ሳይወለድ የሞተው ኦሮማራ!!

0
800

ይነገር ጌታቸው የኦሮማራ (የኦሮሞና የአማራ ል ፖለቲካ ልኂቃን ጥምረት) ትርክትን አንጋፋው ፖለቲከኛ አንዳርጋቸው ጽጌ የ1966ቱን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ከተነተኑበት መጽሐፍ በመዋስ ሳይወለድ የሞተ ሲሉ ይገልጹታል። ኢትዮጵያ የታሪክ ተቃርኖዋን በሚያዛልቅ ኹኔታ ለመፍታት የምትችለው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገቷ የብሔር ጥያቄን በመደብ ጥያቄ መቀየር ሲችል ብቻ ነው በማለት መፍትሔ ያሉትንም ሐሳብ ጠቁመዋል።

አንድዳርጋቸው ፅጌ “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር” በተሰኘ መጽሐፉ የ1966ቱን አብዮት ሳይወለድ የሞተ ነው ይለዋል። ሐሳቡ ነባሩን እውነት የሚንድ በመሆኑ ሊያከራክር ይችላል። የንጉሱ በወታደራዊ መንግሥት መተካትስ ምን ሊባል ነው ያስብላል። ሥር ነቀል ለውጥ የተደረገበትን የፖለቲካ ሽግግር አብዮት ካልለነው ምን ብለን ልንጠራውስ እንችላለንስ የሚል ሙግት ያስነሳል። የአንጋፋው ፖለተከኛ ምላሽ አጭር ነው። በ1966 የተካሔደው የፖለቲካ ለውጥ ዝምተኛ መፈንቅለ መንግሥት እንጅ አብዮት አይደለም። አንዳርጋቸው በርግጥ ለአብዮት የሚሆን ምቹ አጋጣሚ ተፈጠሮ ነበር ይላል። ይሁን እንጅ ወታደራዊ ኀይሉ ሁሉን ዐቀፍ የሆነውን የአብዮቱን ሞተር አጥፍቶ ለራሱ ብቻ የአብዮታዊነትን ሥያሜ አጎናፀፈ፤ በዚህ ጎዳናም ባልተወለደ አብዮት አገርን ለ17 ያህል ዓመታት አስተዳደረ። ከሥልጣኑ ሲሰናበትም ያልተወለደውን አብዮት ሞተ ብሎ ለፈፈ።

ለእኔ የኦሮማራ ትርክት ከ66ቱ አብዮት ጋር እጅጉን የተመሳሰለ ነው። ከዓመት በፊት የነበረው አገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ከሞላ ጎደል የኦሮሞና የአማራ ፖለቲካ ልኂቃንን የትርክት ልዩነት የማጥበብ ድባብን የፈጠረ ነበር። የዚህ ድባብ መፈጠር ግን እንደ አብዮቱ ሁሉ ኦሮማራን እውን ለማድረግ በቂ አልሆነም። በዚህ የተነሳም ኦሮማራን ለመፍጠር ተሞከረ እንጅ ከግብ አልደረሰም። ብዙ ተንታኞች የሕወሓት የበላይነት የተገታው በኦሮማራ ጥምረት ነው የሚል አስተያየት ሲሰነዝሩ እሰማለሁ። ጥቂት የማይባለው የፖለቲካ ልኂቃን ደግሞ የሕወሓት ከፋፍለህ ግዛ ከኢትዮጵያ ምድር ከተነቀለ ኦሮማራ የሚለው ሥያሜ ቢኖርም ባኖርም የኹለቱ ክልል የፖለቲካ ልኂቃን ልዩነት በራሱ ጊዜ ከስሟል የሚል አስተያየት ሲሰነዝር አደምጣለሁ። ለእኔ ኹለቱም አመክኒዮዎች ውሃ የሚያነሱ አይደሉም። አብዮቱን እዚህ ቦታ ላይ እናምጣውና ነገሩን በውሉ ለማየት እንሞክር። ለሺሕ ዘመናት የዘለቀው ንጉሣዊው አስተዳደር በየዘመናቱ ጠንካራ ተቃውሞ ሲደርግ በት ቢቆይም ቀዳማዊ ኀይለስላሴን ከዙፋናቸው የወረዱት ግን በደርግ እጅ ነበር።

ይህ እውነት ንጉሣዊውን ስርዓት የጣለው ደርግ ነው ለማለት በቂ አይደለም። እንደውም ደርግ ሕዝባዊ መሰረቱ የተሸረሸረውን አስተዳደር በቀላሉ ገፋ ሲያደርገው ወደቀለት እንጅ እዚህ ግባ የሚባል ትግል ሚናን አልተወጣም። የ66ቱ ለውጥ ዋና ባለቤት ተማሪው በጥቅሉም ሕዝቡ ነበር። የታሪክ ኦዲት ውስጥ ከገባን ደርግ ንጉሡን በመጣል በኩል የነበረው ሚና ትንሽ መሆኑ አያከራክርም። ነገር ግን ለውጡ ሳይተሳብ በሠራዊቱ ተወካዮች እጅ ወደቀ። እነሱም ዋናው የለውጡ መሪ ደርግ ነው ማለት ጀመሩ። በጊዜ ሒደትም እውነተኛውን አብዮታዊ ኀይል አስወግደው እራሳቸውን ሃቀኛ አብዮታዊ አደረጉ። የኦሮማራ መሪዎች አስተዋጽዖ በንጉሡ መውረድ ውስጥ በመጨረሸ ከመጣው ደርግ ጋር የሚመሳሰል ነው ።

ኢትዮጵያዊያን ባለፉት 27 ዓመታት ፍታሐዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን እንዲሆን በየጊዜው ከፍ ያለ መስዕዋትነት ከፍለዋል። ፕሮፌሰር አስራትም ሆነ ኮለኔል ገመቹ ከኦሮማራ ጥምረት በፊት ሕወሓት መራሹን አስተዳደር ተቃውመው እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል፤ ወደ ማረሚያም ወርደዋል። የሕይወት መስዕዋትነትም እስከመክፈል ደርሰዋል። ሜጀር ጄነራል ከማል ገልቹም ሆኑ ኮለኔል አለበልም በርሃ የወረዱትም ሆነ የታገሉት ኦሮማራ ስለነበረ አይደለም። የኦሮማራ ትርክት ሳይፈጠር የኦሮሞ ልጆች ጊንጪ ላይ መንግሥትን በቃን ብለዋል። ለማና ገዱ ሳይጣመሩ አማራ ክልል ውስጥ ያሉ ወረዳዎች በራሳቸው የጎበዝ አለቃ እስከመተዳደር ደርሰዋል። ትኩረቴን ኹለቱ ሕዝቦች ላይ አደረኩ እንጅ በሌሎች አከባቢዎችም ተመሳሳይ ትግሎች ሲካሔዱ መቆየታቸው የማይካድ ሃቅ ነው። ሲዳማዎች መንግሥታዊ አፈናውን ተቃውመው ሎቄ ላይ ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተዋል። ጋምቤላዎች ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ለቀናት ተፋጠው በርካታ ልጆቻቸውን ገብረዋል። ጉራጌም ጉምዙም ሀደሬውም መንዜውም በተለያዩ ወቅቶች የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በቀላሉ የማይታይ አስተዋጽዖን አድርጓል። እንዲህ ያለው በየጊዜው የተስተዋለው ሕዝባዊ እምቢተኝነትም እንደ ምስጥ ስርዓቱን ከሥሩ በመቦርቦር በቀላሉ ቢገፉት ወደሚወድቀበት ደራጃ አድርሶታል። እኔ እስከሚገባኝ ኦሮማራ የሚል ሥም የተሰጠው የፖለቲካ ታክቲክ ሕዝባዊ መሰረቱ በዘመናት ሒደት ተሸርሽሮ ይደገፍበት ያጣውን ስርዓት የጣለ ሰበብ እንጅ መሰረታዊ ምክንያት አይደለም።

በርግጥ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ 70 በመቶውን የአገሪቱ ነዋሪ የሚሸፍን በመሆኑ ጥምረታቸው ቀላል የሚባል አይደለም። ይሁን እንጅ ሕዝባዊ መሰረቱን ያጣ አስተዳደር አይደለም በኦሮማራ ሥም የረባ ድጋፍ ባልነበረው ደርግም ሲውድቅ ተመልክተናል። በቁጥር አነስተኛ ሕዝብን የሚወክለው ሕወሓትም ከሕዝብ የተነጠለውን በአፍሪካ ቀዳሚ የመከላከያ ኀይል ያለውን የጎድ መንግሥቱ አስተዳደር ጥሎታል። ከዚህ አንጻር ኦሮማራ ቢኖርም ባይኖርም በ2010 የነበረው አገራዊ ሁኔታ ለውጡ በውድም በግድም እንዲመጣ የሚያደርግ ከባቢን የፈጠረ መሆኑ ላይ መግባባት ያስፈልጋል።

እኔ እስከሚገባኝ ከመጋቢቱ ለውጥ ቀደም ብለው በነበሩት ወራት አማራ ክልል ውስጥ የነበረው የመንግሥት መዋቅር ከሞላ ጎደል ተበጣጥሷል። በኦሮሚያም ከ11 ዞኖች በላይ ከመንግሥት ቀጥጥር ወጥተዋል። ይህ አጋጣሚ በአገሪቱ ለውጥ ካልመጣ በስተቀር የቀደመውን ስርዓት ማስቀጠል እንደማይቻል በአግባቡ የሚያረጋግጥ ነበር።

የአማራም ሆነ የኦሮሚያ ሕዝብ ኦሮማራ የሚሉት የፖለቲከኞች ታክቲካዊ ጥምረት እውን ሆነም አልሆነም ዳግም ሕወሓት መራሽ ነው በሚባለው አስተዳደር ውስጥ የመቀጠል ዕድል አልበረውም። ጣናን የተንተራሰው ፖለቲካ ከኮለኔል ደመቀ እስር በኋላ የሚሰማው ማጣት ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊ ሥራን እንኳን ለማከናወን የተቸገረ ነበረ። በኦሮሚያም ከላይ እንደጠቀስኩት አገራዊ ቀውሱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ካልተቀየረ በስተቅር እንዲሁ የሚቀጥልበት መስርት አልነበረውም። ከዚህ አንጻር ኦሮማራ ደርግ በአብዮቱ ውስጥ የነበረውን ሚና ተጫወተ እንጅ ሌላ ፋይዳ የለውም። ይህ አገላለጽ ድፍረት እንዳይመስል አሮማራ ከኦሮሞ እና አማራ ሕዝብ የወጡ ፖለቲከኞች የፈጠሩት ታክቲካዊ ጥምረት እንጅ የሕዝብ ጥምረት አለመሆኑን በውሉ መረዳት ያስፈልጋል ።

ለዚህ ሙግታችን የዛሬው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ በቂ ማስረጃን ስለሚያውስ ፊታችንን ወደዛ እናዙር። ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ይገባኛል አተካራ ውስጥ የገቡት የአማራና የኦሮሚያ ልኂቃን በጊዜ ሒደት የለየለት አምባጓሮ ውስጥ ተዘፍቋዋል። ባሳለፍነው ሳምንትም የአማራ ተወላጆች ወደ ኦሮሚያ እንዳይገቡ እስከመከልከል ደርሷል። የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይንም በጉልበት ወደ አንድ ክልል ለማጠቃለል ተሞክሯል። ይህ አጋጣሚ በብዙዎች አገላለጽ የኦሮማራ መሞትን የሚያረጋግጥ ነው።

እኔ ግን እጠይቃለሁ። አንዳርጋቸው ፅጌ አብዮቱን ለመፍጠር የሚረዳ ድባብ ተፈጠረ እንጅ አብዮት አልነበረም እንዲል እኔም ኦሮማራን ለመፍጠር የሚረዳ ከባቢ ተፈጠረ እንጅ ኦሮማራ እውን እልሆነም ነበር እላለሁ ። ይህን ሙግት በሀሊዮም በገቢርም ለማየት እንሞክር።

ታዋቂው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ አጥኝ ዶናልድ ሌቪን ኢትዮጵያ በአማራ አምብሮና በኦሮሚያ ተቃርኖ የቆመች አገር ናት ይላሉ። የፕሮፌሰሩ አገላለጽ ቢያስደንግጥም የፖለቲካ ታሪካችንን ገመና ግን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ለምን የሚል ጥያቄ የሚጠበቅ ስለሆነ ወደ እሱ ልለፍ። የመቶ ዓመት ታሪካችን ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ትግል የባላባትና የጭስኛ ብቻ ሳይሆን የእኔ ልምራ ግብግብም የተጫነው ነበር። ጆን ማርካኪስ በመቶ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ያልተመለሰለት ወሳኝ የፖለቲካ ጥያቄ ኢትዮጵያን ለመምራት አለመቻሉ ነው የሚለውም ከዚህ በመነሳት ይመስላል።

ይህ አገላለጽ ድፍረት እንዳይመስል ከዚህ ዘመን ጋር እናሰናስለው። ጀዋር መሐመድ ከወራት በፊት ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ አሁን ያለው ለውጥ ከቀደሙት የሚለየው ኦሮሞን ከተመሪነት ወደ መሪነት ማሽጋገሩ ነው ብሏል።በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችም በምዕተ ዓመት ትግል እጃቸው የገባውን ሥልጣን እርስበርስ በመተጋገል እንዳያጡት ሊጠነቀቁ እንደሚገባ አሳስቧል። የታሪክ ምልከታችንን ከላይ እያነሳነው ካለው የኦሮማራ ትርክት ጋር ለማስተሳስር እንሞክር። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ በአማራና ትግሬ አገር ማስተዳደር እና በአሮሞ ልቀቁልኝ የሚል ግብግብ የተፈጠረው ነው ካልን ኦሮማራ ይህን ልዩነት አስታርቄያለሁ ወይ የሚለውን ሊመለስ ይገበዋል። በወቅቱ አዲስ አበባና ደብረ ብርሃን ላይ የተካሔዱ የምሁራን ውይይቶች “የኹለቱ ሕዝቦች የፖለቲካ ልኂቃን ልዩነት ከምን መጣ? እንዴትስ ይፈታል?” የሚለውን በአግባቡ ለመመለስ ከመጣር ይልቅ የሁሉም ነገር መነሻ ያለፈው ኹለት ዐሥርታት አስተዳደራዊ ችግር ነው ብሎ ደምድሟል። ንጉሱ ጥላሁንና አዲሱ አረጋን የመሳሰሉ የድርጅት አመራሮችም ኦሮማራ የሚላውን ፖለቲካው እንቅስቃሴ መሬት ለማውረድ ከመጣር ይልቅ ትናንትም አንድ ነበርን ወደ ፊትም የሚለየን የለም የሚል መፈክርን አስምተዋል፤ ይህ ግን ፍፁም ስህተት ነበር። የኢትዮጵያ ፖለቲካ አይደለም በብሔር ደረጃ በጎሳ ሳይቀር ጎጠኝነት የሚስተዋልበት መሆኑን ታሪክ በአግባቡ ይነግረናል ።

ተክለሐዋርያት ተክለማሪያም የሕይወት ታሪካቸውን ሲጽፉ እቴጌ ጣይቱን እንዲህ ይገልጿቸዋል። “ትልቅ ሴት ኑረዋል። እውነት ነው ለወገናቸው አድሊ ሁነው፤ የሽዋን ሰው ከከብት ይቆጥሩት ነበር። የሽዋን ሀብት ለየጁና በጌምድር ማበለጠጊጠያ አደረጉት። እጅግ ችግረኛ የነበሩት ተወላጆቻቸው በሽዋ ቤተ መንግሥት ጌቶች ሆኑበት።”
ከመቶ ዓመት በፊት የነበሩት አንጋፋ ፖለቲከኛ አስተያየት ፖለቲካችን ከብሔር አንሶ በጎጥ ከተከፈለ ምዕተ ዓመት እንደጠቆጠረ ያረጋግጣል። የዛሬ ዘመን ፖለቲከኞችም ሆነ የኦሮማራ መሪዎች ግን ይህን አያውቁትም አልያም መስማት አይፈልጉም። በመሆኑም ትናንት አንድ ነበርን፤ ነገም የሚለየን የለም የሚል መፈክርን ብቻ ይዘው መጓዝን መርጠዋል። የኦሮማራ የክሽፈት መነሻ እውነተኛ ችግሮችን ያለየ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ አረዳዱ ዝንፈት ያለበት ከመሆኑ ይመነጫል። ይህ እንደ ክልል ሲታይ በኹለቱ ክልል ፖለቲካ ልኂቃን ላይ ጎልቶ ይስተዋል እንጅ እንደ አገርም ደጋግመውን ተፈትነን የወደቅነበት ጉዳይ ነው። በየዘመናቱ የመጡ መሪዎቻችን ግን እንዲህ ያለው መራራ እውነት ጋር መጋፈጥ አይፈልጉም። ኢትዮጵያ ትናንትም ሆነ ነገ አንድ ናት ከሚለው ላም አለኝ በሰማይ ትርክት አላፈገፈጉም።

ይህ ደግሞ ኦሮማራን ሳይወለድ እንደቀበረው ሁሉ የኢትዮጵያን ህልውናም እየተገዳደረ ነው። የሚገርመው ነገር ግን ዛሬም ከዚህ ሀቅ ጋር ለመፋለም አልደፈርንም። መንግሥታዊና አገራዊ እሳቤያችንን ዳግም መበየን አስፈላጊ መሆኑን ለመነጋገር እንኳን አልተዘጋጀንም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አዲስ ወግ የሚል የውይይት መርሃ ግብርን በጽሕፈት ቤታቸው በማዘጋጀት የምሁራንን ሐሳብ ለመስማት ሞክረዋል። ይሁን እንጅ የእኛ አገር ምሁራን የተረኝነት ሰለፈኛ እንጅ የሐሰብ ተሟጋች ባለመሆናቸው የፈየዱት ነገረ እዚህ ግባ የሚባል የሆነ አይመስልም። በዚህ የተነሳም ሐሳብ ያጠራቸው የአገራችን የፖለቲካ መሪዎች ብሔራዊ የታሪክ መዛነፍን አንግበው አገራዊ ውሕደትን ይሰብካሉ። በዜጎች መካከል ያለውን የኢትዮጵያዊነት አረዳድ ሳያጠቡ የአገራችን ሕልውና ለድርድ አይቀርብም ይላሉ። ስለችግሩ በድፈርት የማያወራ ሕዝብና መንግሥት እንዴት የብሔር ፖለቲካ ነጋዴዎች በበዙበት ሁኔታ ህልውና ሊኖረው ይችላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከወራት በፊት የኢትዮጵያ አምላክ እያለ ይህ ሕዝብ አይበተንም አሉ። ወዳጃቸውና አማካሪያቸው ዲያቆን ዳንኤል ክበረትም ባሳለፍነው እሁድ ከኢሳት ጋር በነበረው ቆይታ “ኢትዮጵያ ጥሎ የማይጥላት አምላክ አላት” ሲል ሰማሁት። ሃይማኖታዊ ሙግቱን ወደ ጎን ትቼ ፖለቲካዊ ትርጉምን ከካርል ማርክስ አስተምሮ በመዋስ እንዲህ ልግለፀው። ማርክስ ድንችን ለአንድ ቀንም ይሁን ለዓመታት በኩንታል አስረህ ብታኖረው ተፈጭቶ የተዋሐደ እስካልሆነ ድረስ የፈታሃው ጊዜ መበታተኑ አይቀርም ይላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዘነጉት መሰረታዊ እውነት ይህ ይመስለኛል። መደመር እንደ ኩንታሉ በውድም በግድም ሁሉንም አንድ ላይ ሊይዝ ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጅ ቀልጠው ወደ አንድነት እስካልመጡ ድረስ ችግር ሲገጥማቸው በየፊናቸው መንከባለላቸው መበታተናቸው አይቀርም።

ማርክስ በድንች የሚወክለውን አገራዊ አንድነት ለመፍጠር ካፒታሊዝም ወሳኛ መሆኑን ያነሳል። በፋብሪካ ውስጥ ያለፉ ድንቾች የመጀመሪያ ሕልውናቸውን ጥለው አንዱን ከአንዱ ለመለየት እንደሚያስቸግሩ ሁሉ የኢንዱስትሪዎች መብዛትም ማኅበረሰቡን ከብሔር ጥያቄ ወደ መደብ ጥያቄ ያሽጋግራል ።

ኢትዮጵያ የታሪክ ተቃርኖዋን በሚያዛልቅ ሁኔታ መፍታት የምትችለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ የብሔር ጥያቄን በመደብ ጥያቄ መቀየር ሲችል ብቻ ነው። እስከዛ ምን ይሁን የሚል ጥያቄ ከተነሳ ግን የአገረ መንግሥትና የብሔር ግንባታውን ዳግም ብያኔ መስጠት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በእኔ ግምት ኦሮማራ እንደ 66ቱ አብዮት ድባቡን ብቻ ፈጥሮ እንደ ጠዋት ጤዛ ድንገት የጠፋውም ይህን ባለማድረጉ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here