የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በ7ሚሊዮን ብር ወጪ የደንብ ልብስ ተዘጋጀላቸው

0
588

በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለ362 ሠራተኞቹ የደንብ ልብስ ያሰፋ ሲሆን ለእያንዳንዱ ሠራተኛ በ20 ሺሕ ብር ገደማ ኹለት የደንብ ልብስ ከነመጫሚያው በማዘጋጀት እና በየአንድ ዓመቱ አዳዲስ ደንብ ልብስ ለመስጠት ማቀዱ ታወቀ።

በጽሕፈት ቤቱ በተለያዩ የሥራ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እና ባለሃብቶች የግብር አገልግሎት ለማግኘት ወደ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ እንደሚመጡ የተገለጸ ሲሆን፣ ደንበኞችን ደረጃውን በጠበቀ አለባበስ ለማስተናገድ እና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የራሱ የሆነ መለያን ለመፈጠር እንደሚረዳ የገቢዎች ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኡሚ አባጀማል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ለዩኒፎርም ዝግጅቱም ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።

የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ለሥራው የማይመጥን እና ለደንበኞች እይታ የማይስቡ ልብሶችን አድረገው ወደ ሥራ እንዳይመጡ ለማድረግ በማሰብ እንዲሁም በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ለሚስተናገዱ ተገልጋዮች የሚመጥን አለባበስን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲረዳ በማሰብ ከ362 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች ዩኒፎርም በማዘጋጀት እንዲለብሱ መደረጉ ተገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2012 የበጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 56 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 57.3 ቢሊዮን ብር ወይም የእቅዱን 102 በመቶ መሰብሰቡን ከቀናት በፊት ገልፆ ነበር።

ይህ አፈፃፀም በየወሩ ሲተነተንም በሐምሌ ወር 18 ቢሊዮን ብር፤ በነሐሴ ወር 20.2 ቢሊዮን ብር እና በመስከረም ወር ደግሞ 19.1 ቢሊዮን ብር በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ 57.3 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል።

በሩብ ዓመቱ ከተሰበሰበው ገቢ 54 በመቶ ያህሉ ከሀገር ውስጥ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው 46 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከጉምሩክ ገቢ የተሰበሰበ ነው። ይህ አፈፃፀም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ12.9 ቢሊዮን ብር ወይም የ29 በመቶ እድገት አሳይቷል።

ለእድገቱም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከማስተማር ጀምሮ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራዎችን የሠራ ሲሆን በዚህ ሩብ ዓመትም ከድርጊታቸው ያልተቆጠቡና ሀሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀም ግብይት የፈፀሙ 16 ድርጅቶች በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲዉሉ አድርጓል። በተመሳሳይ በግብይት ወቅት ደረሰኝ የማይቆርጡ ድርጅቶች ላይ የኢንተለጀንስ ሥራ በመሥራት 50 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲዉሉና 2.6 ሚሊዮን ብር አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲቀጡ አድርጓል።

ሠራተኛውና አመራሩ ሥራውን በብቃት መስራቱ እንዲሁም ግብር ከፋዩ ግብሩን በታማኝነትና በወቅቱ መክፈሉ ለዕቅዱ መሳካት ጉልህ ሚና እንደነበረው የተገለፀ ሲሆን፣ በያዝነው የጥቅምት ወር የገቢ እቅድ ካለፉት ወራቶች ከፍተኛ ስለሚሆን ሠራተኛውና አመራሩ ጠንክሮ በመሥራት፤ ግብር ከፋዩም ግብሩን በወቅቱ በመክፈል ለዕቅዱ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማድረግ እየተሠራ ነው ተብሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here