የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በ92 በመቶ ማደጉ ተገለፀ

0
814

ኢትዮ ቴሌኮም ከሐምሌ እስከ መስከረም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሞባይል እና መደበኛ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ደንበኞቹ ቁጥር ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ92 በመቶ መጨመሩን አስታወቀ። ከዘርፉ የተገኘው ገቢም የ33 በመቶ እድገት በማሳየት 2.91 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ታውቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬ ሕይወት ታምሩ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት፣ ቴሌኮሙ በያዘው የሪፎርም እቅድ እና በዓለምዐቀፉ ልምድ መሰረት የድምፅ አገልግሎት ይልቅ የዳታ አጠቃቀም ከፍተኛ መጨመር እያሳየ መምጣቱ፣ በመተግበር ላይ ያለው የቴሌኮሙ የንግድ ሞዴል ትክክለኛ መንገድ ላይ እንዳለ ያሳያል ብለዋል። በተገባደደው የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ21 በመቶ ከፍ ያለ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን በአጠቃላይ 10.1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ችሏል።

በሩብ ዓመቱ ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥም 1.4 ቢሊዮን ብር ግብር መከፈሉን ሥራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ 141 ሚሊዮን ዶላር ብድር የከፈለው ቴሌኮሙ፣ ከዚህ ውስጥ እስከ 2011 ድረስ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት ሲቀንስ የቆየው የቴሌኮሙ ዓለማቀፍ ገቢም 126 በመቶ መጨመር፣ 41.15 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ ተመዝግቧል። ከቴሌኮሙ አጠቃላይ ገቢ ውስጥም የዓለማቀፍ ግብይት ድርሻ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ብሎ የነበረ ሲሆን ባለፈው የበጀት ዓመት መጨመር የጀመረው ገቢው ባለፉት ሦስት ወራት ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 11.8 በመቶ የሚሆነው ከዓለም ዐቀፍ ገቢ የተገኘ እንደሆነ ቴሌኮሙ አስታውቋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ፍሬ ህይወት ታምሩ እንደገለፁትም፣ የዓለማቀፍ ንግድ የሥራ ክፍል እና የቴሌኮም ደኅንነት ክፍል በማቋቋም ከተለመደው የዓለማቀፍ ጥሪ በተጨማሪ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ገቢው እንዲሻሻል ለማድረግ ተችሏል ብለዋል።

‹‹ባለፈው ዓመት ያደረግናቸው ማሻሻያዎች ውጤታቸውን በዚህ ዓመት በደንብ መመልከት ችለናል። በአመራር እና በአሰራር ላይ ያመጣናቸው ለውጦች፣ የጀመርናቸው አዳዲስ አገልግሎቶች በገቢም ሆነ በደንበኞች አገልግሎቶች ላይ ለውጥ አምጥቷል›› ሲሉ ፍሬ ህይወት ተናግረዋል።

በሦስት ወር ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት 74 ሚሊዮን ብር ወጪ ያደረገ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚገኙ 34 ሺሕ ተማሪዎችም የትምህርት መሣሪያ ግዢ መፈፀሙ ተገልጿል። እንዲሁም ለአዛውንት፣ ለሴቶች፣ ለልጆች፣ ለወጣቶች፣ በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ እንዲሁም ለአረንጓዴ ልማት የተደረጉ ድጋፎች እንደነበሩም ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።

የቴሌኮም ደንበኞች ቁጥርም በሩብ ዓመቱ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 10.4 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ከ 40.26 ሚሊዮን ወደ 44.45 ሚሊዮን ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የቴሌኮም ገበያው ጋር ሲነፃፀር 45 በመቶ ነው። የዓለማቀፍ ጥሪ መጠንም በደቂቃ 80.4 ሚሊዮን በመሆን ካለፈው ሩብ ዓመት የ 143 በመቶ እድገት ማሳየቱን ቴሌኮሙ አስታውቋል። በተመሳሳይም የሞባይል ድምፅ ጥሪ የ15 በመቶ፣ የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በ13 በመቶ እድገት ሲያሳዩ የመደበኛ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ 1.17 ሚሊዮን ወደ 1.05 ሚሊዮን ዝቅ በማለት የ 10 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

በአጠቃላይ የቴሌኮሙ ደንበኞች 51.6 ሚሊዮን የተለያዩ መገልገያዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 93 በመቶ የሚሆኑት ቀፎዎች የአንድሮይድ ተጠቃሚ እንደሆኑ ቴሌኮሙ አስታውቋል። የስማርት ሞባይል ተጠቃሚ ቁጥርም ወደ 32 በመቶ ከፍ በማለት እድገት አሳይቷል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በቴሌኮም አገልግሎት ላይ ሲጋጥሙ የነበሩ የተለያዩ መቆራረጦች የደንበኞችን የቴሌኮም አገልግሎት አጠቃቀም ቀንሶት ነበር ያሉ ሲሆን፣ ቴሌኮሙም ፍላጎቱ እንዲያንሰራራ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ ገቢው አንዲሻሻል ለማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

በቴሌኮም ሴክተሩ ላይ እየተሠሩ ያሉ ሪፎርሞችን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ የተለያዩ የማይመለከታቸው አካላት የሚሰጡት የተዛባ ዘገባ ሊቆም እንደሚገባው እና ይህ ካልሆነ ግን ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ የመክፈቱ ሂደት ላይ የራሱ ጫና ይኖረዋል ብለዋል።

‹‹ለውጥ ሊፈጠር ነው ተብሎ ኢትዮ ቴሌኮም የሚፈራርስበት ሁኔታ አይፈጠርም፣ እንዲፈጠርም አናደርግም፤ አንፈቅድምም ጭምር›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፣ ‹‹ቴሌኮም እንዴት እንደሚሠራ እንኳን በቅጡ ያልተገነዘቡ እና በቂ እውቀት የሌላቸው ሰዎች ማብራሪያ በመስጠት እና ሠራተኞቻችን ላይ ሽብር ሲፈጥሩ እያየን ነው፤ ይህ ሃገርንም ተቋሙንም አይጠቅምም›› ሲሉ አሳስበዋል።

ለውጥ ሊመጣ ነው ሲባል ማንኛውም ሠራተኛ ሃሳብ ሊገባው እንደሚችል የተናገሩት ፍሬ ህይወት፣ የድርጅቱ አመራር ይህ ስጋት በሠራተኛው ውስጥ ሳይፈጠር ለውጡ እንዲሳካ በማድረግ የተረጋጋ እና ውጤታማ የሥራ ከባቢ መፍጠር ችሎ መዝለቁን አስታውሰዋል። የቴሌኮም ሴክተር ለደቂቃዎች እንኳን ያለመዘናጋት በትጋት የሚሠራ ሠራተኛን የሚፈልግ በመሆኑ የተለያዩ አካላት የሚያወጧቸው መረጃዎች አሁን ላይ የሠራተኛውን ስሜት በመረበሽ የእለት ተእለት ሥራው ላይ ተፅእኖ እንዳያመጣ መስጋታቸውን ተናግረዋል። ለዚህም የተሳሳተ መረጃ ሲያወጡ የነበሩ ተቋማት ማስተካካያ እንዲያደርጉ መደረጉንም ጨምረው ገልፀዋል።

ወደ ቴሌኮም ገበያው ይቀላቀላሉ የተባሉት ኹለት የቴሌኮም አንቀሳቃሾችም ቴሌኮሙን መሰረተ ልማት በኪራይ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ የገለፁት ፍሬ ህይወት፣ የራሳቸውን መሰረተ ልማት መገንባት እንደሚችሉም አዲስ የተቋቋመው የተቆጣጣሪ ኤጀንሲ አዋጅ መፍቀዱን ተናግረዋል።

አዳዲስ ቴሌኮም አንቀሳቃሾች መምጣታቸውን ተከትሎም ኢትዮ ቴሌኮም ራሱን እያዘጋጀ እንደሆነ አስታውቆ ይህ ሂደት ግን በተያዘው ዓመት መሰካቱ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ግን ገልፀዋል።

‹‹የቴሌኮም ሴክተር በጣም ውስብስብ በመሆኑ ፈቃድ ብድግ ተደርጎ የሚሰጥበት አይደለም። አሁን አራተኛው ወር ገብተናል፤ ስለዚህ ፈቃድ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች ይኖራሉ። ይህንን ለማድረግ ባለው ቀሪ ወራት ይሆናል ብለን አናስብም። ደግሞም ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ አንድ አገልግሎት ሰጪ ሲም ካርድ መሸጥ ይጀምራል ማለት እንዳልሆነ እኛ በሥራው ውስጥ ስለምንገኝ እናውቃለን።በኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ መገልገያዎቻቸውን አድረገው ሲም ካርድ ካልሸጡ በስተቀር በቀሩት ወራት አንድ አገልገሎት ሰጪ ገብቶ አገልግሎት ይሰጣል ብሎ መናገር አይቻልም›› በማለት በሚነሱ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here