበትን ሲመጣ ራሳቸውን ከድንኳናቸው ጋር ያሰሩ፣ ልብሳቸውን መሬት ላይ በማጣበቂያ የለጠፉ እና የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ለመነሳት ያስቸገሩ ነበሩበት። ሆኖም አንዳቸውም – ፖሊሶቹም ይሁን ሰልፈኞቹ – ቅንጣት ኀይል አልተጠቀሙም። በእርግጥ ፖሊሶቹ አንነሳም ያሉትን ሰልፈኞች ለአራት እና ከዚያም በላይ በመሆን ተሸክመው ይወስዷቸው ነበር።

ይህ ከመሆኑ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ፣ የአዲስ አበባው ሰልፍ ይካሔዳል ተብሎ በሚታሰብበት ቀን ዋዜማ – ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2012 – ፖሊስ የሰልፉ አደራጆች እየተነሱ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የለጠፏቸውን ፎቶዎች እየተመለከቱ እያደኑ ማሰራቸውን ተያያዙት፤ በለንደኑ ሰልፍ አስተባባሪዎች የፖሊስ ተባባሪ ተደርገው ነው የሚቆጠሩት። ምክንያቱም የፖሊስ ብቸኛ ጭንቀት መሆን ያለበት የሰልፈኞችም ይሁን ያልተሰለፉ ሰዎች ደኅንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ማድረግ ብቻ ነው።

የአዲስ አበባው ሰልፍ አስተባባሪዎች መታሰር ከተማዋን በፍርሐት እንድትናጥ አድርጓታል። በዚህም አዘጋጆቹ ባለቀ ሰዓት ሰልፉን ለመሰረዝ ተገድደዋል። የዛኑ ዕለት አመሻሹ ላይ እና በማግስቱ የታሰሩት ሰዎች በሙሉ መለቀቃቸውን አዘጋጆቹ ተናግረዋል። ለምን እንደታሰሩ እና ሰልፉን ማስተጓጎል እንደተፈለገ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም። እስክንድር ነጋ “ለራሳችሁ ደኅንነት አስበን ነው” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ለሚዲያ ተናግረዋል። ሆኖም ታስረውባቸው የነበሩትን ሰዎች ቁጥር እነሱም አላወቁትም፤ ፖሊስም ይፋ አላደረገም። ይህንን እስር ያዘዘው ማን እንደሆነም የሚታወቅ ነገር የለም።

የእኛ እና የነሱ ነገር!
የለንደን ሰልፈኞች፣ አዘጋጆች እና ደጋፊዎች የሚዲያ ክርክሮችን እና ውይይቶችን በዚህ ዙሪያ አጧጡፈው ቀጥለዋል። ለምሳሌ ሚዲያዎች ‘የኤክስአር ደጋፊዎች ግብዞች ናቸው፤ ራሳቸው አካባቢ በካይ በሆነ የኑሮ ዘዬ እየመሩ መንግሥት ላይ ይጮሃሉ’ የሚል ወቀሳ አቅርበውባቸው ነበር፤ ለዚህ ከመቶ በላይ ታዋቂ ሰዎች በፈረሙበት ግልጽ ደብዳቤ ‘አዎ፣ ግብዝ ነን፤ ለዚያም ነው ስር የሰደደ እርምጃ በመንግሥት መወሰድ አለበት የምንለው’ ብለው መልስ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል የአዲስ አበባው ሰልፍ መደናቀፉ በራሱ የመንግሥት አፋኝነት አልቀረም የሚል ውይይት ከማስነሳቱ በስተቀር በሰልፉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ቀጣይ ውይይት አላስከተለም።

የለንደኑ ሰልፍ በቂ ዝግጅት የተደረገበት፣ የሰልፉ አጀንዳ ግልጽ እና ቅልብጭ ያለ፣ የየዕለቱ ተግባርም በይፋ የተገለጸ እና ከሰኞ እስከ ሰኞ የሚታወቅ፣ ፖሊስም የሚፈቅደው እና የሚከለክለው የሚታወቅበት ነበር። የአዲስ አበባው ሰልፍ እጅግ በጣም ሰፊ አጀንዳ የያዘ እና ለትኩረት እና ለሚዲያ አጀንዳ የማይመች፣ አጀንዳዎቹ አላግባብ ለረዥም ጊዜ በምሥጢር የተያዙበት፣ የፖሊስ እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት በጊዜ መልስ ያልሰጡበት፣ ጊዜው ሲደርስም በኃይል ያደናቀፉበት እና ግልጽ ማስተባበያ ያልተሰጠበት ነበር።

የለንደኑን ሰልፍ ድባብ አይቼ ስለ ዴሞክራሲ ቀንቻለሁ፤ አዲስ አበባ ስገባ ደግሞ የተቀበለኝ አዘጋጆቹ እየተሳደዱ እየታሰሩ ነው የሚል አሳዛኝ ዜና ነበር። ካለፈ በኋላ መንግሥት ለሰላማዊ ሰልፍ ጥበቃ በማድረግ ለመፍቀድ የማይደፍርበት፣ ሰልፈኞችም መንግሥት የሚከለክለው መሆኑን ብቻ ለማሳየት በቅጡ ሳይሰናዱ የሚያዘጋጁት የሰልፍ ጥሪ ያስተናገድን እየመሰለኝ ነው። ዴሞክራሲ በተለይ በተለይ ወደደም ጠላም የመንግሥትን ፈቃጅነት፣ አክባሪነት እና ጠባቂነት፣ የተሟጋቾቿን ደግሞ ሐቀኛ ጥረት ትጠይቃለች። እስከዚያው ከተደናቀፈ በኋላም ቢሆን ሕዝባዊ ርዕሰ ጉዳይ የሚሆነውን የለንደኑን ዓይነት ሰልፍ እንናፍቃለን።

በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here