ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሲሳይ ተስፋዬ የተባሉ ግለሰብ የውጭ አገር ዜጋ ገንዘብ ሆነና በስህተት ወደ አካውንታቸው የገባን 501 ሺሕ 840 ብር ለባለቤቱ በታማኝነት መመለሳቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።
ነገሩ እንዲህ ነው ሲሳይ ተስፋዬ በስልካቸው አንድ መልእክት ይደርሳቸዋል፡፡ በወቅቱ ሀሰተኛ መልዕክት ስለመሰላቸው ብዙም ትኩረት አልሰጡትም፡፡ በጡረታ ላይ የሚገኙት ሲሳይ ዘመድም ወዳጅም ይህን ያደርጋል ብለው የሚጠብቁት ነገር ስላልሆነ በሂሳባቸው 501 ሺሕ 840 ብር መግባቱን የሚናገረውን መልዕክት ሀሰተኛ ነው ብለው አምነዋል፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ ሂሳባቸውን በኤ.ቲ.ኤም ሲያዩ ግን እውነትም ገንዘቡ ወደ ሂሳባቸው ገብቷል፡፡ ግለሰቡ በጡረታ ዘመኔ ያገኘሁት ሲሳይ ነው ብለው አልተደሰቱም፡፡ ይልቁንስ በስህተት የገባ ገንዘብ መሆኑ ስለገባቸው የገንዘቡን ባለቤት ማፈላለግ ጀመሩ፡፡
ወደ ባንክ በመሄድ የሂሳብ ዝርዝር አስወጥተው ገንዘቡን ወደ ሂሳባቸው ያስገባውን ሰው ሥም አገኙ፣ የውጭ አገር ዜጋ ነው፡፡ ስልኩን ከባንኩ ተቀብለው ደወሉለት፡፡ እውነትም በስህተት የገባ ገንዘብ መሆኑን አረጋገጡ፡፡ አስፈላጊውን ማጣራት አድርገው የገንዘቡ ትክክለኛ ባለቤት መሆኑን ሲያረጋግጡም ገንዘቡን በታማኝነት መለሱ፡፡
ገንዘቡ ህይወታቸውን ሊለውጥ ቢችልም ህሊናቸውን ግን ሊለውጥ እንደማይችል የተናገሩት ሲሳይ፣ ገንዘቡን ሲመልሱ የተሰማቸው ደስታ ወደር የለውም፡፡ የሰው ገንዘብ በፍፁም እንደማይፈልጉ እምነታቸው አድርገው የኖሩት ሲሳይ፣ አጋጣሚው የሚሉትን በተግባር ሆነው ያገኙበት ሆኖ ማለፉን ተናግረዋል፡፡
ገንዘቡ በስህተት ገቢ የተደረገበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ቅርንጫፍም ለሲሳይ ተስፋዬ ታማኝነት እና አራያነት ያለው ተግባር የምስጋና እና የአድናቆት ደብዳቤ ሰጥቷቸዋል፡፡



